አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ኃይል በፍጥነት ማዘዣዎችንና የጦር ካምፖችን ነበር ማጥቃት የጀመረው፡፡ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በወታደራዊ ካምፖች ላይ በከፈታቸው ጥቃቶችም በርካታ የሱዳን ጦር ኃይልን ማሽመድመድ፣ ከትጥቅ ውጪ ማድረግና መበታተን ችሎም ነበር ይባላል፡፡ የሱዳን ጦር ኃይል በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ምት ለመፍትሔ ያልተገኘለት ሁለተኛ ዓመቱን የደፈነው የሱዳን ጦርነትና ቀጣናዊ ሥጋቱ ሱዳን እ.ኤ.አ. በ1956 ከእንግሊዝ ቅኝ ተገዥነት ከወጣች ጊዜ ጀምሮ ዋና ዋና የሚባሉ ሁለት የእርስ በእርስ ጦርነቶችን በትንሹ አስተናግዳለች፡፡ አገሪቱ ከዚህ በተጨማሪም በዳርፉር፣ በደቡብ ኮርዶፋንና በብሉ ናይል ግዛቶች ግጭቶችን ሲካሄዱባት ኖራለች፡፡ በግጭትና በጦርነት መፈተን ዕጣዋ የሆነው ሱዳን ከቅኝ ተገዥነት ነፃ ከወጣች ወዲህ ብቻ ወደ 19 ጊዜ የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገውባታል፡፡ ከእነዚህ መፈንቅለ መንግሥቶች ሰባቱ የተሳኩ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1989 ኦማር ሐሰን አል በሽር ወደ ሥልጣን የመጡበት አጋጣሚ አንዱ ነው፡፡ አል በሽር ከ30 ዓመታት በላይ የዘለቀ ሥልጣናቸውን አንድ ብለው የጀመሩት በመፈንቅለ መንግሥት ሲሆን፣ በስተመጨረሻም የሕዝብ ተቃውሞና ቁጣ ሲበረታባቸው የእሳቸው ታማኝ በነበሩት በሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ በጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ትብብር ነበር ከሥልጣናቸው ተገደው የተፈነቀሉት፡፡ አል በሽርን ለማስወገድ የተባበሩት ሁለቱ የጦር ጄኔራሎች አልቡርሃንና ሄሜቲ ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ አግኝቶ የነበረውን በአብደላ ሃምዶክ የሚመራውን የሲቪል አስተዳደርም ለማፍረስ እስከ መተባበር ድረስ ሄደው ነበር፡፡ ሁለቱ ጄኔራሎች አብደላ ሃምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ የሱዳን የሽግግር ጊዜ ምክር ቤትን በብቸኝነት ተቆጣጠሩት፡፡ የሱዳን ጦር መሪው ጄኔራል አልቡርሃን ዋና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ሄሜቲ ደግሞ ምክትል ሆነው ጊዜያዊ የሽግግር ጊዜ መንግሥቱን ይመሩት ጀመር፡፡ ይህ ግን ብዙም ለመዝለቅ ሳይችል ቀረ፡፡ ሁለቱ የጦር ጄኔራሎች ተባብረው መንግሥት ከመገልበጥ በዘለለ ተባብረው አገር መምራትና ወደ ዴሞክራሲ ማሸጋገር ሲሳካላቸው አልታዩም፡፡ አንዱ በሌላው ላይ መሣሪያ በማንሳቱ ሱዳን ላለፉት ሁለት ዓመታት ከባድ ጦርነት ሲካሄድባት ቆይታለች፡፡ በጄኔራል ሄሜቲ የሚመራው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 15 ቀን 2023 ጦርነቱ መፈንዳቱን ተከትሎ፣ በጄኔራል ማፈግፈግ ተገዷል፡፡ ከካርቱምና ከሌሎችም በርካታ አካባቢዎች ለቆ የቀይ ባህር ጠረፍ የምትገኘው ፖርት ሱዳን ከተማ ዋና መቀመጫውን አዛውሮም ነበር፡፡ ለሁለት ዓመታት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በጦርነቱ ብልጫውን የወሰደ ይመስል ነበር፡፡ ዘንድሮ ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ግን የሱዳን ጦር ጠንካራ የሚባል የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ መክፈት ጀመረ፡፡ ለ22 ወራት ከእጁ ወጥተው የነበሩ እንደ ኦምዱርማንና ካርቱም ያሉ አካባቢዎችን መልሶ መቆጣጠር ጀመረ፡፡ የሱዳን ጦር በዚህ ብቻም ሳይወሰን ወደ ምሥራቃዊ የሱዳን ግዛቶች መገስገስ ቀጠለ፡፡ በአልጄዚራ፣ እንዲሁም በገዳሪፍ ግዛቶች ይዞታውን መልሶ ማጠናከር ቀጠለ፡፡ በአጠቃላይ የሱዳን ጦር መልሶ ማጥቃቱን በጀመረ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደ 430 ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን በተለያዩ የሱዳን ግዛቶች ውስጥ ማስለቀቁ ነው የተነገረው፡፡ አሁን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በኮርዶፋንና በዳርፉር ግዛቶች አካባቢ ተወስኗል ነው የሚባለው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር መከበቡን እየተናገሩ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሱዳን የራሴ የሚለውን መንግሥት በያዛቸው አካባቢዎች መመሥረቱን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ የጄኔራል ሄሜቲ ኃይል አሁንም ቢሆን ጠንካራ የውጊያ አቅም እንዳለው ይነገራል፡፡ የውስጥም የውጭም አጋሮች ያሉት ሲሆን፣ ቁልፍ የገቢ ምንጭ የሆኑ የማዕድን ቢዝነሶችን የተቆጣጠረና በተለያዩ መንገዶች ዶላርም ቁሳቁስም ይዞ ይገኛል ይባላል፡፡ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ 100 ሺሕ ተዋጊ ኃይል እንዳለው የሚነገር ሲሆን፣ ረዥም ሰንሰለት ያለው የወርቅ ንግድ የዘረጋ፣ በየመንና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ቅጥረኛ ወታደሮችን በመላክ ዳጎስ ያለ ገቢ ያገኘ ኃይል በመሆኑ ጦርነቱን ለመቀጠል አሁንም አቅሙ አለው እየተባለ ነው፡፡    የቀጣናውን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፖለቲካ ተንታኝ፣ በሱዳን ያለው ጦርነት አገሪቱን ወደ መገነጣጠል ሊወስዳት እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ሰኞ ዕለት የኮሎምቢያ ቅጥረኛ ወታደሮች ከሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ ፑንትላንድ  ቦሳሱ ወደብ ከተማ በአውሮፕላን ተጭነው ወደ ምዕራብ ሱዳን መግባታቸው ተረጋግጧል፡፡ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ለማገዝ ዕርዳታ በምታደርግለት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ እንደተላኩ ነው የሚጠረጠረው፡፡ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በውጭ ኃይሎች ታግዞ ውጊያ ሊቀጥል ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል፡፡ ፈጥኖ ደረሽ ኃይሉ ራሱን የቻለ መንግሥት እንደመሠረተም አውጇል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ሱዳን ለሁለት ልትከፈል ትችላለች፡፡ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉርና በደቡብ ኮርዶፋን ነው በዋናነት የመሸገው፡፡ ሄሜቲ ከዳርፉር የወጡ ሰው ሲሆኑ ሌላው በሱዳን ፖለቲካ ተፅዕኖ ያላቸው እንደ አብደላ ሃምዶክ ያሉ ፖለቲከኛ ደግሞ የኮርዶፋን ተወላጅ ናቸው፡፡ በእነዚህ ግዛቶች ግጭት መቀጠሉ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ በተለይም ሄሜቲ ዋና የሥልጣን ማዕከል ባደረጓት በሰሜን ዳርፉር አልፋሸር አካባቢ የከፋ ግጭት ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ አሁን ዳርፉር 20 ታጣቂ ቡድኖች የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ነው፡፡ ዳርፉር ራሱ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምዕራብ፣ መካከልና ምሥራቅ ተብሎ የሚከፋፈል ሰፊ ግዛት ሲሆን፣ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉም ሆነ ከሱዳን ጦር ጋር የሚዋጉ በርካታ አማፂያን በተለይም የጎሳ ሚሊሻዎች ተፈልፍለውበታል፡፡ እነዚህን ኃይሎች ለመውሰድና ከጎን ለማሠለፍ ሁለቱ የሱዳን ጦር ኃይሎች እየተፎካከሩ ነው፡፡ በእኔ ግምት ሱዳን ዚያድ ባሬ ከወደቀ በኋላ ሶማሊያ እንደሆነችው ዓይነት ነገር ሊገጥማት የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ሰፊው የዳርፉር ግዛት ብቻ ለምሳሌ ከአራት የጎረቤት አገሮች ጋር ይዋሰናል፡፡ ቻድ፣ ሊቢያ፣ ደቡብ ሱዳንና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የግዛቱ ተጎራባች ሲሆኑ ጦርነቱን ያለ መሣሪያ ችግር ለመቀጠል ግዛቱ አመቺ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ ይህንኑ ግምት የሚያጠናክር ሐሳብ ያስነበበው ክራይሲስ ግሩፕ በበኩሉ፣ የሱዳን ጦርነት ወደ ጎረቤት አገሮች የመጋባት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ክራይሲስ ግሩፕ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት የሱዳን ጦርነት ወደ ቻድና ወደ ደቡብ ሱዳን እየተዛመተ መሆኑን በሰፊው አትቷል፡፡ ሪፖርቱ ሱዳንና ቻድ ከሃያ ዓመታት ቀደም ብሎ በድንበር ተሻጋሪ ግጭት ሲታመሱ መኖራቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ አሁን በሱዳን በሚካሄደው ጦርነት ዋና ተሳታፊ ለሆነው ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጎረቤት ቻድ ዋናዋ የጦር መሣሪያ መተላለፊያ መሆኗን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፣ ይህ ደግሞ አዲስ ድንበር ተሻጋሪ ግጭት እንዳያመጣ ያሠጋል ይላል፡፡ የክራይሲስ ግሩፕ ሪፖርት እንደሚለው ደቡብ ሱዳንም ቢሆን በአዲስ ዙር የእርስ በእርስ ጦርነት አፋፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ አዲስ ዙር የደቡብ ሱዳን ግጭት ከተባባሰ ደግሞ በሰሜን ሱዳን ለሁለት ዓመታት ከቀጠለው ጦርነት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ቀጣናዊ የሆነ ቀውስ ሊፈጥር ይችላል ይላል ሪፖርቱ፡፡ የሰሜን ሱዳን ጦርነት ቀጣናዊ ቀውስ ወደ መሆን የሚሸጋገረው ግን በቻድና በደቡብ ሱዳን በኩል ብቻ እንዳልሆነ ክራይሲስ ግሩፕ ያስረዳል፡፡ ሱዳን በስተምሥራቅ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰን አገር መሆኗን በሚያስታውስ መንገድ፣ ሱዳን ወደ ሁለቱ አገሮችም ጦርነት ለመላክና ለመቀበል የምትችልበት ሰፊ ዕድል መኖሩን ነው ያመለከተው፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት እየሻከረ በሒደት ወደ ግጭት ሊያመራ አፋፍ ላይ መድረሱን ያመለከተው ሪፖርቱ፣ ይህ ሁኔታ ወደ ግጭት የሚያመራ ከሆነ ደግሞ ከሱዳን ጦርነት ጋር ሊዛመድ እንደሚችል ነው የጠቆመው፡፡    ለሪፖርተር አስተያየታቸው የሰጡት የፖለቲካ ተንታኙ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው ረዥም ዘመናት ያስቆጠረ የድንበር ይገባኛል ውዝግብ በቀላሉ አይፈታም ነው የሚሉት፡፡ ሱዳኖች ወረው በያዙት ኢትዮጵያ ይገባኛል በምትለው መሬት የተነሳ የሱዳን ጦርነት በቀጠለ ቁጥር የተለየ ነገር ይፈጠራል ብለው እንደማይሠጉ ነው የጠቆሙት፡፡ ‹‹በሱዳን ጦሩ እያሸነፈ ከቀጠለ በየቦታው ለሚሊታሪው ታዛዥ የሆነ መዋቅር ይፈጠራል፡፡ ይህ ደግሞ አወዛጋቢው የድንበር መሬትንም ይጨምራል፡፡ ሆኖም ቀስ በቀስ በየቦታው የተለያዩ የጦር አበጋዞች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ጄኔራል አልቡርሃን ከሚመሩት የሱዳን ጦር ውስጥም ራሱን የቻለ አማፂ ወይ አንጃ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በደቡብ ሱዳን እንደሆነው ከአንድ የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ (SPLM) ከተባለ ቡድን ውስጥ እየተከፈሉ ብዙ ቡድኖች እንደወጡት ሁሉ፣ አሁን ካሉት ተዋጊ ኃይሎች ውስጥም ተከፍለው የሚወጡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በደቡብ ሱዳን የሪክ ማቻር፣ የሳልቫ ኪር፣ አሁን ደግሞ ዋይት አርሚ እየተበሉ ብዙ አንጃዎች ተፈጥረዋል፡፡ ይህ ወደ ሰሜን ሱዳን ሊመጣም ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ አክራሪ የእስልምና ቡድኖችም ሊወጡ ይችላሉ፡፡ እስላማዊ ብርጌድ የሚባለውን ኃይልን የአልቡርሃን ቡድን ካርቱምን ለማስለቀቅ ተጠቅሞበታል፤›› በማለት የሃይማኖት ታጣቂ ቡድኖች በሱዳን ሊፈለፈሉ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ከሰሞኑ የሱዳን ጦር ካርቱምን አስለቅቆ መልሶ መቆጣጠሩ በተነገረበት ወቅት፣ አል ባራ ቢን ማሊክ ብርጌድ (AlBaraa Bin Malik Brigade) የተባለው ከጦሩ ጎን የተሠለፈ ታጣቂ ኃይል ጎልቶ ስሙ ሲጠራ ነበር፡፡ የወታደራዊ ጉዳዮች አጥኚው መሐመድ አባስ ለአንድ የዓረብ ሚዲያ እንደተናገሩት ከሆነ ግን፣ ቡድኑ በሱዳን የፖለቲካ ለውጥ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ መደራጀቱንና ዛሬ 20 ሺሕ ተዋጊዎች አደራጅቷል፡፡ ይህ ቡድንም ሆነ ሌሎች በሁለቱ ዋና ዋና ተፋላሚ ኃይሎች ካምፕ የተሠለፉ የሚሊሻ ኃይሎች ለየተሠለፉበት ቡድን፣ ታማኝነታቸውን ይቀጥላሉ ወይስ ሌላ ዓይነት ግጭት በሱዳን ይፈጥራሉ የሚለው አሳሳቢ መሆኑን ነው መሐመድ ያስረዱት፡፡    በሱዳን ከታጠቁና መሣሪያ ካነገቡ ኃይሎች በተቃራኒው በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራትን ያሰባሰበው በአብደላ ሃምዶክ ይመራ የነበረው የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች ቅንጅት (Forces for Freedom and Change/ FFC) የተባለው የፖለቲካ ቡድንም ቢሆን ተዳከመ እንጂ ጨርሶ አለመጥፋቱ ይነገራል፡፡ ይህ የፖለቲካ ኃይል በሱዳን ፖለቲካ በቀጣይ ምን ዓይነት ሚና ይኖረዋል የሚለው ጉዳይም በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው ነው በርካታ ተንታኞች የሚጠቁሙት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በርካታ የዓረብ አገሮችን ጨምሮ ኤርትራን አስተባብረው በየመን ሁቲ አማፂያን ላይ ጦርነት ሲያውጁ፣ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በርካታ ተዋጊ በመላክ ተሳትፎ ነበር፡፡ ሱዳን ቅጥረኛ ወታደሮችን የምትልክ አገር እንድትሆን ያስቻለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሊቢያም ውጊያ ወታደሮቹ ገብተው መካፈላቸው ታውቋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ጸሐፊው አሌክስ ደዋል በወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ድረ ገጹ ላይ ከሰሞኑ እንደከተበው፣ ጄኔራል ሄሜቲ የአሜሪካውን ዲከንስና ማድሰን የተባለ የውትወታ (ሎቢ) የሚሠራ ቡድን ቀጥረዋል፡፡ ይህ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጪዎችን ለማሳመን የሚሠራ የሎቢ ቡድን ደግሞ ከዚህ ቀደም በዚምባብዌው ሮበርት ሙጋቤ፣ እንዲሁም በሊቢያው ጄኔራል ካሊፋ ሀፍታር ጭምር ተቀጥሮ የነበረ መሆኑን በመጥቀስ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪው ጄኔራል ሄሜቲ የምዕራቡን ዓለም በሎቢ ቡድን በማሳመን፣ ከእነ ሩሲያና ከእነ ዓረብ ኤምሬትስ ደግሞ የመሣሪያና የሎጂስቲክስ ድጋፍ ለማግኘት የሚሞክሩ የጦር ሰው መሆናቸውን አመልክቷል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የሱዳን ጦርን በርካታ አገሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲደግፉት መቆየታቸው፣ ግብፅና ኤርትራ በቀጥታ ጦር በማስገባት ጭምር የሱዳን ብሔራዊ ሠራዊትን ማገዛቸው ይነገራል፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያም ይህንኑ በጄኔራል አልቡርሃን የሚመራ ሠራዊት ትደግፋለች ይባላል፡፡ የቅርብ ሰሞን ሪፖርቶች ደግሞ የሱዳን ጦር ጠንካራ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በከፈተበት ወቅት፣ የትግራይ ጦርነት ሲፈነዳ ከኢትዮጵያ ተሰዶ በሱዳን የቆየው የሕወሓት ክንፍ ነው የሚባል ሠራዊት ዕገዛ አድርጎለታል እየተባለ ነው፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የፖለቲካ ተንታኙ ሳዑዲና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በሱዳን ጦርነት ረዥም እጃቸውን እንደከተቱ ይናገራሉ፡፡

‹‹የቀይ ባህር ተዋሳኝ የሆነችው ሳዑዲ ከሱዳን በሚነሳ የሕዝብ ስደትም ሆነ በቀጣናው ባላት የፀጥታ ሥጋት ለሱዳን ጦርነት ልዩ ትኩረት ሰጥታዋለች፡፡ አገሪቱ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር የገባችበት ፉክክርም ለሱዳን የራሱ ጣጣ አለው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስም ብትሆን የቀይ ባህር ፖለቲካን መራቅ አትፈልግም፣ አባል መሆን ትፈልጋለች፡፡ አገሪቱ የወርቅ ንግድ ከሄሜቲ ጋር በከፍተኛ ደረጃ ታካሂዳለች፡፡ ዓረብ ኤምሬቶች ብዙ ዓይነት ፍላጎት ነው በቀጣናው ያላቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ወደ ትግራይ መድኃኒትና ሌላም ብዙ የቁሳቁስ ዕርዳታ ልከዋል፡፡ ወልቃይትን ጨምሮ ሱዳንና ኢትዮጵያ የእኔ ነው የሚሉትን አልፋሽቃን እንረሰው ብለው መጠየቃቸውም የታወቀ ነው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ቀጣናዊ ተፅዕኖ ያለው ኃይል ለመገንባት ይፈልጋሉ፤›› በማለት ነው ሐሳባቸውን የገለጹት፡፡ የክራይሲስ ግሩፕ ሰሞነኛ ሪፖርት በሱዳን ሰላም ሊሰፍን የሚችለው በምን መንገድ እንደሆነ ባጠያየቀበት ግርጌ፣ በሱዳን ጦርነት ውስጥ ይብዛም ይነስም እጃቸውን ያስገቡ ኃይሎች በሙሉ የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና ሲጫወቱ እንደሆነ በሰፊው አብራርቷል፡፡ የሱዳን ጦር አዛዥ ጄኔራል አልቡርሃን አሁን ድላቸውን ማስቀጠል እንጂ ድርድር ብሎ ነገር አይፈልጉም፡፡ ጄኔራል አልቡርሃን ብቻ ሳይሆኑ ከእሳቸው በስተጀርባ ከተሠለፉ አጋሮቻቸው መካከል ድርድርና ሰላማዊ የመፍትሔ አማራጭን መስማት የማይፈልጉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልም ቢሆን አሁን ቁስሉን በማከክ፣ አቅሙንና ደጋፊዎቹን አሰባስቦ ዳግም ስለሚከፍተው ዘመቻ ከማሰላሰል በዘለለ ለሰላም እጁን ሲዘረጋ አይታይም በማለት ነው ሪፖርቱ ያተተው፡፡ ከሁለቱም ኃይሎች ጀርባ የተሠለፉ አጋሮች የድሮን፣ እንዲሁም ፀረ ድሮን ቴክኖሎጂን ጨምሮ አሉ የሚባሉ መሣሪያና ትጥቆችን ያቀርቡላቸዋል፡፡ ከሱዳን ብሔራዊ ጦር ጀርባ ግብፅ ዋና አጋር ሆና እንደተሠለፈችው ሁሉ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጀርባ ደግሞ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዋና አጋር ሆና መቆሟ ይነገራል፡፡ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በሰሜንና በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢዎች ለረዥም ዓመታት ሲንቀሳቀስ ከቆየው የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ በሰሜን (Sudan People’s Liberation Movement-North/ SPLM-North) ከተባለው ሸማቂ ቡድን ጋር አዲስ አጋርነት ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሁለት ግዛቶች ደግሞ በተለይ ሱዳንን ከደቡብ ሱዳን ጋር ብቻ ሳይሆን ከምዕራባዊ የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር የሚያጎራብቱ በመሆናቸው ጦርነቱ በቀላሉ ወደ እነዚህ አገሮች እንዲዛመት የሚያደርግ ነው፡፡ በቅርቡ በኬንያ ባደረጉት ስብሰባም ይህንኑ አጋርነት ያጠናከሩ ሲሆን፣ ሁለቱ ኃይሎች በመተባበር በሰሜን ሱዳን በደቡብ ኮርዶፋንና በብሉ ናይል ግዛቶች የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለማካሄድ በመዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጦርነቱን ወደ ሰሜናዊ የሱዳን ጫፍም የመውሰድ ዕቅድ አለው፡፡ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በቅርቡ በሰሜናዊ ሱዳን ክፍሎች ጥቃት መጀመሩን አውጆም ነበር፡፡ በተቃራኒው የሱዳን ብሔራዊ ጦር ተይዘው የቆዩ የሱዳን ግዛቶችን ለማስመለስ ለከፈተው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በየአካባቢው ብዙ ዓይነት የሚሊሻ ቡድኖችና ታጣቂዎችን በማደራጀት አስተባብሮ ሲያዋጋ ቆይቷል፡፡ እነዚህ የሚሊሻ ቡድኖችም የሱዳን ፖለቲካ ላይ የሚያመጡት ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያና ግብፅ በቀጥታ የሚደግፉትን የሱዳን ብሔራዊ ጦር አዛዥን ጄኔራል አልቡርሃንን ወደ ሰላም እንዲመጡ ማስገደድ ይችላሉ፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ደግሞ በቀጥታ የምትደግፈው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ሄሜቲ ወደ ሰላም እንዲመጡ ማስገደድ ትችላለች፡፡ ግብፅም ቢሆን በአፍሪካ ኅብረት በኩል በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የድርድር ጥረት እንዲጀመር ማድረግ ትችላለች፡፡ በሌላ በኩል የአንካራ፣ የዶሀ፣ የአዲስ አበባና የናይሮቢ መንግሥታትም ቢሆን ለሱዳን ሰላም ጠቃሚ ሚና መጫወት ይችላሉ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የዓረብም ሆነ የአፍሪካ አገሮች ዋና አጋር የሆኑት ምዕራባዊያኑ ተፅዕኗቸው ከፍተኛ ነው፡፡ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ለሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ቅርብ የሆኑ መንግሥታትን በመጠቀም በሱዳን የሰላም ጥረት እንዲደረግ ተፅዕኖ መፍጠር ይችላል፡፡    ይህን ሁሉ የዘረዘረው የክራይሲስ ግሩፕ ሪፖርት፣ ከሰሞኑ የሱዳን ጦርነት ሁለተኛ ዓመት መድፈንን ተከትሎ በእንግሊዝ ለንደን የተጀመረው ስለሱዳን ሰላም የሚመክረው ስብሰባ ጠቃሚ ዕርምጃ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) የመሩት የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን፣ በለንደኑ የሱዳን ሰላም ጉባዔ ላይ መካፈሉን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በሱዳን ተኩስ አቁም ማድረግ ስለሚቻልበት፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሥራ ስለሚመቻችበትና የሱዳን ግጭትን በሰላም ለመፍታት ስለሚቻልበት ሁኔታ በዚሁ ጉባዔ የተለያዩ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት መመካከራቸው ተነግሯል፡፡ የለንደኑ ጉባዔ በበጎ ቢጠቀስም ይሁን እንጂ ዋነኞቹ የጉዳዩ ተዋንያን የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች አለመካፈላቸው፣ መድረኩ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችል ስለመሆኑ በጥርጣሬ እንዲታይ ያደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙ እንደሚገልጹት የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ የሱዳንን ቀውስ ማወሳሰቡ ይቀጥላል፡፡ ‹‹እስራኤል ቀይ ባህር ቀጣና ላይ ለምዕራባዊያን ያጋደሉ መንግሥታት እንዲፈጠሩ ፍላጎት አላት፡፡ የየመን ሁቲዎች የፈጠሩት የመርከብ ዕገታና ጥቃት በቀይ ባህር የምዕራባዊያንን ፍላጎት የሚያስቀድም የሁቲዎችና የኢራንን እንቅስቃሴ የሚገታ ኃይል መፈጠር አለበት እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡ በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲዎች የመርከብ ዕገታ ተራ እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ምዕራባዊያኑ ትኩረት የሰጡት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ በእነ ሱዳንም ሆነ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል ሕወሓት አሁንም በአፍሪካ ቀንድ ተፈላጊ ለመሆን መጣሩን ይቀጥላል፡፡ ሕወሓትም ሆነ ይህን መሰል ፍላጎት ያላቸው የታጠቁ ኃይሎች ምናልባት ልክ እንደ ቺቺኒያ ዓይነት ፖለቲካ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ እንደ ፑቲን የሚሆኑትም ሆነ እንደ ራምዛን የሚሆኑት ኃይሎች ማን ናቸው የሚለውን በሒደት እናያለን፡፡ ከዚህ በመለስ ኤርትራ ሁሌም ቢሆን የህልውና ጥያቄ ነው ያለባት፡፡ የኤርትራ መንግሥት ህልውናውን ለአንድም ቀን ቢሆን የሚያስቀጥልለት ወገን ካገኘ መጠጋቱ የማይቀር ጉዳይ ነው፤›› በማለት በሱዳን ብቻ ሳይሆን፣ በተጎራበተችው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ይሆናል የሚሉትን ክስተት አብራርተዋል፡፡ በሁለት ዓመት ውጊያ የሱዳን ተፋላሚዎች ሱዳንን 33 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አከናንበዋታል፡፡ የአገሪቱ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) ወደ 40 ከመቶ ተኮማትሯል፡፡ ወደ 20 ሺሕ ሰዎች ስለመገደላቸው ቢመዘገብም በአንዳንድ ግምቶች ከ150 ሺሕ በላይ ሕዝብ ማለቁ እየተነገረ ነው፡፡ ሱዳን ከባድ የሰብዓዊና የመሠረተ ልማት ውድመት ከማስተናገድ ባለፈ እንደ ኮሌራ ያሉ ወረርሽኞች ደጋግመው የሚጎበኙዋት ሆናለች፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነም ተፋላሚዎቹ ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት አጥተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ቀጣናውን እንዳያቃውስ ሥጋት እየፈጠረ ነው፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *