ተቋርጦ የቆየው የመጀመሪያ ዙር 75 ሺሕ የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች ትጥቅ የማስፈታት፣ መልሶ የማቋቋምና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ በሰኔ ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ በ2017 ዓ.ም. ሰኔ ወር መጨረሻ ድረስ የትግራይ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን የሠራዊት ብተና (Demobilization) ለማድረግ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ቅድመ ተዋጊ መሆናቸውን የማረጋገጥ፣ የመመዝገብና ከተመዘገቡ በኋላ ደግሞ ዲጂታል መታወቂያ የመስጠት ሥራ የሚያከናወን መሆኑን፣ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሙዩኒኬሽንና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ መለስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኅዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ያስጀመረው የሠራዊት ብተና (Demobilization)፣ ትጥቅ የማስፈታት (Disarmament) እና መልሶ ከማኅበረሰቡ ጋር የመቀላቀል (Reintegration) ፕሮግራም በመጀመሪያ ዙር በአራት ወራት ውስጥ 75,000 የቀድሞ ታጣቂ ኃይሎችን ለማሠልጠን ዕቅድ መያዙ ይታወሳል፡፡ ፕሮግራሙን ለማከናወን በክልሉ በሦስት ቦታዎች ማለትም በመቀሌ፣ በዕደጋ ሐሙስና በዓድዋ በሚገኙ ማዕከላት እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ የተጠቀሰውን አኃዝ በየቀኑ በመመዝገብ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡ በተለይ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል ሥራ በኦሮሚያ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግና ላለፉት ሁለት ወራት በትግራይ ክልል ተጀምሮ የነበረው ምዝገባ ተቋርጦ እንደነበር አክለው ገልጸዋል፡፡ ከዓለም አቀፍ አጋር አካላት በተገኘ 60 ሚሊዮን ዶላርና የፌዴራል መንግሥት ባቀረበው አንድ ቢሊዮን ብር ድጋፍ፣ የትግራይ ክልል የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት ከሠራዊት የማሰናበትና የማቋቋም (DDR) የመጀመሪያ ሥልጠና መቋረጡን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ ለመልሶ ማቋቋሚያ ሥልጠናቸውን ላጠናቀቁ የቀድሞ የፀጥታ አካላት ስለሚሰጥ የገንዘብ ድጋፉን በተመለከተም ፕሮግራሙ በተጀመረበት በኅዳር ወር ሪፖርተር ያነጋገራቸው በመጀመሪያው ዙር የተካተቱ የቀድሞ ታጋዮች 200,000 ብር እንደሚከፈል እንደተነገራቸው ሲገልጹ፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የኮሚሽኑ ኃላፊ በበኩላቸው ለእያንዳንዱ የቀድሞ ተዋጊ የሚከፈለው የገንዘብ መጠን የተለያዩ መሆኑን፣ ኮሚሽኑም ለሕዝቡ ይፋ የሚያደርገውን በሚስጥር የሚይዝ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡ በወቅቱም የትግራይ ክልል የፀጥታ ኃይል ሠራዊ ውስጥ መቀጠል የለባቸውም ብሎ ያመነባቸው 80 በመቶ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ ፈትተው የቀድሞ ተዋጊዎች እንዲበተኑ ከተደረገ በኋላ የተሃድሶ ሥልጠና የሚወስዱ መሆናቸውን፣ በኋላም ዲጂታል መታወቂያ ወስደው ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ይደረጋሉ መባሉ ይታወሳል፡፡ በመላ አገሪቱ ትጥቅ በመፍታት ወደ ማኅበረሰቡ ይቀላቀላሉ ተብለው የሚጠበቁ 375 ሺሕ የቀድሞ ተዋጊዎች መሆናቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ 270 ሺሕ ያህሉ በትግራይ ክልል እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *