ተባባሪ ፕሮፌሰሩ የሚከፈለኝ የወር ደመወዝ 99 ዶላር ነው ብለዋል የመምህራን ሕይወት አለመለወጥ ለትምህርት ጥራት መውደቅ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት የመምህራን ሕይወት የሚቀየርበት አሠራር እንዲዘረጋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ፡፡ ጥያቄ የቀረበው ምክር ቤቱ የትምህርት ሚኒስቴርን የስምንት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ሲገመግም ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ባቀረቡት ሪፖርት፣ በ2017 ዓ.ም. አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ መርሐ ግብሮች 26.7 ሚሊዮን  ተማሪዎች ተመዝግበው በመማር ላይ እንደሚገኙ፣ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል 25.2 ሚሊዮን ተማሪዎች፣ በጎልማሶች መሠረታዊ ትምህርት በርቀት፣ በቀንና በማታ ፕሮግራሞች 1.5 ሚሊዮን ተማሪዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 872 ሺሕ ተማሪዎች በግልና የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ 5,354 ትምህርት ቤቶች በሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት የመማር ማስተማር ሥራዎችን ማከናወን ባለመቻላቸው፣ በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ 7.2 ሚሊዮን ወይም 22.4 በመቶ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አለመመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚያመላክተው፣ በኢትዮጵያ ከሚገኙ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች 85 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከደረጃ በታች ናቸው፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ ወ/ሮ ለጢፋ ከተማ የተባሉ የምክር ቤት አባል ባቀረቡት ጥያቄ፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራን ሕይወት መቀየር፣ የኑሮ ደረጃቸውን ማሻሻል ቁልፍ ተግባር መሆኑን፣ የራሱን ልጅ በአግባቡ ማስተማር ያልቻለ የሕዝብን ልጅ በአግባቡ ሊያስተምር እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ ገነነ ገደቡ (ረዳት ፕሮፌሰር) የተባሉ የምክር ቤት አባል፣ መምህራን ራሱን መስዋዕት እንደሚያደርግ ወታደር አገራቸውን የሚጠብቁ በመሆናቸውና የሚጫወቱት አገራዊ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ መንግሥት የኑሮ ሁኔታቸውን ሊያሻሽልላቸው ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አክለውም ‹‹መምህራን ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች የትምህርት ሚኒስቴር ምን ያህሉን ፈትቷል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ በብዙ የትምህርት ውድቀት ባጋጠማቸው አገሮች አንደኛው የተሠራበት ጉዳይ የመምህራን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ማሻሻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት ወደ ረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሲሸጋገሩ 356 ዶላር በወር ያገኙ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን እያገለገሉበት ባለው የተባባሪ ፕሮፌሰነት ማዕረግ እያገኙ ያሉት የወር ደመወዝ 99 ዶላር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ ዝቅተኛ ደመወዝ ብቻ ሳይሆን ኢሞራላዊ ነው፤›› ያሉት የምክር ቤት አባሉ፣ የኢትዮጵያ መምህራን የሚከፈላቸው ደመወዝ ልጆቻቸውን አብልተው እንዲያድሩ፣  ልጅ እንዲያስተምሩና  ልብስ እንዲቀይሩ አያስችልም ብለዋል፡፡ ‹‹ሞራሉ የተጎዳ መምህር ይዘን ነገ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ዜጋ ይፈጥራል ብሎ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ጉዳይ በትምህርት ሚኒስቴር ግፊት ተደርጎበት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የማሻሻያ በጀት ተጠይቆ ወደ እኛ ምክር ቤት ይቅረብልን፤›› ያሉት ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ በእኛ በኩል ደግሞ ምክር ቤቱ ያፀድቃል አያፀድቅም የሚለውን እናያለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያ፣ በአማራ በአፋርና ትግራይ ክልሎች አሥር ሚሊዮን የሚደርሱ ሕፃናት በትምህርት ገበታ ላይ አለመሆናቸው ቢገለጽም፣ ከትምህርት ሚኒስትሩ መረጃ ጋር የሚጋጭ መሆኑን አክለው አስረድተዋል፡፡ ‹‹በዚህ አገር በተደጋጋሚ እንደምናገረው የቅድሚያ ቅድሚያ አሰጣጥ ችግር አለ፡፡ በርካታ ገንዘብ ቅድሚያ ለማይሰጠው ጉዳይ ይጠፋል፡፡ ልጆቻችን የምናስተምርበት የትምህርት ሥርዓትና የፈራረሱ ትምህርት ቤቶችን ለመጠገን መንግሥት የሚያፈሰው ሀብት ግን ዝቅተኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩን ሪፖርት ጠቅሰው ባነሱት ጥያቄ ከለጋሽ ድርጅቶችና ከኅብረተሰቡ ተሳትፎ በተገኘ ገንዘብ የተከናወኑ ሥራዎች እንጂ፣ በመንግሥት በኩል ሀብት ተመድቦ አዲስ ትምህርት ቤት ስለመገንባቱ በሪፖርቱ ምንም ነገር አልተመላከተም ብለዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስትሩ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ በአጠቃላይ  በአገሪቱ ለሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛው የሚከፈለው ደመወዝ ዝቅተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  መምህራን የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ማዕቀፍ ውስጥ በመሆናቸው፣ የደመወዝ ስኬሉን የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻውን ሊሠራው አይችልም ብለዋል፡፡ ነገር ግን መምህራን የሚከፈላቸው ደመወዝ ከሌላው ያነሰ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሙያው ከችግር እንዲወጣ መደረግ አለበት ሲሉ አክለዋል፡፡ እየተቸገሩና ‹ልጄን ምን አበላሁ?› እያሉ ሳይሆን፣ በቂ ደመወዝ ተከፍሏቸው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ሊያኖሩ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ መንግሥት የደመወዝ ማስተካከያ ለማድረግ ረዥም ጊዜ ሕልሙ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ለማስተካከል ቢያንስ ለመምህራን የመኖሪያ ቤት መሥሪያ የሚሆን መሬት በመንግሥት ቢቀርብላቸው ብለው፣ ፋይናንስ የሚያደርጋቸው የመምህራን ባንክ በሚቀጥለው ዓመት ለማስጀመር ትልም መያዙን ተናግረዋል፡፡ ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ ተማሪዎች ቁጥር አሥር ሚሊዮን ነው በሚል የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት መረጃ ያመላክታል ተብሎ በቀረበው ጥያቄ፣ ‹‹እኔ እሱን አላምንም፤›› ብለዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *