የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተናን አስመልክቶ ባወጣው መመርያ መሠረት፣ ዘጠና ያህል የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚያስፈትኗቸው ተማሪዎች 75 በመቶ ያህሉን ማሳለፍ ባለመቻላቸው መዘጋታቸው ተነገረ፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ኮራ ቱሹኔ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የአፍሪካ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት፣ ዘጠና ያህል የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተዘግተዋል፡፡
መንግሥት ከዚህ በፊት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ከሚያስፈትኗቸው ተመራቂዎች ውስጥ 75 በመቶና ከዚያ በላይ ባላሳለፉት ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ከገለጸ በኋላ፣ እስካሁን ምን የተወሰደ ዕርምጃ አለ? ተብሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ይህ መመርያ ከተላለፈ በኋላ ራሳቸው ላይ ዕርምጃ የወሰዱ ተቋማት አሉ፡፡ በተለይ ከግሎቹ 90 ያህል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተዘግተዋል፡፡ አብዛኞቹ መመርያውን ካዩ በኋላ ራሳቸውም እየዘጉ ናቸው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እስካሁን የተዘጋ ባይኖርም ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተቋማት እንዳሉም ሚኒስትር ደኤታው ተናግረዋል፡፡ ተዘግተዋል የተባሉት የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲያስተምሩ የነበሩ ቢሆኑም ስማቸው አልተጠቀሰም፡፡
‹‹የእኛ ሥራ ሄዶ መዝጋት ሳይሆን ተቋማቱ ያሉበትን ሁኔታ መግለጽና መማር ለሚፈልጉ ዜጎች ለውሳኔ እንዲረዳቸው ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፤›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የወጡ መመርያዎችን በማየት ብቻ በራሳቸው ከገበያ የወጡ ተቋማት መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ መመረቂያና ጥናታዊ ጽሑፎች ከዚህ በፊት የተሠሩና ከሌሎች የተቀዱ ናቸው የሚሉ ሪፖርቶች እየጨመሩ በመሆናቸው፣ ይህንን ለማስቆም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን እንዲመልሱም ለሚኒስትር ደኤታው ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ ‹‹የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተግበሪያዎችን ጨምሮ ሐሰተኛ የመመረቂያ ጽሑፎችንና ጥናቶችን ለመከላከል፣ ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙና ምርምሮችን ችግር ፈቺ እንዲሆኑ፣ በተቀናጀ መንገድ እንዲሠሩ እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የሚታተሙ ጥናቶች ከእጥፍ በላይ እንደጨመረ የገለጹት አቶ ኮራ፣ አብዛኞቹ ከመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ወንደሰን ታምራት (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚል በወሰዳቸው ዕርምጃዎች ምክንያት የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎች መጎዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ አገር ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር ቅበላ ጉዳቱ በሁሉም ላይ ቢሆንም፣ የግል ተቋማት እንደ መንግሥት አቻ ተቋማት የበጀት ድጎማ ስለማያገኙ ጉዳቱ የበለጠ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ከዚህ በፊት ይቀበላቸው ከነበሩ ተማሪዎች ጋር የሚመጣጠኑ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቅበላ ማነስ ብዙ ተቋማት እንዲዘጉ አድርጓል ብለዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስደው ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት ያልቻሉ፣ ነገር ግን የዳግም ወይም ሬሚዲያል ፕሮግራም በመኖሩ ጉዳቱ የተወሰነ መቀነሱንም ፕሬዚዳንቱ አውስተዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ የግል የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉንም አካላት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ወንደሰን (ዶ/ር) አክለዋል፡፡
መንግሥት ዘርፉ ላለፉት 25 ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ በ100 ሺሕ የሚቆጠሩ ሠልጣኞችን ያፈራ፣ በአገር ደረጃ የነበረውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ችግር ሲፈታ የቆየ መሆኑን ተረድቶ፣ ለግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የግል ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለማቆየትና ከገበያ ላለመውጣት ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ ፖሊሲ መከተል ይጠበቃል ብለዋል፡፡