የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ዕገታ የሚስፋፋው በሚዲያው ምክንያት ነው ብሏል በተለያዩ ሥፍራዎች እየተፈጸሙ ያሉ ዕገታዎችና ግድያዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ አሽከርካሪዎችና የታጋቾች ቤተሰቦች ጥያቄ አቀረቡ፡፡ መጋቢት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ ልዩ ስሙ ‹‹አሊዶሮ›› በተባለ አካባቢ ታጣቂዎች ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል ሲጓዝ በነበረ ‹‹ፈለገ ግዮን›› የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ፣ አብዛኞቹ ተሳፋሪዎች ታፍነው ከተወሰዱበት ዕገታ፣ አንድ ሚሊዮን ብር ከፍለው ስለተመለሱ አክስታቸው ለሪፖርተር የተናገሩ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደጀን ከተማ ነዋሪ፣ ዕገታ ዜጎችን እያማረረ ነው ብለዋል። አስተያየት ሰጪው ታጣቂዎቹ አክስታቸው እንዲለቀቁ 1.5 ሚሊየን ብር ጠይቀው እንደነበር ተናግረዋል፡፡   ዕገታው መፈጸሙን የሚገልጽ የድጋፈ ደብዳቤ ከደጀን ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት አጽፈው  ገንዘብ በማሰባሰብ አንድ ሚሊየን ብር አዘጋጅተው ለታጣቂዎች በባንክ አስገብተው አክስታቸው ከታገቱ ሁለት ሳምንት በኋላ እንደተለቀቁላቸው ገልጸዋል። በተመሳሳይ ሁለት ወንድሞቹ የታገቱበት የክልሉ ነዋሪ እስካሁን እንዳልተለቀቁ ተናግሯል። ታጣቂዎች ለወንድማማቾቹ ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ መጠየቃቸውን የገለጸው አስተያየት ሰጪው፣ እስካሁን 450,000 ብር ተሰብስቦ ለታጣቂዎቹ እንዲደርስ ቢደረግም፣ ቀሪውን ክፍያ ካልከፈሉ እንደማይለቀቁ ተነግሯቸው እንደገና እየሰበሰቡና ሁኔታውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ አስረድቷል። ሆኖም የኑሮ ሁኔታው አስቸጋሪ መሆንና የታጋቾች መብዛት ገንዘብ ለመሰብሰብ መሰላቸት እንደፈጠረ አክሏል። ‹‹አሁን  ማንም ሰው ምን ማድረግ ይችላል? የዕገታ ሁኔታ  አስቸጋሪ ሆኗል፤›› ብሏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በአሽከርካሪዎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግድያ መቀጠሉን አሸከርካሪዎችም ገልጸዋል። የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ፣ ‹‹የሚያሠጉ ቦታዎች በምንላቸው በተለይ በኦሮሚያ ክልል የወለንጭቲ መስመር እኛም ክትትል ስናደርግ በፀጥታ አካላት በፓትሮል ሲጠበቅ ዓይተናል፡፡ ነገር ግን በሆነ ቅጽበት ችግሩ እየተፈጠረ ነው፤›› ብለዋል። ለአብነት በቅርቡ ወለንጪቲ ማደያ ላይ አንድ አሽከርካሪ በታጣቂዎቸ መገደቡን ጠቅሰዋል። ‹‹በተመሳሳይ በቅርቡ ከሱሉልታ ወደ ፍቼ በሚወስደው መስመር ሁለት አሽከርካሪዎች ታግተውብናል፤›› ሲሉም አክለዋል። ሆኖም ከ2015 ዓ.ም በፊት ይፈጸም ከነበረው ዕገታና ግድያ አንፃር አሁን ድርጊቱ በመጠን እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል። ለአብነት ያህል መሳቀቅ ይበዛባቸው በነበሩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ድርጊቶች ቀንሰዋል ብሎ ማኅበሩ እንደሚያምን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል። ድርጊቱ መቀነሱን ገምግማችኋል ወይ? ባለፉት ሁለት ዓመታት እየቀነሰ መጥቷል ስትሉስ በምን ዓይነት ንፅፅር ላይ ተመሥርታችሁ ነው? ተብለው የተጠየቁት አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ከ2015 ዓ.ም. በፊት በቀን 20 እና 30 የሚደርሱ አሽከርካሪዎች ይታገቱ ነበር፣ አሁን ግን ድርጊቱ እየቆየ እንደሚፈጸም እያየን ነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ የተረጋገጠ ከ120 በላይ የሚሆኑ አሽከርካሪዎች ተገድለዋል፡፡ ከሁሉም አካባቢዎች የተረጋገጠ መረጃ ስለማይመጣልን እንጂ፣ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ የሚልበት ዕድል አለ፤›› ብለዋል፡፡ የጣና አሸከርካሪዎች ማኅበር በበኩሉ ድርጊቱ እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ ነው ይላል፡፡ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ሰጡ ብርሃን እንዳሉት፣ ድርጊቱ ቀነሰ የሚባል ሳይሆን እየጨመረ ነው፡፡ በተለይ ዕገታ እየተለመደና ጭካኔዎች እየበዙ ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ለ24 ሰዓት በነፃነት እንጓዝ ነበር፣ አሁን ግን እንቅስቃሴያችን  የተገደበ ሆኗል፡፡ አሽከርካሪ እንደ ቢሮ ሠራተኛ ጠዋት ወጥቶ አመሻሽ ከ11፡00 ሰዓት በኋላ እንዳይቀሳቀስ እየተገደበ ነው፡፡ የትራንስፖርት ዘርፉ ግን በዚህ ሁኔታ መሥራት አይችልም፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የራሱ የሆነ ተዕፅኖም ይኖረዋል፤›› ሲሉ አቶ ሰጡ ገልጸዋል። የችግሩን ጥልቀትና አሳሳቢነት በተመለከተ ለፌዴራል፣ ለአማራ፣ ለኦሮሚያና ለአፋር ክልሎች ደብዳቤ ማስገባታቸውንንና መነጋገራቸውን የጠቀሱት አቶ ሰጡ፣ ዘላቂ መፍትሔ ግን አለመገኘቱን አስረድተዋል፡፡ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር በበኩሉ፣ ‹‹የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ክልልና የፀጥታ አካላትን ስንጠይቅ ምላሽ ይሰጡናል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ያለው የከተማ አስተዳደሮች ላይ ነው፡፡ ከቀናት በፊትም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በድጋሚ ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ስለሆነ በክልሉ ድንገተኛ ክስተቶች ይፈጠራሉ፡፡ ይኼ ነው ብለን ሐሳብ የማንሰጥበት ችግር ነው ያለው፤›› ብሏል፡፡ ከቀናት በፊት ደብዳቤ በድጋሚ ማስገባታቸውንም አክለዋል። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይ ዋና ዋና መንገዶችን ተከትሎ በትራንስፖርት ተጠቃሚ ዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የዕገታና ግድያ ድርጊቶች ቁጥጥርን በተመለከተ እየተሠራ ስላለው ሥራ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ዕገታ የተለመደ ወቅታዊ ድርጊት (ፋሽን) እየሆነ መጥቷል፡፡ ለኅብረተሰቡ እንግዳ ነበር፣ አሁን ግን ሚዲያው እያስፋፋው ይገኛል፣ ስለዚህ በልኩ ነው መገለጽ ያለበት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ዕገታ እዚህ ቦታ ላይ ተፈጸመ፣ ተፈጠረ ማለት አይጠቅምም፤›› ያሉት ኃላፊው፣ በአጋቾች ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ ተወሰደ የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት፡፡ ዕርምጃ ሲኖር ‹‹ለሕዝብ እናሳውቃለን›› በማለት አስረድተዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የመከላከያ ሚኒስቴር ምን እየሠራ እንዳለ በስልክ መረጃ እንዲሰጡን  ሪፖርተር የጠየቃቸው የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እንዲህ ዓይነት መረጃ በስልክ የሚሰጥ አለመሆኑን በመግለጽ መረጃ ከመስጠት  ተቆጥበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር ሚዛኔ አባተ (ዶ/ር)፣ በአጠቃላይ እየተፈጸሙ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ሪፖርቶች እየወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። በዚህም በቅርብ ጊዜያት የተፈጠሩ ክስተቶችን አስመልክቶ በደረሳቸው ጥቆማ መሠረት፣ ኮሚሽኑ ክትትልና ምርመራ እያደረገ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ክትትሉ ሲያልቅ ምላሽ እንደሚሰጥ ለሪፖርተር ገልጸዋል። በሌላ በኩል የኬላ ክፍያ ይጠይቅባቸዋል በሚባሉ በተወሰኑ ሥፍራዎች ድርጊቱ መቆሙን፣ ነገር ግን አሁንም የሚያስከፍሉ ስላሉ ችግሩን ለመፍታት ተጨማሪ ሥራ እንደሚጠይቅ አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡   አቶ ሰጡ በበኩላቸው አሸርካሪዎች አሁንም እየከፈሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ለአብነት  በቅርቡ በቤኒሽንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ አሸከርካሪዎች ሲደርሱ ከ10,000 እስከ 30,000 ብር ለአሶሳ ከተማ ኮሪደር ልማት ድጋፍ በሚል ደረሰኝ እየተቆረጠላቸው እንዲከፍሉ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ክፍያውን ያልከፈለ እንደማያልፍና ለእስር እንደሚዳረግ ገልጸዋል። በአዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ለሆስፒታል ማሠሪያ በሚል አንድ ሺሕ ብር ክፍያ እንዲፈጸሙ እየተደረገ እንደሆነ አክለዋል።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አመለወርቅ ህዝቅኤል በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ በተለይ አሽከርካሪዎች የሚጠየቁት የኮቴ ክፍያ ሕጋዊ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ከክልሎች ጋር እየተደረገ ባለው ቅንጅታዊ ሥራና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *