ከሁለት ሚሊዮን ተፈናቃዮች በዘጠኝ ወራት የተመለሱት 380 ሺሕ ናቸው ተብሏል ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ወደ ቀድሞ ሕይወታቸውና መኖሪያቸው እንዳይመለሱ፣ የፖለቲካ ማስያዣና የኢኮኖሚ መጠቀሚያ ተደርገዋል ሲል የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የሚኒስቴሩ የሥራ ኃላፊዎች ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ዓ.ም. የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርቡ ነው ይህንን የተናገሩት፡፡ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ የፈረሰባቸውን ቤት ገንብቶ ወይም ትራንስፖርት አመቻችቶ ማጓጓዝ ቢሆን ኖሮ ያን ያህል እንደማያስቸግር፣ ነገር ግን እነሱን መያዣ አድርጎ የመጫወት ፖለቲካ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ለአብነት በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላ፣ በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን የመመለስ እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ተፈናቃዮችን የፖለቲካ አጀንዳና መያዣ ማድረግ የሚፈልግ አካል፣ መፈናቀላቸውን በደል አድርጎ ቢያቀርብም፣ ተስማምተው በቀዬአቸው መኖራቸውን ግን አይፈልግም ብለዋል፡፡ መንግሥት ቁርጠኝነት እንዳለውና ተፈናቃዮችም የመመለስ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ቢሆንም፣ ሒደቱን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ፖለቲከኞች መኖራቸው ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በራያ አካባቢ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራን ለማደናቀፍ ከሕወሓት አካባቢ የተደረገውን ጥረት ስንመለከተው አጀንዳውን ለፖለቲካ የመጠቀም ፍላጎት እንደሆነ እናያለን፤›› ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ የሚባሉ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው በመመለስ በነበሩበት አካባቢ አልምተው ባፈሩት ሀብት ጥቅማቸውን አስጠብቆ መሄድ የዜግነት ጉዳይ ነው ያሉት አቶ መሐመድ፣ መንግሥት በዚህ ላይ ግልጽ አቋም እንዳለውና ማኅበረሰቡም ችግር እንዳሉበት ጠቁመዋል፡፡ የሰላም ሚኒስትር ደኤታው አቶ ቸሩጌታ ገነነ፣ ተፈናቃዮችን መመለስ ከሰብዓዊ አጀንዳነት የወጣና ፖለቲካዊ መሆኑ ሥራውን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አሁን አሁን በተፈናቃዮች ላይ ፖለቲካ የሚሠራ ኃይል አለ፡፡ በተፈናቃዮች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያገኝ ኃይል አለ፡፡ ይህ ኃይል ደግሞ ተፈናቃዮችን መመለስ አስቸጋሪ አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚሠሩ ኃይሎች፣ ተፈናቃዮች ወደ ሰላማዊ አካባቢ እንዳይመለሱ ፍርኃት እንዲያድርባቸው ያደርጋሉ ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች ቢኖሩም በተያዘው ዓመት ብቻ 380 ሺሕ ተፈናቃዮች መመለሳቸውንና በሚቀጥሉት ዓመታት የተፈናቃዮችን ቁጥር ዜሮ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሁለት ሚሊዮን ያህል ተፈናቃዮች መኖራቸውን የቋሚ ኮሚቴው መረጃ ያሳያል፡፡ ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ በኢትዮጵያ 51 የሃይማኖት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች መኖራቸውንና ቁጥራቸው ከንግዱ ሚዲያ የላቀ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹የሃይማኖት ተቋማት በአገራዊ የሰላም ግንባታና ከግጭት ውስጥ ለመውጣት እንደ አንድ መሣሪያ የመጠቀም ፍላጎት አለን፤›› ብለዋል፡፡ ለአገረ መንግሥትና ለብሔረ መንግሥት ግንባታ ምክክርና የንግግር ባህል ኢትዮጵያን ያበረቷት እሴቶች ቢሆኑም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን በሚሰብኩ ልዩነትን በንግግር ከመፍታት ይልቅ አጥፊ በሆነ ለአገርም ለትውልድም በማይጠቅም መንገድ ግጭትን እንደ ልዩነት መፍቻ አድርገው በሚፈልጉ የፖለቲካ አካላት ምክንያት በአገር ውስጥ በውጭም ያሉ ፈተናዎች ለአገሪቱ ጉዳት እያስከተሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰበሳቢ ፈቲ መሐዲ (ዶ/ር) በሰጡት አስተያየት፣ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ ካለው የተፈናቃይ ቁጥር አንፃር፣ ዜጎች በተቻለ ፍጥነት ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል፡፡ አክለውም ዜጎች ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱና ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ድጋፎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ተፈናቃዮችን ለፖለቲካ አጀንዳና ኢኮኖሚ ፍጆታ መጠቀም የሚፈልጉ አካላትን መታገልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *