የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንገብጋቢ ለተባሉ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ሊሰጣቸው ባለመቻሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ
(ዶ/ር) በድጋሚ እንዲያነጋግሯቸው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጠየቀ፡፡ ከሠራተኛው ደመወዝ በቀጥታ
ተቆርጦ ለአደጋ ሥጋት መከላከል ገቢ ይደረግ በሚል የሚያስገድደው ረቂቅ አዋጅ ሠራተኛው ላይ ተፈጻሚ እንዳይሆን
ጥያቄ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ነገ የሚከበረውን የሜይዴይን በዓል
አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ በተከታታይ መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥባቸው የቀረቡ ዋና ዋና ጥያቄዎች እስካሁን
ምላሽ ባለማግኘታቸው ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ አወንታዊ ምላሽ
ይሰጥባቸዋል ተብሎ ቃል ተገብቶባቸው የነበሩ ጥያቄዎች እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሳናገኝባቸው የቀሩና የሠራተኛው አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው ካሉዋቸው ውስጥ በቀዳሚነት የጠቀሱት
የደመወዝ ግብር ምጣኔ አንዱ ሲሆን፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ይተግበር የሚለውም ምላሽ ካላገኙና ቁልፍ ጥያቄያቸው
እንደነበር አመልክተዋል፡፡
ጥያቄው መቅረብ ከጀመረ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ለነዚህና ለሌሎች ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ሳይሰጥ በመቆየቱ፣
የዘንድሮውን የሜይደይ በዓል ‹‹መንግሥት ላቀረብናቸው ጥያቄዎች አስቸኳይ ምላሽ ይስጠን›› በሚል መሪ ቃል ለማክበር
እንዳስገደዳቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዘንድሮውን ሜይዴይ በዓል ‹‹እንዲከበር የተመረጠው መሪ ቃል፣ በዋጋ ንረትና ካለበት በማይነቃነቅ ደመወዝ ከእጅ ወደ
አፍ በሆነ ኑሮ በልቶ ማደር እየቸገረው ያለውን የሠራተኛውን የዕለት ተዕለት እውነታ የሚያንፀባርቅ በመሆኑ ነው፤›› ያሉት
አቶ ካሳሁን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ያለው የኑሮ ሁኔታ አሁንም በጣም የሚያሳስብ መሆኑን
ገልጸዋል፡፡ የዋጋ ግሽበት የደመወዝ ተከፋዩን የመግዛት አቅም መሸርሸሩን እንደቀጠለ በመሆኑና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን
ሠራተኞች ለመጠበቅ የሚያስችል ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አሁንም አለመወሰኑ፣ የሠራተኞችን በልቶ የማደር አቅም
ተፈታትኗልም ብለዋል፡፡ ሠራተኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ ሆኖ እያለ ከፍተኛ የገቢ ግብር ስለሚቆረጥባቸው፣
መሠረታዊ ፍላጎታቸውን እንዳያሟሉ እስከማድረግ መድረሱን ስለመቀጠሉ በማውጣት መንግሥት እነዚህን ታሳቢ እያደረገ
አወንታዊ ምላሽ እንደሚጠቅበት አመልክተዋል፡፡ ከነዚህ ችግሮች ባሻገር አንዳንድ አሠሪዎች የማኅበር መሪዎች
ለአባሎቻቸው ስለቆሙ፣ ከሥራ እንደሚያባርሩና እንደሚያዋክቡ ወይም ራቅ ወዳለ ቦታ እንዲዘዋወሩ ማድረግም ሠራተኞች
እያጋጠሙዋቸው ካሉ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የኅብረት ስምምነት ለመደራደር ፈቃደኝነቱ ያለመኖር፣
ቢደራደሩም ስምምነቶቹ የማይከበሩበት ሁኔታ መኖሩንና የሠራተኞች ችግሮች እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ጭምር ይገለጻሉ
ብለዋል፡፡
የኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለራሱና ለቤተሰቡ ደኅንነት ጤንነት ደረጃውን የጠበቀ ጤናና
ፍትሐዊ ደመወዝ የማግኘት መብት እንዳለው ባረጋገጠው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ሠራተኞች ጥያቄ ብቻ ሳይሆን
ፍትሐዊነትና ክብርን እንደሚፈልጉ በጽኑ እንደሚያምንም አቶ ካሳሁን በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡
‹‹ከረዥም ዓመታት በፊት በወር 600 እና ከዚያ በታች ደመወዝ ተከፋይ የሆኑ ሠራተኞች፣ ከሥራ ግብር ነፃ የተደረገው
የጊዜው የገበያ ሁኔታ ግምት ውስጥ ገብቶ ነበር፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁንም ወቅታዊውን የገበያ ሁኔታ ያገናዘበ ሁኔታ ሊስተካከል ይገባ የነበረ ቢሆንም፣ ይህንን ለማድረግ እንኳን እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡
‹‹ቢያንስ በሕጎች ደረጃ የመደራጀት መብታችን ዕውቅና አግኝቷል›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ በሠራተኞች የሚነሱ ጥያቄዎች
የሚናቁበትና ምላሽ የሚነፈጉበት ዘመን ከማለፉም በላይ፣ ከከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ችግሮቻችንን በውይይትና
በድርድር የመፍታት አሠራር የተለመደበት ዘመን ላይ መዳረሱን ገልጸዋል፡፡
በውይይት በጽኑ የሚያምን የሠራተኛ መሪ ድርጅት የሆነው ኢሠማኮ ባለፉት ዓመታት የሠራተኛውን ጥያቄ ሰምቶ የውይይት
በር እንዲከፍት ሲሠራ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተለይ በ2015 ሜዴይ ሲከበር በአደባባይ ልናቀርባቸው የነበሩ የሠራተኛ ዋና
ዋና ጥያቄዎች መንግሥት የውይይት በር በመክፈቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር በተደረገው ውይይት
ጥያቄዎችን ተቀባይነት አግኝቶ ለሚመለከታቸው ሚኒስትሮች አቅጣጫ በመሰጠቱ ተስፋ ተደርጎ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ሆኖም የተወሰኑ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኙ ቢሆንም ቁልፍ የሆኑ የሠራተኛ ጥያቄዎች አልተመለሱም፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ያለውን ችግር የሚያመላክቱ ጉዳዮችን በመዘርዘር የአቋም መግለጫ ጭምር በማውጣት ጉዳዩን
ለሚመለከታቸው አካላት ጭምር የላኩ ቢሆንም ምላሽ ባለማግኘታቸው አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማነጋገር ማስፈለጉን
ጠቁመዋል፡፡
‹‹ለጥያቄዎቻቸው መልስ ባለመገኘቱ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካለባቸው የተጣበበ ጊዜ በመሸረፍ፣ ሌላውን ማኅበረሰብ
እንደሚያወያዩት ሁሉ መሠረታዊ ማኅበራት ተወካዋዮች በተገኙበት የኢትዮጵያ ሠራተኞችን ድምፅ ለመስማት ጊዜ
እንዲያመቻቹልን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፤›› በማለት በመገናኛ ብዙኃኑ በኩል ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
ኢሠማኮ ለዓመታት ሲጠይቃቸው የነበሩ ቁልፍ ናቸው የተባሉ ብዙዎቹ ጥያቄዎች መልስ ያለማግኘታቸው፣ መንግሥት
ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት ስለሌለው ነው ወይስ የእናንተ የመደራደር አቅም ማነስ ነው? ለሚለው ከሪፖርተር ቀረበ ጥያቄ
አቶ ካሳሁን በሰጡት ምላሽ ይህ የሆነው ከኢሠማኮ የመደራደር አቅም ማነስ አይደለም እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ
እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር ኢሠማኮ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፤›› ብለዋል፡፡
ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በፊት ኢሠማኮ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተወያየበት ወቅት ጥያቄዎቹ በመንግሥት በኩል
ትክክል አይደሉም ወይም አሁን ምላሽ አይሰጥባቸውም የተባሉ እንዳልሆኑም ገልጸዋል፡፡ እንዲያውም ጥያቄዎቹን
ተቀብለው ለሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን እንዲያዩት አቅጣጫ የተሰጣቸው መሆኑን አክለዋል፡፡
ይመለከታቸዋል ከተባሉ የመንግሥት አካላት ጋር በግንባር ጭምር በመሄድና በጽሑፍም በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት
ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ግን ምላሽ ሊገኝ አልቻለም፡፡ የተወሰኑ ጥያቄዎች ግን ምላሽ ማግኘታቸውን የጠቀሱት
አቶ ካሳሁን፣ ወሳኝ የሚባሉ ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ጥያቄያቸውን እንዲገፉበት አስገድዷቸዋል፡፡
ከጥያቄዎቹ መካከል የመደራጀት መብትን በተመለከተ በአዋጅ በተቀመጠው መሠረት ዕቅድ ወጥቶ እየተሠራበት ነው፡፡
በዚህም ረገድ ክፍተት ቢኖርም በመደራጀት ዙሪያ ባሉ ችግሮች ከሥራና ክሀሎት ሚኒስቴር ጋር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው
ነገር ግን ገና ጅምርና በተግባር መሬት ላይ ያልወረደ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
መነሻ የደመወዝ ወለልን ለመወሰን ቦርድ እንዲቋቋም ያስፈልጋልና ይህ እንዲሆን ለቀረበው ጥያቄም ሥራና ክህሎት
ሚኒስቴር ጥናት እያደረገ መሆኑንና ምላሽ የምሰጠውም በዚሁ ጥናት ላይ ተመሥርቼ ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቶ
እየተጠበቀ ስለመሆኑም በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል፡፡
የሥራ ግብርን የተመለከተም ጥያቀ እስካሁን የተጨበጠ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ሥራዎች በተወሰነ መልኩ
እየተሠሩ ነው፡፡ በተለያዩ ተቋማትም በኩል ግፊት እያደረግን በመሆኑ፣ የመደራደር አቅማችን በዚህ ሊለካ ይችላል፡፡ ምላሽ
ያገኘንባቸው ጥያቄዎችም የተገኙት ኢሠማኮ ገፍቶ ስለሄደ በመሆኑ፣ የመደራደር አቅም የለውም ሊባል አይችልም፡፡
አሁንም ትግላችንን በተለያየ ዘዴ እንቀጥላለን ያሉ አቶ ካሳሁን፣ የኢሠማኮ የመደራደር አቅሙ ከመሰል የአፍሪካ አገሮች ጋር
ሲነፃፀር የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ በየጊዜው አስፈላጊውን ሥልት እየቀየሱ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ
ስለመሆኑንም በማከል፣ ኢሠማኮ የመደራደር አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ሌላው ችግር ሆኖ እየታየ ያለው፣ ከአነስተኛ ደመወዝ ላይ ለተለያዩ ጉዳዮች እየተቆረጠ ያለው ገንዘብ
እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡ ሠራተኞች ለተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችና ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ከደመወዛቸው በቀጥታ
የሚቆረጠው ገንዘብ ከሚያገኙትን ገቢ እያሳነሰው በመሆኑ፣ እንዲህ ያሉ አሠራሮች እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡ በተለይ የአደጋ
ሥጋት መከላከል ረቂቅ አዋጅ ሠራተኞችን ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጡ የሚያስገድድ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ
ኢሠማኮ አቋም እንደሚወስድ አመላክተዋል፡፡
የአደጋ ሥጋትን ለመከላከል በሚል የወጣው አዋጅ አስፈላጊነት ላይ የሚስማሙና ትክክልና ወቅታዊ ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፣
አዋጁ በመርሕ ደረጃ የሚደገፍም ነው ይላሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ አገሮች ዕርዳታዎቻቸው እየቆሙ መሆኑንም
ገልጸዋል፡፡ እንደ ዩኤስኤአይዲ ያሉ ተቋማት እንዳልወሰዱት ዓይነት ዕርምጃ ሌሎች የአውሮፓ አገሮችም ይህንን
እየተከታተሉ ነው፡፡ ስለዚህ አገሮች ራሳቸውን ካልደገፉ የውጭ ዕርዳታ አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ የአደጋ ሥጋት መከላከል
አዋጅ መቀረፁ ለአገር ይጠቅማል፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህ ተቋም የሚያስፈልገውን ሀብት ለማሰባሰብ በቀጥታ ከሠራተኞች
ገቢ ላይ ተቆርጦ እንዲከፈል የሚፈለገው መዋጮ፣ አሁን ላይ ቢተገበር ተፅዕኖው ከፍተኛ በመሆኑ፣ በተፋጠነ ሁኔታ
ሊተገበር እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡
ከሠራተኛው ደመወዝ በቀጥታ እንዲቆረጥና እንዲከፈል የሚያደርግ ውሳኔ የወቅቱን ሁኔታ ማገናዘብ ይኖርበታልም
ብለዋል፡፡
ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ አሁን ባለው የኑሮ ውድነትና ከሠራተኛው ወቅታዊ አቅም አንፃር፣ ከሠራተኛው ገቢ ላይ ሌላ
አዲስ ወጪ ማከሉ ተገቢ ባለመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ የሠራተኛው የኑሮ ሁኔታ እየታየ መሆን እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡
ወደፊት ከሠራተኛው የሚቆጠረው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ እንጂ፣ አሁን ይጀመር ቢባል ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር
የሠራተኛውን ኑሮ ያከብደዋልና ለጊዜው የዚህ የአዋጅ ተፈጻሚነት እንዲዘገይና ከሠራተኛው ደመወዝ እንዳይቆረጥ ጥያቄ
እያቀረቡ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በዚህ አዋጅ ላይ ያላቸውን አቋምም አዋጁን በተመለከተ በሚደረገው ውይይት ላይ እንደሚንፀባረቁ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከስምንት መቶ ብር ጀምሮ ደመወዝ የሚከፈለው በተለይ በብዙዎቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና
ከፓርኮች ውጭ በማኑፋክቸሪንግ ውስጥ በአማካይ የሚከፈላቸው ከ1,000 እስከ 2,500 ብር ነው፡፡ ከዚህም ደመወዝ ላይ
ታክስ ይደረጋል፡፡ ሕጉ ከ600 ብር በላይ ግብር የሚከፈል በመሆኑ ይከፍላሉ፡፡ በዚህም ደመወዝ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር
አይቻልም፡፡ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ይኑር የሚባልበት ምክንያት ይኽ ነው፡፡ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚጠየቀው ደግሞ
ለሠራተኛው ብቻ ታስቦ ሳይሆን ለምርታማነት መጨመር አስተዋጽኦ ስላለው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ሰው ጥሩ ሊሠራ የሚችለው በልቶ ሲያድር ነው፡፡ በልቶ ካላደረ ምርታማነት ሊጠበቅ አይችልምና ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል
ላይ አስቸኳይ ምላሽ ያስፈልጋል፤›› በማለት፣ የዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አስፈላጊነትን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር
በተያያዘ ኢሠማኮ ጥናት እያደረገ ሲሆን፣ ዋናው ነገር ግን ቦርዱ ተቋቁም ወደ ሥራ መግባት አለበት፡፡ ዝቅተኛ የወለል
ምጣኔውም ጥናት ላይ መሠረት አድርጎ እንዲተገበር አሁንም ግፊት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አቶ ካሳሁን
አመልክተዋል፡፡