አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ እና ድጋፍ ሊቀርብ ይገባል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ፣ በቦታው ያሉ የሲቪል ሰዎች ደኅንነት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቦታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች በአሳሳቢና ወደ ሰብአዊ ቀውስ ሊያመራ በሚችል ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገለጸ። ኮሚሽኑ ከታኅሣሥ 6 እስከ ታኅሣሥ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በጎንደር እና በዳንሻ በመገኘት እንዲሁም፣ ከታኅሣሥ 22 እስከ ታኅሣሥ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በትግራይ ክልል፣ ደቡባዊ ዞን፣ ጨርጨር ወረዳ በሚገኙት ኡላጋ እና ቢሶበር መንደሮች በመጓዝ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም ተጎጂዎችና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ያደረገውን ክትትል ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

በተጨማሪም የኮሚሽኑ ባለሞያዎች ከጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተጨማሪ ዙር የመስክ ምልከታ ወደ መቀሌ ከተማ እና ሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች በመንቀሳቀስ፣ በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን የሰብአዊ ቀውስ እና የሰብአዊ መብት ጉዳዮች በመመርመር ላይ የሚገኝ ሲሆን ስራው እንደተጠናቀቀ ተጨማሪ ሪፖርቱን ይፋ የሚደረግ መሆኑን ኮሚሽኑ አክሎ አሳውቋል።

የአሁኑ ክትትል በዋነኛነት በተካሄደባቸው በዳንሻ፣ በሁመራ፣ በቢሶበር እና በኡላጋ ጦርነቱ የሲቪል ሰዎችን ሞትና አካላዊ ጉዳት አስከትሏል፣ የሲቪል ሰዎችን መኖሪያና የንግድ ቦታዎች ለዝርፊያና ለተለያዩ ጉዳቶች አጋልጧል እንዲሁም በመሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመትና የኤሌክትሪክ እና የውሃ የመሳሰሉ አገልግሎቶች አለመመለስ፣ በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች እና በተፈናቃናዮች ላይ የበለጠ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያስከትል የሚያሰጋ ነው። በቢሶበር እና በኡላጋ 31 ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፣ 104 መኖሪያ ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል እንዲሁም የአካባቢው ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በሁመራ እና በዳንሻ የሲቪል ሰዎች ንብረት የሆኑ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶችን ጨምሮ የአካባቢው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ውድመት እና ዝርፊያ ደርሷል። ሲቪል ሰዎች በብሔራቸው ምክንያት ወይም በአካባቢዎቹ የፀጥታ መጓደል ምክንያት ለደኅንነታቸው እንደሚሰጉ ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። በአጠቃላይ በነዚህ አራት ከተሞች ያለው የፀጥታ ስጋትና የፍትሕ አካላት ወደ መደበኛ ስራቸው አለመመለስ፣ የሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅና የሰብአዊ መብቶቻቸውን ጥበቃ ለማረጋገጥ አዳጋች አድርጎታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሲያስረዱ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ምርመራውና ክትትሉ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ፣ የነዋሪዎቹንም ሆነ ከትግራይ ክልል ወደ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን ሰብአዊ እርዳታ ፍላጎት እንዲጨምርና የመቋቋም አቅማቸውን በአስከፊ ሁኔታ እንዲፈተን አድርጓል” ብለዋል። የኮሚሽኑ ምርመራ ቡድን የጎበኟቸው ተጎጂዎች በአብዛኛው በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው አልያም አንድ ዙር ብቻ እርዳታ የተደረገላቸው መሆኑን በሪፖርቱ እንደተመለከተ ጠቅሰው፣ “በአካባቢዎቹና በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰው ጉዳት የሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት ከፍተኛና አፋጣኝ ርብርብ የሚጠይቅ ነው” በማለት ገልጸዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *