selegna

Byselegna

Jan 22, 2021

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በረቂቅ የመገናኛ ብዙኃን አዋጁ ውስጥ በሚዲያዎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን የመፍታት ኃላፊነት፣ እንደ አዲስ ለሚቋቋመው ‹‹የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን›› መሰጠቱ አግባብ አይደለም አለ፡፡

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 73 ላይ ደንቦችና መመርያዎችን ተላልፈው የተገኙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ለባለሥልጣኑ ተሰጥቷል፡፡

ይሁን እንጂ በቅርቡ የተቋቋመው የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በሚዲያ ተቋማት ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን የመፍታት ኃላፊነት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ የተመሠረተበት አንዱ ዓላማውም ይኸው መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሰኞ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በረቂቅ አዋጁ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች፣ የሚዲያ ባለቤቶችና አደረጃጀቶች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ተወካዮች ‹‹በየትኛውም አገር እንዳለው ሁሉ፣ ሚዲያዎች እርስ በርስ እንዲገማገሙ የሚያስችል ተቋም ያቋቁማሉ እንጂ መንግሥት ተቆጣጣሪና ውሳኔ ሰጪ መሆን የለበትም›› ብለዋል፡፡

ወደ 50 የሚጠጉ የሚዲያ ተቋማትን ያቀፈው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከተለያዩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን ጠቁሞ፣ በአሁኑ ጊዜ ‹‹ባለሥልጣኑ የራሱን ሕግ አውጥቶ ይግባኝ ይሰማል›› ተብሎ የተቀመጠው አካሄድ ‹‹እንደገና ሊታይ ይገባል›› በማለት ጠይቋል፡

ምክር ቤቱ ራሱን የቻለ ዳኝነት የሚሰጥና ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ግለሰቦችን የያዘ አካል መቋቋሙን የጠቀሱት የምክር ቤቱ አባላት፣ ኃላፊነቱ ለምክር ቤቱ ተሰጠ ማለት ሁሉም ነገር በዚህ መንገድ ያልቃል ማለት እንዳልሆነና ለመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ ጉዳዩን አላቀርብም ወይም የተሰጠውን ውሳኔ አልቀበልም የሚል ካለ ወደ ፍርድ ቤት የመሄድ ዕድሉ የተከበረ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ ፈቃዱን አውጥቶ ሥራውን ለመጀመር ዕርምጃ በጀመረበት ጊዜ፣ ‹‹እኔ ልቆጣጠር እኔ ሕግ ላውጣ›› የሚል አካል መምጣቱ ተገቢ ባለመሆኑ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ጊዜ ተሰጥቶት መወያየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

አባላቱ ስለጉዳዩ ሲናገሩ ከዚህ በፊት በብሮድካስት ሚዲያዎች ላይ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ሲቆጣጠር እንደነበር ጠቁመው፣ ይህም የሆነበት ምክንያት በሥራ ላይ ያለ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት እንዳልነበረና አሁን ግን ምክር ቤቱ ተቋቁሞ እያለ ለሚቋቋመው ባለሥልጣን መስጠት ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ ራስን በራስ ማረም የሚያስችል አቅምና ሥርዓት እየገነባ እንደሆነና የራሱ የሆነ መተዳደሪያ አውጥቶ ከመንግሥት ጋር ፍርድ ቤት ከመጓተት፣ ራስን በማረም ኃላፊነት የሚሰማው ሚዲያ መፍጠር ዓላማ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱ እስካሁን በነበረው አሠራር ቅሬታ እንደሌለው፣ ወደፊት ግን ጋዜጠኞችን በተመለከተ የሥነ ምግባር ደንብ እንዲያወጣና ቅሬታ አፈታቱንም ለምክር ቤቱ መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፣ ባለሥልጣኑ ሊያወጣቸው የሚችሉ የሥነ ምግባር ደንቦች ለብቻው ሳይሆን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን እንደሚያዋጣቸው፣ ለባለሥልጣኑ የተሰጡ ኃላፊነቶችም ለሽግግር ጊዜ የተሰጡ እንደሆኑና ቀስ በቀስ የተቋማቱ ቁመና እየታየና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን እየገመገመ ሕዝብም እምነት እየጣለባቸው መሆኑን ሲረዳ፣ የራሱን ሥልጣን ቆርሶ አሳልፎ መስጠት የሚችልበትን መንገድ አዋጁ ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አሁን የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት እየጠየቀው ያለውን ጉዳይ ከሦስት ዓመት በኋላ እያየ ኃላፊነቱ የእርስ በርስ ቁጥጥር አደረጃጀት በአማራጭነት እንዲወስኑ በማድረግ፣ የባለሥልጣኑ ቦርድ ውሳኔዎችን በይግባኝ የመመልከቱ ሥልጣን ሊኖረው እንደሚቻል ተገልጿል፡፡

ጌዲዮን (ዶ/ር) አክለውም ምክር ቤቱ የበለጠ እየተጠናከረ እስኪሄድና እስኪታይ ድረስ መታየት ስላለባቸውና ከመገናኛ ብዙኃን ጥቅም ብቻ ሳይሆን፣ በሌላ ጎኑ የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎትንም ማመዛዘንና ከግምት ውስጥ ማስገባት ስላለበት ሚዛናዊ ይሆናል ተብሎ የታሰበው አካሄድ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አክለውም ባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ የሚቋቋምና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ይህ ተቋምና አንድን በሲቪል ማኅበረሰብ የተቋቋመ ድርጅት አቻ ወይም እኩል ናቸው ብዬ አላስብም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እንዳለመታደል ሆኖ እነዚህ ተቋማት ከዚህ በፊት ተቋቁመው በሚገባ አላየናቸውም፡፡ ወደፊት ተጠናክረው ኃላፊነቱን ይወጡታል የሚል ተስፋ አለን፤›› በማለት የገለጹት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ፣ ‹‹ነገር ግን አሁን በተግባር ታይቶ ቁርጥ አድርጎ የእርስ በርስ ቁጥጥር አደረጃጀቶች ይሥሩት ብሎ ለመደምደምና ለመተማመን የሚያስችል ሁኔታ ላይ አይደለንም፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም መካከለኛ አማራጩ አሁን ለዚህ ዴሞክራሲያዊ ተቋም እንዲሰጥ፣ ከዚህ በኋላ የእነዚህን ተቋማት ውጤታማነትና ጥንካሬ እየታየ ተላልፎ እንዲሰጥ በሚል የሦስት ዓመት ገደብ መቀመጡን አመላክተዋል፡፡

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ረቂቅ አዋጁ ለረዥም ዓመታት በውይይት የዳበረ በመሆኑ፣ከየትኛውም አዋጅ በላይ ጊዜ የፈጀ ስለሆነ ፓርላማው ወደ ዕረፍት ከመውጣቱ በፊት ተመልክቶ ሊያፀድቀው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *