የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ በፍጥነት አለመፅደቅ ጥቃቶች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል ሲል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ ይህንን የገለጸው፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት መብቶች አያያዝን በተመለከተ በ2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ይፋ ባደረገው የክትትል ሪፖርት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች አተገባበር ላይ ባከናወነው ምልከታ፣ የተለዩ ግኝቶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መጋቢት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት ባካሄደበት ወቅት መሆኑን፣ የሰብዓዊ መብት ተቋሙ ሐሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ያወጣው የክትትል ግኝት መረጃ ያሳያል። የኢሰመኮ የሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረ ሐዋርያ፣ አብዛኛው የጥቃት ወንጀሎች ሪፖርት እንደማይደረጉ ጠቁመው፣ ፍትሕ ፍለጋ ሪፖርት ያደረጉ ውስን የጥቃት ተጎጂዎች በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ የሕግና የአሠራር ክፍተቶች የተነሳ ለተጨማሪ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋልጠዋል ብለዋል። ‹‹ተጎጂዎች የደረሰባቸውን ጥቃት እንዳያመለክቱ፣ እንዲሁም የጥቃት ወንጀሎች እንዲስፋፉ ምክንያት ሆኗል፤›› ሲሉ ኮሚሽነሯ አስረድተዋል። በውይይቱ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት ከአቤቱታ አቀራረብ ጀምሮ በምርመራ ሒደት፣ በክስ አቀራረብ፣ እንዲሁም በችሎት ሒደት በዓለም አቀፍ፣ በአኅጉራዊና በአገራዊ ሕጎች የተጠበቁላቸው መብቶች፣ ተግባራዊ ያልተደረጉ ምክረ ሐሳቦችና በመጀመሪያው የክትትል ሥራ የተለዩና የቀጠሉ አሳሳቢ ጉዳዮች ምክክር እንደተደረገባቸው ተነግሯል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ረቂቅ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ ሳይፀድቅ መዘግየት፣ በጥቃት ተጎጂዎች መብቶች አያያዝ ላይ እክል መፍጠሩን ገልጸዋል። የወንጀል ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ረቂቅ ሕግ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ስለሚኖራቸው የተለየ የመብት አያያዝ እንደሚደነግግ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ የምክረ ሐሳብ አተገባበር ክትትል እስከተከናወነበት ጊዜ ድረስ ረቂቅ ሕጉ ሳይፀድቅ ነባሩ አሠራር መቀጠሉን ተገልጿል። የዓቃቤ ሕግና የፖሊስ የሥራ ክፍሎች የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አለመጀመራቸው፣ በሥራ ላይ ያሉት የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋማት በአሠራር መመርያ መሠረት አለመሥራታቸውና የመጠለያ ተቋማት አለመስፋፋታቸው፣ ከታኀሳስ 16 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም.፣ እንዲሁም ከየካቲት 2 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በተካሄዱ ክትትሎች በተለዩ አፈጻጸሞች በአሳሳቢነት የተለዩ ግኝቶች መሆናቸው ተጠቁሟል። በመጀመሪያው ክትትል የተጎጂዎች ፍትሕ የማግኘት መብት፣ የፍትሕና የድጋፍ ሰጪ ተቋማት ኢኮኖሚያዊ ተደራሽነት (Economic Accessibility)፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆን፣ የቋንቋና የመረጃ ተደራሽነት፣ ክብርን በጠበቀና ለዳግም ጥቃት በማያጋልጥ መንገድ የመስተናገድ፣ ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ የፍትሕ አገልግሎት፣ የደኅንነት ጥበቃ፣ የመሰማት ወይም የመሳተፍ፣ የተፋጠነ ፍትሕና ውጤታማ የድጋፍ አገልግሎት የማግኘት መብቶቻቸው በተሟላ ሁኔታ የማይተገበሩ መሆናቸው ከተለዩ ግኝቶች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸው ተመላክቷል።

የጤና ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በሴቶችና በሕፃናት መብቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ክልሎችና ሌሎች አቻ ተቋማት በተሳተፉበት ውይይት ላይ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት መብቶች አያያዝን ለማሻሻል፣ ሁሉም የፍትሕ አካላትና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *