‹‹ የተላለፈ ክልከላ የለም ›› ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር– ኤጀንሲዎች 200 ሺሕ ዶላር ዋስትና ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል የውጭ አገር ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀርብ በተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ ላይ ቅሬታ አቀረቡ። ሚኒስቴሩ በበኩሉ ‹‹የተላለፈ ክልከላ የለም›› ሲል የቀረበውን ቅሬታ አስተባብሏል። ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ካቀረቡ ኤጀንሲዎች በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች አሠሪዎች ፌዴሬሽን ተመሳሳይ ቅሬታውን ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጽሑፍ አሳውቋል። ሪፖርተር የተመለከተው የፌዴሬሽኑ ደብዳቤ፣ ፌዴሬሽኑ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል፣ በውጭ አገር ሥራ ሥምሪት ዘርፍ የሚወጡ አዳዲስ መመርያና አዋጆች ፀድቀው ወደ ሥራ ከመግባታችው በፊት፣ ገና በረቂቅ ደረጃ ላይ እያሉ የማየትና የበኩሉን ገንቢ አስተያየት የማቅረብና የመወያየት ሰፊ ልማድ እንዳለው፣ በዚህም ለዘርፉ የተሻለ ግብዓት ይሆናሉ በማለት ያመነባቸውን ሐሳቦች በጽሑፍ ጭምር በማቅረብ የጎላ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁሟል። ይሁን እንጂ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘውን የውጭ አገር ሥራ ሥምሪት አዋጅ ሙሉ በሙሉ የሚሽርና በአዲስ የሚተካ ረቂቅ አዋጅ በሥራና ከህሎት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ፣ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል እየታየ እንደሆነ መገንዘቡን ፌዴሬሽኑ ጠቁሟል። ‹‹ረቂቅ አዋጁ የእኛን ተሳትፎና ምልከታ ሳያካትት ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር መላኩ ረቂቅ አዋጁን የተሟላ ያደርገዋል የሚል እምነት የለንም፣ በዚህም ቅሬታ እንደፈጠረብን መግለጽ እንወዳለን። ስለሆነም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ረቂቅ አዋጁ ላይ እንደ ማንኛውም የባለድርሻ አካል የሚጠበቅብንን ግብዓት በማበርከት ዜጋ ተኮርና የሚያሠራ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ኃላፊነታችንን በተሟላ መንገድ እንድንወጣ፣ የአዲሱን ረቂቅ አዋጅ ቅጂ ለፌዴሬሽናችን በጊዜ በመስጠት እንዲተባበረን በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፤›› ሲል ሚኒስቴሩን ጠይቋል። ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሁለት የውጭ ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች በበኩላቸው፣ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ አወዛጋቢ ድንጋጌዎች የተካተቱበት ስለመሆኑ መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ሥራ ፈላጊዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች አማካይነት ወደ ውጭ መሄድ እንደማይችሉ፣ ይልቁንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራ ፈላጊዎችን በሙሉ መዝግቦ ለኤጀንሲዎች የሚመድብበት አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ በሪቂቅ አዋጁ ውስጥ መካተቱን ጠቁመዋል። እንደ ኤጀንሲዎቹ ከሆነ፣ ይህ አሠራር ከዚህ በፊት ከአንድም ሁለት ጊዜ ተሞክሮ መሳካት ባለመቻሉ ቀሪ መደረጉንና አሁንም ቢሆን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታም ይህንን አሠራር ቢመልሰው ይሳካል ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ ሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት ኤጀንሲዎች ወደ ውጭ ለሚልኳቸው ሠራተኞች መብትና ደኅንነት ማስከበሪያ 100 ሺሕ ዶላር ወይም ተመጣጣኙን የኢትዮጵያ ብር በኤጀንሲው ስም በተከፈተ ዝግ ሒሳብ ማስቀመጥ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ አሁን በተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ ግን ኤጀንሲዎች ለሠራተኞች መብትና ደኅንነት ማስከበሪያ 200 ሺሕ ዶላር በሚኒስቴሩ ዝግ ሒሳብ በካሽ ማስገባት እንደሚኖርባቸው መጠቀሱን ገልጸዋል። ይህ የኤጀንሲዎችን አቅም ያላገናዘበ እንደሆነ የሚጠቅሱት ኤጀንሲዎቹ፣ ሪቂቅ አዋጁ ሙሉ ይዘት እንዲሰጣቸውና በእነሱ በኩል ሊቀርቡ የሚችሉ ግብዓቶች እንዲካተቱና ለአጠቃላይ የውጭ ሥራ ዘርፍ የሚጠቅምና የሚያሠራ አዋጅ እንዲቀረፅ፣ የረቂቅ አዋጁ ሙሉ ይዘት ተሰጥቷቸው አስተያየታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አማካሪ አቶ ደረጀ ፍቅሬ፣ ኤጀንሲዎቹ ስላቀረቡት ቅሬታ መረጃ እንደሌላቸው፣ ነገር ግን በሚኒስቴሩ በኩል የተላለፈ ክልከላ እንደሌለ ተናግረዋል። ‹‹ኤጀንሲዎቹ አቅርበናል የሚሉት ጥያቄ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሲደርስ ምላሽ ይሰጥበታል፤›› ብለዋል።