ዘላቂነት ያለው የልማት ፖሊሲ እንዲነደፍ ጥሪ ቀርቧል

እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2023 ባሉ 22 ዓመታት መንግሥት ድህነትን ለመቀነስ ያወጣቸው ፖሊሲዎች ውጤት ከዜሮ እንደሚያንስ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ያደረገው ጥናት አመላከተ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2023 ባለው 22 ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አፈጻጸምና አስተዳደር ምን እንደሚመስል ያደረገው ጥናት ሐሙስ ግንቦት 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ የጥናት ውጤቱን ያቀረቡት የአሶሴሽኑ የፖሊሲና ጥናት ግምገማ ክፍል ተወካይ ዳይሬክተርና ተመራማሪ አቡሌ መሀሪ (ዶ/ር)፣ እ.ኤ.አ. ከ2001 እስከ 2023 ባሉ ዓመታት ድህነትን ለመቀነስ የወጡ ፖሊሲዎች (Low Poverty Elasticity to Growth) ውጤታቸው፣ በታሰበው ልክ ግቡን አለመምታቱንና ድህነት አለመቀነሱን ገልጸዋል። ‹‹ፖሊሲዎቹ ደሃን ከድህነት ማውጣት አልቻሉም፣ ድህነትን ለመቀነስ ያመጡት ውጤትም ከዜሮ ያንሳል፤›› ብለዋል። ‹‹ደሃን ከድህነት የሚያወጣ ዘላቂ ፖሊሲ መንደፍ ያስፈልጋል፤›› ሲሉም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ የማምረት አቅም እ.ኤ.አ. እስከ 2019 ዕድገት ቢያሳይም፣ ከዚያ በኋላ ግን ባለበት እየሄደ (Stagnant) መሆኑ በጥናቱ መለየቱን አክለዋል። በዚህም ሳቢያ ምርትና ማኅበራዊ ግስጋሴን የማሳደግ አቅም መገደቡን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደገ ካሉ አገሮች አንዷ የነበረች ቢሆንም፣ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ግን ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ እያሽቆለቆለ መሆኑ በአሶሴሽኑ ጥናት ተመላክቷል። በተለይ ቋሚ ገቢ ያላቸው ዜጎች ባለው የዋጋ ግሽበት የተነሳ ፍላጎታቸው መቀነሱ፣ ከዜጎች ፍላጎት በተጨማሪ የምርት አቅርቦት እንደቀነሰ በጥናቱ ቀርቧል። እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ምኅዳር ወጥነት የሌለውና ግልጽ ያልሆኑ ፖሊሲዎች እንደነበሩት፣ በአገሪቱ ያለው የእርስ በርስ ግጭትና አለመረጋጋት ችግሩን ማባባሱ በጥናቱ ተጠቁሟል። በተመሳሳይ እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ የመንግሥት አስተዳደር ተገማች አለመሆንና በሕዝብ ያለው አመኔታ እየተዳከመ መምጣቱ በጥናቱ ተለይቷል። ግጭቶች የአስተዳደርን መዳከምና የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ (TYDP) በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ እንዳይደረግ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት እንዲፈጠር፣ ድህነት እንዲጨምር፣ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲቀንስ ማድረጋቸው በጥናቱ ተመላክቷል።

ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ የምርት መቀነስ፣ የሥራ አጥነት መጨመርና በባለሀብቶች ላይ የደኅንነት ሥጋት ማስከተሉ ተመላክቷል። ኢኮኖሚው በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ ምክንያት ዘገምተኛ የሆነ ዕድገት ማሳየቱ በጥናቱ ተካቷል። ችግሩን ለመፍታት ዘላቂነት ያለው የልማት ፖሊሲ ነድፎ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ፣ መንግሥት ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ አስተዳደራዊ መዋቅሩን እንዲያጠናክር፣ ከዚህ በተጨማሪ የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ በትኩረት እንዲሠራ በጥናቱ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል። በኢትዮጵያ የአገልግሎት ዘርፍ ዕድገት እየጨመረ በመሆኑ፣ ግብርና ለአገራዊ ጠቅላላ ምርት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2004 እና 2005 አንድ ሦስተኛ ድርሻ አለው ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የመቀነስ ምጣኔ አሁንም እንደሚቀረው ተመላክቷል። ሆኖም የአገሪቱን 32.4 በመቶ ኢኮኖሚ ለሚያስገኘው የግብርና ዘርፍ የሚቀርበው የብድር መጠን አነስተኛ መሆኑ፣ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2012 ጀምሮ መጠኑ እየቀነሰ ከሦስት በመቶ ማነሱ ተጠቅሷል። በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወጣ የሚያስችል አዋጅ ቢኖርም እስካሁን እንዳልወጣ የተናገሩት አቡሌ (ዶ/ር)፣ በየዘርፉ ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ የማውጣት አዋጭነት ላይ አጠቃላይ ጥናት እንዲካሄድ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል። በኑሮ ውድነት፣ በኢኮኖሚ ሁኔታና በሥራ ገበያ መረጃ ላይ የተመሠረተ ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ ሥርዓት ሊነደፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ባለፉት 30 ዓመታት እስካሁን ያከናወናቸው ሥራዎች ምን ለውጥ አመጡ? የሚለው በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ይፋ እንደሚደረግ፣ የአሶሴሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መንግሥቱ ከተማ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *