በጥቅምት ወር ነበር ወደ ፖርት ሱዳን አፈግፍጎ የቆየው በጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ጠንካራ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የከፈተው፡፡ ለዘጠኝ ወራት ለቋቸው የቆዩ ግዛቶችንና ከተሞችን ቀስ በቀስ መልሶ መቆጣጠርም ጀመረ፡፡ እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 15 ቀን 2023 ጀምሮ የሱዳን ሠራዊት ከጄኔራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር የሚያደርገው ጦርነት፣ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ሁለተኛ ዓመቱን ሲደፍን እንደ ካርቱም ያሉ ቁልፍ ቦታዎችን መቆጣጠር ችሎ ነበር፡፡ የሱዳን ጦር ከጥቅምት ጀምሮ በከፈተው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ወደ 430 ቁልፍ ቦታዎችን መልሶ መቆጣጠር መቻሉ፣ በጦርነቱ የበላይነት እየጨበጠ መጥቷል የሚል ግምት አሰጥቶ ነበር፡፡

ከ23 ወራት በኋላ የሱዳን ጦር እ.ኤ.አ. መጋቢት 21 ቀን 2025 የካርቱም ቤተ መንግሥትን ሲቆጣጠር፣ የመላው ዓለም መገናኛ ብዙኃን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በቃ ተሸነፈ ወደሚል ድምዳሜ ያጋደለ ዘገባ መሥራት ጀመሩ፡፡ በጊዜው የሄሜቲ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሥልታዊ ማፈግፈግ ማድረጉን ቢናገርም፣ ነገር ግን የሱዳን ጦር ማሸነፍ ሞገዱን ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ ሦስቱ መንታ ከተሞች በሚባል የሚታወቁትን በሁለቱ ዓባይ ወንዞች መጋጠሚያ የሚተሳሰሩትን ካርቱምን፣ ኦምዱርማንና ባህሪን የሱዳን ጦር መልሶ የተቆጣጠረ በመሆኑ ብቻ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ላይ ድል እየቀናው ነው ተባለ፡፡ የሱዳን ጦር በዚህ ላይ የስናርና የአልጀዚራ ግዛቶችን ቁልፍ ዋና ከተሞች መያዙ ከባድ ግምት አሰጥቶታል፡፡ የጄኔራል አልቡርሃን ሠራዊት ከቀይ ባህር ዳርቻዋ ከፖርት ሱዳን ተንደርድሮ ወደ ደቡብ አቅጣጫ መላ ሱዳንን መልሶ እየተቆጣጠረ፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደ ደቡብ እንዲያፈገፍግ ማስገደዱ በሰፊው ተነገረ፡፡ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በማዕከላዊ ሱዳን አካባቢዎች በሱዳን ጦር ከበባ ውስጥ ወደቀ መባል ጀመረ፡፡ በካርቱም ግዛት፣ በስናርና በሰሜን ኮርዶፋን የተወሰኑ አካባቢዎች እንቅስቃሴው እንዲገደብ መገደዱም ተነገረ፡፡ በመጋቢትና በሚያዝያ ወራት ይወጡ የነበሩ ሪፖርቶች የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የአቅርቦት ሰንሰለቱ ተቆርጦ የሱዳን ጦር ኃይል የጦርነቱ አሸናፊ ሆኖ መውጣቱን የሚጠቁሙ ነበሩ፡፡ የሱዳን ጦር ኃይል አሸናፊ እየሆነ የመጣው ደግሞ አዳዲስ የሠራዊት ምልመላ ስትራቴጂዎችን መጠቀም በመጀመሩ፣ የሃይማኖት ፖለቲካ ቡድኖችን ጨምሮ አዳዲስ የውጊያ አጋሮችን በማበጀቱ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ግብፅ ካሉ አገሮች የሚገኘው የውጭ ድጋፍም እየተጠናከረ በመምጣቱ እንደሆነ በሰፊው ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ በዳርፉርና በኮርዶፋን ግዛቶች ብቻ እንቅስቃሴው እየተገደበ መጥቷል ሲባል የሰነበተውን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን የሱዳን ጦር የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ማሸነፉና መደምሰሱ እንደማይቀር በርካቶች ገምተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጄኔራል ሄሜቲ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዳርፉርን ማዕከሉ አድርጎ በያዛቸው አካባቢዎች የራሱን መንግሥት መመሥረቱን ሲያውጅ ደግሞ፣ የሱዳን ጦርነት በአገሪቱ በሁለት ጄኔራሎች የሚመራ መንግሥት ሊያዋልድ ይችላል የሚል መላምት እንዲሰነዘር የጋበዘ ነበር፡፡    ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ማፈግፈጉ ታክቲካዊ መሆኑን መናገሩ ተዓማኒነት ባጣበት በዚያ ወቅት ከውስጥም ከውጭም አጋሮችን ለማሰባሰብ መንቀሳቀሱ ይነገር ነበር፡፡ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የደቡብ ኮርዶፋን ግዛት ሸማቂ በመሆን የሚታወቀው የደቡብ ሱዳን የነፃነት ትግል ማለትም የሱዳን ሕዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ በሰሜን (Sudan People’s Liberation Movement-North/ SPLM-N) በመባል ከሚታወቀው ከአብዱላዚዝ አል ሂሉ ኃይል ጋር ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አጋር መሆኑ ሲነገር ነበር፡፡ ይህ ቡድን በሰሜን ሱዳን በሰሜን ኮርዶፋን ገብቶ የሱዳንን ጦርነት የተዋጋ ሲሆን፣ የሱዳን ጦርም የግዛቱን ዋና ከተማ ኤል ኦቤድን በአየር ሲደበድብ ቆይቷል፡፡ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዋና ማዕከሉ አድርጓቸዋል የሚባሉ የደቡብ ዳርፉር ዋና ከተማ ኒያላን፣ እንዲሁም የምሥራቅ ዳርፉር መዲና አልዳይን የሱዳን ጦር ተከታታይ የአየር ድብደባ ሰለባ ሆነው ነበር፡፡ ከካርቱም እስከ ሰሜን ዳርፉር ዋና ከተማ ኤልፋሸር ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ ይርቃል የሚለው የአልጄዚራ ሰሞነኛ ዘገባ፣ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለካርቱም ቅርብ ናት የምትባለው ጠንካራ ይዞታው ይህችው ከተማ እንደሆነች ይጠቁማል፡፡ የሱዳን ሠራዊት ግን በ800 ኪሎ ሜትር የምትርቀዋን ኤልፋሸርን በመደበኛነት በአየር ሲደበድብ መክረሙን የሚገልጸው ዘገባው፣ ሌላው ቀርቶ በከተማዋ አቅራቢያ የሚገኙ ረሃብና ጦርነት ሽሽት የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎችም የአየር ድብደባው ሰለባ መሆናቸውን ያትታል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ቢያንስ እስካሁን አላጠፋውም ነው የሚባለው፡፡ ከሰሞኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ያውም ፖርት ሱዳን ድረስ ሄዶ የፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች ደግሞ የሱዳን ጦር ገና መቼ ለየለት እያስባሉ ይገኛል፡፡ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ. ማክሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2025 የሱዳን ጦር ያለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜያዊ ዋና መቀመጫ ሆና ያገለገለችው ፖርት ሱዳን በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተደበደበች፡፡ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድሮን በሁለት ዓመቱ ጦርነት መጠቀሙ አዲስ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ተሸንፎ ማፈግፈጉና እንዳበቃለት እየተነገረ ባለበት ወቅት ያውም ሰሜን ሱዳን ጫፍ ቀይ ባህር ጠረፍ ላይ በምትገኘዋ ፖርት ሱዳን ላይ የድሮን ጥቃት ማድረሱ፣ በሱዳን ጦርና በደጋፊዎቹ ዘንድ ከባድ ድንጋጤ ሲፈጥር ነው የታየው፡፡  የጄኔራል ሄሜቲ ቡድን ለስድስት ተከታታይ ቀናት ያለማቋረጥ የድሮን ጥቃት ማድረሱ ተነግሯል፡፡ ወደብ፣ ወታደራዊ ካምፕ፣ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ሆቴሎችና መኖሪያዎች ጭምር የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድሮን ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ ሲሆኑ፣ አጥፍተው የሚጠፉ ድሮኖችን ጭምር በመጠቀም ጥቃቱን እየፈጸመ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የሱዳን ጦርነት በሱዳን ጦር ኃይል የበላይነት ሊቋጭ ከጫፍ መድረሱ በሚነገርበት በዚህ ወቅት፣ የፈጥኖ ደረሽ ኃይሉ በምን ተዓምር ነው አዲስ ዓይነት ከባድ የድሮን ጥቃት ለማፋፋም የቻለው የሚለው ብዙዎቹን እያነጋገረ ነው፡፡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፣ ‹‹የሱዳን ጦርነት አሁን ከራሳቸው ከሱዳኖች እጅ ወጥቷል፡፡ የፖርት ሱዳኑ ምት ብዙ ተወራ እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ድንበር ቅርብ የሆነውን የከሰላ አውሮፕላን ማረፊያንም በድሮን ደብድበዋል፡፡ ጎረቤት ቻድና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ነበሩ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ደጋፊነት ሲከሰሱ የቆዩት፡፡ ሆኖም ከሞሪታኒያና ከሊቢያ ድረስ አጋሮች አግኝቷል፡፡ በፖርት ሱዳን ጥቃት ተደናግጠው አንዳንድ አገሮች ቆንስላቸውን ዘግተው እየወጡ ነው፤›› በማለት ነው ስለሰሞኑ ሁኔታ የተናገሩት፡

በሚያዝያ አጋማሽ የሱዳን ጦርነት ሁለተኛ ዓመት መድፈኑን አስመልክቶ፣ ‹‹መፍትሔ ያልተገኘለት ሁለተኛ ዓመቱን የደፈነው የሱዳን ጦርነትና ቀጣናዊ ሥጋቱ›› በሚል ርዕስ ሪፖርተር ላስነበበው ዘገባ ግብዓት የሆነ ሐሳባቸውን በተመሳሳይ ያጋሩት እኚሁ የፖለቲካ ተንታኝ፣ በሱዳን የቀጠለውን ጦርነት አስመልክቶ አራት ቢሆኖች እንደሚታያቸው ነው አክለው የተናገሩት፡፡ ‹‹ሱዳን ጦርነት የሚራዘምበት ሁኔታ ከቀጠለ አንደኛ የሊቢያ ዕጣ ፈንታ ሊገጥማት ይችላል፡፡ የቤንጋዚና የትሪፖሊ መንግሥት የሚባሉ ሁለት ዋና ዋና ኃይሎች በሊቢያ የተፈጠሩ ሲሆን፣ በውጭ ኃይሎች ጎራ የለየ ረጂነት ለረዥም ዓመታት ሲዋጉ ኖረዋል፡፡ ልክ እንደ ሁለቱ የሱዳን ጄኔራሎች ሁለት መንግሥት ይዘው የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት ተከትለው ውጊያውን የሚቀጥሉበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል፡፡ ሁለተኛው ቢሆን የሶማሊያ ዓይነት የተበጣጠሰ ራስ ገዝ ግዛቶችና ቡድኖች ሊፈለፈሉ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በማዕከላዊ መንግሥት ላይ የማመፅ ልምድ የነበራቸው እንደ ሰሜን ኮርዶፋንና ብሉ ናይል የመሳሰሉ ግዛቶች ያሉ በመሆናቸው በሱዳን ሁለቱ ጄኔራሎች ከያዙት አካባቢ ውጪ የሆኑ ራስ ገዝ መንግሥት መሥርተናል የሚሉ ኃይሎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ በሦስተኝነት እኔ የሚታየኝ ሱዳን ከሶሪያ በከፋ ደረጃ የሽብርተኞች ምሽግ ልትሆን የምትችልበት ዕድል መስፋቱ ነው፡፡ የሱዳን ጦር አጋር የሆኑ አክራሪ የሃይማኖት ፖለቲካ የሚያራምዱ ኃይሎች አሉ፡፡ ጦርነቱ ሲያበቃ እነዚህን መቆጣጠር ከባድ ሲሆን፣ በጦርነቱ መራዘም ሊፈጠር የሚችል የኃይል መሳሳትን ተጠቅመው ወደፊት ሊመጡም ይችላሉ፡፡ ከእስራኤል ጋር ከባድ ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የፍልስጤም ሐማስና የየመኑ ሁቲ፣ እንዲሁም ትረዳቸዋለች የምትባለው ኢራን በቀይ ባህር ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ማዕከል ልትሆን በምትችለዋ በሱዳን እግር ማሳረፊያ ወደ መፈለግ መግባታቸው አይቀርም፡፡ ሱዳን በታሪኳ በሐሰን አልቱራቢ ለሚመሩት የሙስሊም ወንድማማቾች ማዕከል ሆና ታውቃለች፡፡ ሱዳን ዓለም አሸባሪ ብሎ የፈረጃቸው የእነ ካርሎስ ቀበሮውና የእነ ኦሳማ ቢላደን መሸሸጊያ እንደነበረች መረሳት የለበትም፡፡ አሁንም ቢሆን ከሳህል ቀጣና፣ ከመካከለኛው አፍሪካ፣ እንዲሁም ከሰሜን አፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ ለሚመጡ ኃይሎች መሸሸጊያ ሆና ለማገልገል ልትመረጥ ትችላለች፤›› በማለት የተናገሩት ተንታኙ፣ ከእነዚህ ውጪ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጎ ጫናና ግፊት ጦርነቱ ቆሞ የሲቪል መንግሥት ሊመሠረት የሚችልበት ጠባብ ዕድል መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡   አልጄዚራ ከሰሞኑ ስለሆነው በድሮን ጥቃቶች ታጅቦ ስለተፋፋመው የሱዳን ጦርነት ባተተበት አንድ ዘገባው፣ ከሱዳን ቀውስና ዕልቂት ጀርባ የውጭ ኃይሎች ድጋፍና ረዥም እጅ የጎላ መሆኑን ነው የዘረዘረው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የምትረዳው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የድሮን ጥቃቱን እያፋፋመ ያለው በቻይና ሥሪት ድሮኖች ጭምር መሆኑ ይነገራል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ እንዲሁም እንደ ሒዩማን ራይትስዎች የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ቻይና ሠራሽ ድሮኖች በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከቻይና ተገዝተው ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መቅረባቸውን እንዳረጋገጡ ገልጸዋል፡፡ የሱዳን ጦር ኃይል ይህን መሠረት በማድረግ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያቆመና ዲፕሎማቶችንም ያባረረ ሲሆን፣ ጉዳዩንም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች አቤት ሲል መሰንበቱ ታውቋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መንግሥት ግን ክሱን መሠረት የለሽ በማለት አጣጥላዋለች፡፡ ይሁን እንጂ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የሶማሊያ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት የሆነችውን እንደ ፑንትላንድ፣ እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የቀጣናው አገሮችን በመጠቀም ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ድጋፍ ታደርጋለች በማለት የሱዳን ሠራዊትና ደጋፊዎቹ ክሶችን ሲያሰሙ ነበር፡፡  የሱዳን ሠራዊት ይህን ቢልም፣ ነገር ግን ራሱም ቢሆን ከውጭ ደጋፊዎቹ የጦር ዕርዳታና ድጋፍ ሲቀበል መታየቱ ተረጋግጧል፡፡ ግብፅ እግረኛ ሠራዊት ከመላክ ጀምሮ የአየር ድብደባ ዕገዛ ለሱዳን ጦር ታደርጋለች ይባላል፡፡ የሱዳን ጦር የቱርክ ሥሪት ባይራክታር ቲቢ 2 ድሮኖችን መታጠቁ ይነገራል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2023 መገባደጃ 120 ሚሊዮን ዶላር ከፍሎ ባይራክታር ቲቢ 2 ድሮኖችን የገዛ ሲሆን፣ በጦርነቱ በሰፊው እየተገለገለባቸውም ይገኛል ተብሏል፡፡ የሱዳን ጦር የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስንና ሌሎች የጎረቤት አገሮችን ቢከስም፣ ነገር ግን የኤርትራን፣ እንዲሁም የሕወሓት ተዋጊዎችን ለውጊያ በማሠለፍ እንደሚወነጀል ይነገራል፡፡ የሱዳን ተዋጊዎች ከያዟቸው አካባቢዎች ወደ ውጭ ይወጣል ከሚባለው የወርቅ ምርት ውስጥ 97 በመቶውን የምትረከበዋ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ናት በማለት አገሪቱ የሱዳን ግጭትና ቀውስ ዋና አቀጣጣይ በሚል ትተቻለች፡፡ ይሁን እንጂ የሱዳን ሠራዊትም ቢሆን ከሳዑዲ ዓረቢያ ጀምሮ ከበርካታ አገሮች ድጋፍ እንደሚቀበል በተቃራኒው ይነገራል፡፡ አንዳንድ አገሮች የሱዳንን ግጭት የሚያባብሱት ከራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት በመነሳት እንደሆነ የሚጠቁሙት የፖለቲካ ተንታኙ፣ የግብፆችን ፍላጎት ምሳሌ በማድረግ ጉዳዩን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሱዳን በሸቀጣ ሸቀጥ ወይም በብዙ የፍጆታ ዕቃዎች ራሷን የቻለች አገር ነበረች፡፡ እኔ ባለኝ መረጃ ግን ግብፆቹ ለሱዳን ጦር አጋዥ ነን ብለው በሚያደርጉት የአየር ድብደባ ፋብሪካዎችን ሆን ብለው እያወደሙ ነው፡፡ ለሱዳን ያሰቡ ይምሰሉ እንጂ ሱዳን ለረዥም ጊዜ እንድትንኮታኮት ነው ግብፆቹ ፍላጎታቸው፡፡ የዓባይ ውኃ ተጋሪያቸውን ለማዳከም በማሰብ ብቻ ሳይሆን ግብፆቹ ሀላይብ ትሪያንግል በሚባል የድንበር ግዛት ከሱዳን ጋር ሲወዛገቡ የቆዩ ናቸው፡፡ በሌላም በኩል ግብፆቹ እንደ ማኅበረሰብ የሱዳንን የሆነ ነገር ሁሉ ሕዝቡን ጭምር ዝቅ አድርጎ የመመልከትና ዘረኝነት የተሞላ ስሜት አላቸው›› በማለት የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ሁሉ ፍላጎት ያላቸው አገሮች በሱዳን ጦርነት እጃቸውን በማስገባታቸው ቀውሱን ማስቆሙ ከባድ እንደሚሆን ነው የገመቱት፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሺናል የሱዳን ጦርነትን ያወሳሰበውና እንዳይቆም እያደረገው ያለው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የምታስታጥቀው ዘመናዊ መሣሪያ እንደሆነ በሪፖርቱ ይፋ ማድረጉ ትልቅ ትኩረት ስቧል፡፡ ከሞርታር የሚተልቅ፣ ነገር ግን ከመድፍ አነስ የሚል 810 ኪሎ ግራም የሚመዝንና ወደ ዘጠኝ ኪሎ ሜትር የሚወነጨፍ ቅምቡላ የሚተኩሰውን ቻይና ሠራሽ ሀውዜር የተባለ መሣሪያ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለቡድኑ አቅርባለች የሚለው ሪፖርቱ፣ በቪዲዮና በፎቶግራፍ ምሥሎች በማስደገፍ የዓለም መነጋገሪያ አድርጎታል፡፡ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በዳርፉርና በካርቱም ግዛቶች ይህንኑ መሣሪያ መጠቀሙን አረጋግጫለሁ የሚለው አምነስቲ፣ መሣሪያውን ከቻይና ገዝታ ያቀረበችው ደግሞ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ናት ይላል፡፡ ለሱዳን ዕልቂትና ቀውስ ሰለባዎች መርጃ የሚሆን ድጋፍ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ከሚፈለገው ዕርዳታ ከ6.6 በመቶ በላይ ማቅረብ አልቻለም ይላል አምነስቲ፡፡ ጦርነቱን በማስቆም ረገድ በቂ ጥረት ሳይደረግ ሱዳኖቹን ለመርዳትም በቂ ድጋፍ አለመደረጉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን ሊያሳፍር የሚገባ ጉዳይ ነው የሚለው አምነስቲ፣ ለግጭቱ እሳት በማቅረብ የሚተባበሩ እንደ ዓረብ ኤምሬትስ ያሉ አገሮች አንድ ሊባሉ ይገባል በማለት ግጭቱን በማባባስ የወነጀላትን አገር ይኮንናል፡፡ ይህ ሪፖርት ደግሞ ከፖርት ሱዳኑ የድሮን ድብደባና ከጦርነቱ መባባስ ጋር በተገናኘ በሰፊው እየተራገበ ነው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ጉዳዩን ውድቅ ብታደርግም ሆነ ዓለም አቀፍ ክሱም የረገበ ቢመስልም፣ ነገር ግን በሒደት የዓረብ ኤምሬትስ አጋር የሆኑ አገሮች ደጅ ድረስ ክሱ ሊሰማ እንደሚችል ነው የተገመተው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ የፖርት ሱዳንን ድብደባ አውግዞ፣ የሱዳንን ጉዳይ በቅርበት እንደሚከታተለው በማስታወቅ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በተመሳሳይ የጋመውን ሰሞነኛ ጦርነት አውግዞታል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *