ምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት መገደላውን ነዋሪዎች ተናገሩ። ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 24/2014 ዓ.ም. በዞኑ በአሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ተገድለዋል የተባሉ ሰዎች ቁጥርን በትክክል ለማወቅ ባይቻልም ከ50 በላይ መሆናቸው ይነገራል። ቢቢሲ ትናንት እና ዛሬ (ነሐሴ 25 እና 26) ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በጥቃቱ የተገደሉ ከ100 በላይ አስክሬኖችን መመልከታቸውን ቢገልፁም፤ ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ የሟቾች ቁጥር ከ50 እንደማያንስ ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገው አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ብሔር ተኮር በሆኑ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። ከሁለት ቀናት በፊት በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት ያደረሱት “የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው” ሲሉ ነዋሪዎች ይከስሳሉ። ቢቢሲ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ይህንን ጥቃት ያደረሰውን ታጣቂ ቡድን ማንነት ከነዋሪዎች ባሻገር ከተጨማሪ ምንጮች እና ከክልሉ ባለሥልጣናት ለማረጋገጥ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ዛሬ ከሰዓት ያነጋገርናቸው የአጋምሳ ነዋሪ የቅርብ ዘመዶቻቸው በጥቃቱ እንደተገደሉባቸው እንዲሁም ንብረታቸው እንደተዘረፈባቸው ገልጸው፤ ካለፈው እሁድ ጀምሮ እስከ ትናንት በከተማዋ ስለነበረው ሁኔታ እንዲህ ተናግረዋል። “አጋምሳ አሁንም አልተረጋጋችም። አሁንም ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ነው ያለችው። ሰው ፈርቶ ጫካ ውስጥ ተደብቆ ነው ያለው። እሑድ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከተማዋን ለቅቆ ወጣ። እነሱ ከወጡ በኋላ ሰኞ ጠዋት ተኩስ ሰማን። ከእንቅልፋችን ስንነሳ ተከበናል። ኦነግ ነን ያሉ ‘ማታ ከዚህ የለቀቁት ግቡ ብለውን ነው የመጣነው’ አሉ።

ከዚያ የነዋሪውን መሣሪያ መሰብሰብ ጀመሩ። . . . እስከ ሌሊት ድረስ 59 ያህል መሣሪያ ሰበሰቡ። ማክሰኞ ጠዋት ከእንቅልፋችን ሳንነሳ በኪረሙ ወረዳ ሀሮ ከምትባል ቦታ ፋኖ የሚባሉ ታጣቂዎች ወደ አጋምሳ ከተማ ገቡ። ሰው ገደሉ። ቤት አቃጠሉ። ንብረት ዘረፉ። . . . ሕዝቡም ተፈናቅሎ ወጣ። እኔ ባለኝ መረጃ 87 የሚደርሱ ሰዎች የት እንደ ደረሱ አይታወቅም። 55 ሰዎች ቀብረናል። 55ቱም ሲቀበሩ ነበርኩ። ከጎርፍ ውስጥ የአራት ጨቅላ ልጆች አስክሬን አግኝተናል። . . . በስለት ወግተው የገደሏቸውም አሉ።” ጥቃቱ ተከትሎ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙት የ10 ቤተሰብ አባላት አስተዳዳሪ አባት በተመሳሳይ ግድያው የጀመረው ማክሰኞ ነሐሴ 24 ንጋት 12 ሰዓት ነው ይላሉ።

“ገና ከእንቅልፍ እንደተነሳን ፋኖዎቹ በአጋምሳ ከተማ ጫፍ እና ጫፍ ተኩስ ከፍተው ወደ መሃል ከተማ መግባት ጀመሩ” ብለዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በከተማዋ ሰፍሮ የነበረው የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪ ኃይል ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ በፌደራሉ መንግሥት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወደ ከተማዋ ዘልቆ ገብቶ ነበር። በመቀጠል መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ መውጣቱን ተከትሎ ነዋሪዎች ፋኖ ናቸው ያሏቸው ታጣቂዎች ማክሰኞ ንጋት ወደ ከተማዋ ዘልቀው በመግባት ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ‘አብራችኋል’ ያሏቸውን መግደላቸውን ጨምረው ተናግረዋል።

ጥቃቱን በተመለከተ ቢቢሲ የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ የክልሉ ኃላፊዎችን እንዲሁም በፌደራል መንግሥት ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በተለይ የክልሉ አስተዳዳሪዎች በአካባቢው ብሔር ተኮር የሆኑ ጥቃቶች የሚፈጸሙት መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና ‘በጽንፈኛ የአማራ ታጣቂዎች’ መሆኑን ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአጋምሳ ከተማ ነዋሪ አዛውንት፣ ንጋት 12 ሰዓት ላይ የጀመረው ጥቃት እስከ እኩለ ቀን 7 ሰዓት ድረስ ዘልቆ እንደነበረ ተናግረዋል። አስር የቤተሰብ አባሎቻቸውን ይዘው እንደሸሹ የሚናገሩት እኚህ ነዋሪ “በእድሜ የገፋች መንቀሳቀስ የማትችል እናቴን ቤት ውስጥ ትተናት ነው የሸሸነው። አሁን በምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለች አናውቅም። አሁንም የምንበላው፤ የምንሄድበት የለንም” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል። እኚህ ግለሰብ ማክሰኞ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉ ከ100 የማያንሱ ሰዎች አስክሬንን መመልከታቸውን ገልፀዋል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪ እና የአጋምሳ ከተማ ነዋሪ የሆነ ወጣት ደግሞ እስከ ሐሙስ ረፋድ ድረስ የሰዎች አስክሬን ተሰብስቦ አለማለቁን ተናግሯል። “እስካሁን ተሰብስቦ ያልተቀበረ አስክሬን ሜዳ ላይ ወድቆ ይገኛል። ሕዝቡ ገና ከእንቅልፉ ሳይነሳ ነው ተኩስ የተከፈተበት። የጠፉ ሰዎች እየተፈለጉ ነው። ይህን ያክል ሰው ተገድሏል ማለት አይቻልም” በማለት ያለውን ሁኔታ ያስረዳል። “ሕይወቴ በመትረፉ በጣም እድለኛ ነኝ” የሚለው ይህ ወጣት፤ “30 አስክሬን ቆጥሬያለሁ” ብሏል።

ሌላው ዛሬ ያነጋገርናቸው ግለሰብ በጥቃቱ አባታቸውን እንዳጡ ገልፀዋል። “አባቴ አቶ ሞሲሳ ጀማ ይባላል። የ108 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ ነበር። ከቤት መውጣት የማይችል ሰው ነበር። በአሰቃቂ ሁኔታ ገደሉት። ከነቀምት ወደ ቡሬ የሚወስደውን መንገድ ዘግተው ነበር። የሚችለው ሮጦ አመለጠ። ሌላው እህል ውስጥ ተደበቀ። ሌላው ጫካ ገባ።” ብለዋል። ይህን ጥቃት ተከትሎ የአጋመሳ ከተማ ነዋሪዎች በእግራቸው ተጉዘው 24 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ስፍራ ተጠልለው እንደሚገኙ ቢቢሲ ያነጋገረው ተማሪ ይናገራል።

ባለፈው ማክሰኞ በአጋምሳ ከተማ ከተፈጸመው ግድያ በተጨማሪ መጠነ ሰፊ ዘረፋ መፈጸሙን ነዋሪዎች ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል። በንግድ ተቋማት ላይ ዘረፋ መፈጸሙን እና ብዙ የንግድ ቤቶች እና ባንኮች በእሳት እንዲጋዩ መደረጋቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ሰምቷል። ታጣቂዎቹ “በመኪና እና በሞተር የቻሉትን የሕዝብ ንብረት ዘርፈው ይዘው ሄደዋል። ያልቻሉትን ደግሞ አቃጥለዋል። ከተማዋ እርቃኗን ቀርታለች” ብለዋል ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ።

ይህ ጥቃት የተፈጸመው በከተማዋ ሰፍሮ የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከተማዋን ለቅቆ ከወጣ ከሁለት ቀናት በኋላ መሆኑን ነዋሪዎች አስረድተዋል። በአሙሩ ወረዳ ስር በምትገኘው ሃሮ ከተማ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የገጠር ከተማዋ አሁንም ድረስ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር እንደምትገኝ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ቢቢሲ ጉዳዩን በተመለከተ ከሆሮ ጉድሩ ዞን፣ አሙሩ ወረዳ እንዲሁም ከክልሉ ባለሥልጣናት እና የደኅንነት አመራሮች መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *