መነሻ ታሪክ

  1. ሐገራዊ እና ክልላዊ አውድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ከመጋቢት 2010 .ም አንስቶ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል ጥሩ የሚባሉ ለውጦችን ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን በሀገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ከ2010 .ም ጀምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡ ለዚህም በዋናነት እንደ ምክንያት ተደርጎ ሊነሳ የሚችለው በሀገሪቷ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ቀውስ ነው፡፡ በፖለቲካ ልዩነቶች መካረር እና የብሔር ጽንፈኝነት የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና እጅግ የከፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲፈጸሙ ምክንያት ሆኗል፡፡

በዚህም ምክንያት የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ደርሷል፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው ለብዙ መከራና ስቃይ ተዳርገዋል፡፡ በእነዚህ አመታት ውስጥ ከተፈጠሩ የፖለቲካ መካረሮች መካከል በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር መካከል የነበረው በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከሁለቱም አቅጣጫ በተደጋጋሚ ጊዜ ሀይለ ቃልን የያዙ የቃላት ልውውጦች ተደርገዋል፡፡ ይህ በነበረበት ሁኔታ ሀገሪቷን ሲመራ የነበረውን የኢሕአዴግ አደረጃጀትን በማፍረስ በብልጽግና ፓርቲ መተካት በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን መቃቃር አባበብሶታል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነሀሴ 2012 .ም ሊደረግ የነበረው ሀገራዊ ምርጫ በጊዜው ተከስቶ በነበረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት በኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ተራዘመ፡፡ የምርጫውን መራዘም ተከትሎ፤ የትግራይ ክልል አስተዳደር ምርጫ ለማድረግ በማሰብ የሕግ ማሻሻያን ጨምሮ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ማቋቋምን የመሳሰሉ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በፌዴሬሽንና ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት የተላለፈውን ምርጫ በመቃወም ጳጉሜ 4 ቀን 2012 .ም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በትግራይ ክልል ምርጫን አከናውኗል፡፡ በዚህም ምርጫ መሰረት ህወኃት በሙሉ ድምጽ አሸናፊ መሆኑን ገልጿል፡፡

የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ ነሃሴ 30 ቀን 2012 .‹‹…የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት፣ አስፈጻሚ አካላት እና ምርጫ ኮሚሽን ምርጫን በሚመለከት ያወጣው አዋጅ፣ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች እና የፈጸሟቸውተግባራት ከሕገመንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ በመሆናቸው እንዳልተደረጉ የሚቆጠሩ፣ የማይጸኑ እና ተፈጻሚነት የሌላቸው  ናቸው…››2 የሚል ውሳኔ አሳልፏል፡፡ መስከረም 26 ቀን 2013 .ም ህወኃት የፌደራል መንግስቱን ህጋዊነት እንደማይቀበለው አሳውቋል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የቀረበው የፌደራል መንግስቱ የአስተዳደር ዘመኑን ማጠናቀቁ እንደሆነ ለዚህም ምክንያት የፌዴራል መንግስት ምርጫ ከተራዘመበት ጊዜ አንስቶ ምንም ህጋዊ የሆነ ስልጣን እንደሌለው ህወኃት በመግለጫው አሳውቋል፡፡

2. የግጭቱ አጀማመር እና ምንነት

ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል ያለውን ግንኙነት ቢያሻክሩትም ለትጥቅ ግጭቱ ዋነኛ መነሻ ምክንያት የነበረው በጥቅምት 24 ቀን 2013 .ም በትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ነበር፡፡ ይህንን ጥቃት ተከትሎ የትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ የሰሜን ዕዝ ማዘዣን እና በውስጡ የነበሩትን አጠቃላይ ንብረቶች ተቆጠጥሮ እንደነበር በፌደራል መንግስት ተገልጿል፡፡ በትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ በሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ ህግ የማስከበር እርምጃበሚል በጥቅምት 25 ቀን 2013 .ም በትግራይ ልዩ ሀይል፣ ሚሊሻ እና በአጠቃላይ በህወሀት ላይ ወታደራዊ የማጥቃት እንቅስቃሴ እንዲጀመር ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡

ይህንን ጥሪ እና ትእዛዝ ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ (በመቀጠልም የተለያዩ ክልሎች ሚሊሻ እና ልዩ ሀይሎች) በአንድነት በመሆን በትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ ላይ የማጥቃት እንቀስቃሴ አድርገዋል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ የትጥግ ግጭት አጀማመሩ ከላይ በተገለጸው መልኩ በፌደራል መንግስት እና በትግራይ ክልል አስተዳደር መካከል ቢሆንም ግጭቱ አድማሱን እያሰፋ የአማራ ክልልን እና የአፋር ክልልን አዳርሷል፡፡ በዚህ ትጥቅ ግጭት ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ (ፋኖ እየተባለ የሚጠራውንም አደረጃጀት ጨምሮ)፣ የአፋር ልዩ ሀይል፣ የክልሎች ልዩ ሀይሎች፣ የትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ፣ እና የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን በየጊዜው ተሳትፈውበታል፡፡

3. የግጭቱ ምንነት 

የግጭቱን ምንነት ለመወሰን በትጥቅ ግጭት ወቅት ተግባራዊ የሚሆነውን የዓለም አቀፉ የሰብዓዊነት ሕግን (International Humanitarian law) መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡ ይህ ህግ በትጥቅ ግጭቶች ውስጥ የተሳተፉ ሰዎችን እና የሲቪል ሰዎችን ዕጣ ፈንታ የሚቆጣጠሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ይይዛል፡፡ ይህ ህግ በሰብዓዊነት ምክንያቶች የትጥቅ ግጭት ውጤቶችን ለመገደብ የሚሹ ህጎች ስብስብ ነው። በጦርነቱ ውስጥ የማይሳተፉ ወይም መሳተፍ ያቆሙ ሰዎችን ለመከላከል እና የጦርነት ዘዴዎችን እና መንገዶችን ለመገደብ ተግባራዊ ይደረጋል። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ የጦርነት ህግ ወይም የትጥቅ ግጭት ህግ በመባልም ይታወቃል።

በቀድሞ ዩጎዝላቪያ የተፈጸሙ የጦር ወንጀለኞችን ለመዳኘት የተቋቋመው ጊዜያዊ ችሎት (ICTY) “የትጥቅ ግጭት ሁለት ሀገራት የታጠቁ ሃይሎቻቸውን በግጭት ወቅት ሲጠቀሙ ወይንም በአንድ ሀገር ውስጥ የተራዘመ የትጥቅ ግጭት በመንግስት ታጣቂ ሀይሎች እና በተደራጁ የታጠቁ ቡድኖች መካከል ሲኖር ወይም በአንድ ሀገር ውስጥ በተደራጁ የታጠቁ ቡድኖች መካከል የትጥቅ ግጭት ሲኖር የትጥቅ ግጭት አለሲል የተጥቅ ግጭትን አብራርቷል፡፡

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ (IHL) እና ከላይ በICTY በተሰጠው ትርጉም መሰረት ጦርነት ወይም የትጥቅ ግጭት አለ የሚባለው በሁለት ሉዓላዊ ግዛቶች መካከል የትጥቅ ግጭት ሲፈጠር (አለም አቀፍ የትጥቅ ግጭት ተብሎ የሚጠራው) ወይም በአንድ ሉዓላዊ መንግስት እና በተደራጁ ታጣቂ ቡድኖች መካከል ወይም በሁለት የተደራጁ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተራዘመ የትጥቅ ግጭት ሲኖር (አለም አቀፍ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት ተብሎ የሚጠራው) ነው። በዚህም መሰረት የአለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ ለሁለት አይነት የትጥቅ ግጭቶች እውቅና ሰጥቷል እነሱም አለምአቀፍ የትጥቅ ግጭት እና አለም አቀፍ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት ናቸው።

አለም አቀፍ ያልሆኑ የትጥቅ ግጭቶች በተሳታፊዎች ለውጥ እና በተሳትፏቸው መጠን ምክንያት ወደ አለም አቀፍ የትጥቅ ግጭቶች ሊለወጡ ይችላሉ (Internationalization of armed conflict)፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ባልሆነ የትጥቅ ግጭት አለም አቀፍ ያልሆኑ የትጥቅ ግጭቶች በተሳታፊዎች ለውጥ እና በተሳትፏቸው መጠን ምክንያት ወደ አለም አቀፍ የትጥቅ ግጭቶች ሊለወጡ ይችላሉ (Internationalization of armed conflict)፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ባልሆነ የትጥቅ ግጭት  ወቅት የተሳታፊዎች መጨመር ሁል ጊዜ በግጭቱ አይነት ላይ ለውጥ ያመጣል ማለት አይደለም፡፡

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ያልሆኑ የትጥቅ ግጭቶች ላይ ምንም እንኳን ሌላ ተሳታፊ ሀገሮች ቢጨመሩበትም እነዚህ አዲስ ግጭቱ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሀገሮች የሚሳተፉበት መንገድ እና የተሳትፏቸውን መጠን መረዳት የትጥቅ ግጭቱን አይነት ለማወቅ ወሳኝነት አለው፡፡ ... በነሐሴ 12 ቀን 1949 የተፈፀመው የጄኔቫ ስምምነቶች የጋራ አንቀፅ 2 ዓለም አቀፍ የትጥቅ ግጭት ማለት በታወጀ ጦርነት ወይም በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የበላይ ተዋዋይ ወገኖች መካከል ሊቀሰቀሱ በሚችሉ ሌሎች የትጥቅ ግጭት ሁኔታዎች ሙሉ፤ ከሁለቱ በአንዱ እውቅና ባይሰጥም እንኳ፤ የሚደረግ ግጭት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በዚህ ምክንያት ግጭት እንደ ዓለም አቀፍ የትጥቅ ትግል ተደርጎ እንዲወሰድ የሚጋጩ ወገኖች ቢያንስ ሁለት ሉዓላዊ አገራት እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል።

እንዲሁም በተጨማሪ ፕሮቶኮል 1 አንቀጽ 1 (4) ሰዎች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብታቸውን ለማስከበር እንደ የቅኝ አገዛዝ የበላይነትን ፣ የባዕዳንን የጦር ወረራ እና ዘረኛ አገዛዞችን (apartheid) የሚታገሉባቸውን ግጭቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የታጠቁ ግጭቶች አካል እንደሆኑ ይደነግጋል። እንደነዚህ ያሉት ግጭቶች እንደ ብሔራዊ ነፃ የመውጣት እንቅስቃሴ ጦርነቶች ተደርገው የሚወሰዱ ሲሆን በዓለም አቀፍ የትጥቅ ግጭት ላይ ተፈፃሚነት ያላቸው ሁሉም የሕግ ጥበቃዎች በአንድ ግዛት ክልል ውስጥ ተወስነው ቢከሰቱም እንኳን ለእነሱም ተፈጻሚ ይሆናሉ። እንዲሁም ዓለም አቀፍ ያልሆኑ የትጥቅ ግጭቶችን አስቀድሞ የጦርነቱ አካል ያልነበረ ሉዐላዊ ሀገር የታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖችን ደግፎ ወደ ግጭቱ ከተቀላቀለ ዓለም አቀፍ ያልሆኑ የትጥቅ ግጭቶች ወደ ዓለም አቀፍ የትጥቅ ግጭትነት እንደሚቀየሩ የዓለም አቀፍ ፍ/ቤቶች ውሳኔ ያሳያል።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት የምንለው በጄኔቫ ስምምነቶች የጋራ አንቀጽ 3 መሠረት በአንድ በተወሰነ ክልል ውስጥ በመንግሥት እና በታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖች ወይም በሁለት ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የሚደረግ ግጭት ነው። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ያልሆኑ የትጥቅ ግጭት ተጎጂዎች ደህንነትን ለመጠበቅ የተደነገገው የጄኔቫ ስምምነት ተጨማሪ ፕሮቶኮል II በአንቀጽ 1 ላይ ጄኔቫ ስምምነቶች የጋራ አንቀጽ 3 ላይ ከተቀመጠው በተጨማሪ ዓለማ አቀፋዊ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት በአንድ ሀገር መንግስት እና በተቃዋሚ የታጠቁ ቡደኖች ወይም ሌሎች የተደራጁ የታጠቁ ቡድኖች መካከል የሚደረግ የትጥቅ ግጭት ሲሆን በዚህ አንቀጽ ላይ እነዚህ የተደራጁ ታጣቂ ቡድኖች በጥበቃው ስር ብቁ ለመሆን ተጨማሪ መስፈርቶችን ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም መስፈርቶች
    ● የግጭቱ ስፋት ወይም መጠን (Intensity)
    ● የታጠቁ ቡድኖች አደረጀጀት (Organization) እና
    ● የክልሉን የተወሰነ ክፍል መቆጣጠር (Territorial control)

የግጭቱ ስፋት ወይም መጠን (Intensity)፡ ይህንን መመዘኛ በምንመለከትበት ወቅት የግጭቱን አጠቃላይ ይዘት መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ ማለትም ሀገራቶች ያጋጠማቸውን ችግር በመደበኛ የፖሊስ አደረጃጀት መፍታት ተስኗቸው መከላከያ ሰራዊታቸውን ጥቅም ላይ ማዋል ይጅምራሉ፡፡ በተጨማሪም የግጭቱ የጊዜ ስፋት፣ የጥቃት ድርጊቱ ወይም የወታደራዊ ኦፕሬሽኑ ተደጋጋሚነት፣ ጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሳሪያዎች አይነት፣ የሲቪል ሰዎች መፈናቀል፣ የታጠቁ ቡድኖች አንዳንድ ግዛቶችን መቆጣጠር፣ የተጎጂዎች መጠን እና የመሳሰሉት ነጥቦች የግጭቱን ስፋት (Intensity) ለመረዳት ይረዱናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ነጥቦች ሁሉም በአንድነት መሟላት ላይኖርባቸው ይችላል፡፡

የታጠቁ ቡድኖች አደረጀጀት (Organization)፡ በትጥቅ ግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የሆነ ያህል አደረጃጃት ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ በመንግስት ታጣቂ ሀይሎች በኩል ይህ መመዘኛ እንደተሟላ የሚቆጠር (presumed facte) ሲሆን በታጣቂ ቡድኖች በኩል ግን ይህ መመዘኛ ተሟልቷል ለማለት ለምሳሌ አደረጃጀቱ የትእዛዝ ተዋረዱን ማሳየት የሚችል መሆኑ፣ የተለያዩ ከፍሎቹን አቀናጅቶ የተደራጀ ኦፕሬሽኖችን መፈጸም መቻሉ፣ አዳዲስ አባላቶችን ማሰልጠን የሚችል መሆኑ እና የሰብአዊነት ህጎችን ማክበር የሚችል መሆኑ የቡድኑን የተደራጀ መሆን ያሳያል፡፡ የክልሉን የተወሰነ ክፍል መቆጣጠር (Territorial control)፡ ይህ መመዘኛ በጄኔቫ ስምምነት ተጨማሪ ፕሮቶኮል II በአንቀጽ 1 ላይ የተቀመጠ ቢሆንም በጊዜ ሂደት ብዙ ትችቶችን ያስተናገደ እና አሁን ላይ መመዘኛነቱ እየቀረ የመጣ ነው፡፡

ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱት በዋናነት የመጀመሪያዎቹ ሁለት መመዘኛዎች ከተሟሉ የትጥቅ ግጭቱ አለማቀፋዊ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከሁለቱ መመዘኛዎች አንዱ ካልተሟላ ግጭቱ የሀገር ውስጥ ውጥረት ወይም ብጥብጥ (Internal disturbance) ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከላይ ያሉትን መመዘኛዎች እና ህጎች መሰረት አድርገን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ እየተካሄደ ያለውን የትጥቅ ግጭት ዓለም አቀፍ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት ብለን ልንፈርጀው እንችላለን፡፡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ እየተካሄደ ያለው ግጭት ከላይ የተቀመጡትን ሁለቱን መመዘኛዎች በሚገባ የሚያሟላ ሆኖ ስላገኘነው ግጭቱ ዓለም አቀፍ ያልሆነ የትጥቅ ግጭት ነው ለማለት እንችላለን፡፡ 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *