ትናንት ሚያዚያ 2/ 2014 ዓ.ም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን፣ ወልዲያ ከተማና አካባቢዎቹ በመከላከያ እና በፋኖ መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት በእርቅ መፈታቱ ተገለጸ። የዞኑ የኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ ኃብተማርያም አሰፋ ትናንት ምሽት በወልዲያ ተከስቶ በነበረው ግጭት አንድ ታጣቂ እና አንድ ሰላማዊ ሰው ሕይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል። የዞኑ የጸጥታ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም አምባዬ በበኩላቸው ግጭቱ የተነሳው በመከላከያ እና ፋኖ መካከል “ኬላ ላይ ተፈተሹ፣ አልፈተሽም” በሚል ምክንያት መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ ትናንት ማታ ምሽት 1፡00 አካባቢ የከባድ መሳሪያ ተኩስ እንደነበር ገልፀው፣ በዚህም አንድ ሰላማዊ ሰው ሕይወታቸው ማለፉንና ዛሬ የቀብር ሥነ ስርዓታቸውን እንደፈፀሙ ተናግረዋል። የዞኑ የጸጥታ ኃላፊ ኮሎኔል ኃይለማርያም በወቅቱ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር አረጋግጠው “መነሻው በፌስቡክ በሚናፈስ አሉባልታ ‘አንድ አመራር ታሰረብን’ በሚል ከሌላ ቦታ የመጡ ታጣቂዎች” ተኩሱን በመክፈታቸው የተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል። ይኹን እንጂ ግጭቱን ብዙም ሳይቆይ ማስቆም ተችሏል ብለዋል።

ኃላፊው ትናንት ምሽት በወልዲያ ከተማ በነበረው የተኩስ ልውውጥም የተጎዱ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጠው፣ ስለደረሰው ጉዳት ግን አጣርተው እንደሚገልጹ ተናግረዋል። የዞኑ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኃብተማርያም አሰፋ ” ‘መከላከያ፣ ልዩ ኃይልና ፋኖ ግጭት ፈጠሩ’ በሚል እኩይ ሥራ የሚሰሩ ይኖራሉ፤ የተፈጠረው ግን በአሰራር ክፍተት ነው” ብለዋል። ትናንት በዞኑ ጎብዬ እና ሮቢት አካባቢ የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኃብተማርያም “ግጭቱ የተፈጠረው በአካባቢው የነበረ የፋኖ መሪ ታስሯል በሚል እዚያ ያለው ፋኖ ሲመጣ መከላከያ ለማረጋጋት ሲሞክር ነበር” በማለት አስረድተዋል።

እንደ ኃላፊው ከሆነ በሁለቱ አካባቢዎች በነበረው ግጭት የደረሰ ጉዳት የለም። ይኹን እንጂ ትናንት ምሽት በወልዲያ ተከስቶ በነበረው ግጭት አንድ ታጣቂ እና አንድ ሰላማዊ ሰው ሕይወታቸው ማለፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ እንደሚያስረዱት፣ “በከተማዋ ፋኖዎች የሚኖሩበት ህንጻ የተኩስ ምልልስ ነበር፤ የጉዳት መጠን አላየንም። አንድ ቄስ ሞተዋል በአካባቢው ሲያልፉ የነበሩ ናቸው ተብሏል፤ እርሳቸውን ቀብረናል” ብለዋል። ይሰማ የነበረው የተኩስ ድምጽ ብዙም ሳይቆይ መቆሙን የገለጹት ነዋሪው የግጭቱ መንስኤ ግን ምን እንደሆነ በውል እንደማያውቁ ተናግረዋል። ዛሬ ወልዲያም፣ ሮቢትም፣ ጎብየም ሰላም መሆናቸውንና በአካባቢዎቹ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩንም ነዋሪው አክለዋል።

የኮሙኒኬሽን ኃላፊው አቶ ኃብተማርያም ደግሞ “በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችንና ጠላትን ለመመከት እንዲሁም ተላላኪዎችን ለመለየት የተለያዩ አሰራሮች ተዘርግተዋል፤ ያንን ለማጥራት የተጀመሩ ስራዎች ስለነበሩ፤ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ኃይሎች የራሳቸውን ሥራ ሰርተውበታል፤ ነገር ግን መከላከያ እና ፋኖ እንደተለያዩ ተደርጎ የሚወራው ፍፁም ሐሰት ነው” ብለዋል። “ፋኖ ለመከላከያ ደጀን ነው። መከላከያም ለፋኖ በግብዓትም በሬሽንም ግብዓት የሚያቀርብ ነው” በማለትም የተፈጠረው አለመግባባት በውይይት መፈታቱን ተናግረዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *