የፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር አዲስ አበባ መግባታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

ልዩ መልዕክተኛው የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ትናንት መጋቢት 12 መጀመራቸውን እና ዛሬ መጋቢት 13/2014 ዓ.ም. እንደሚያጠናቅቁ የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ባወጣው መግለጫ ገልጿል። አምባሳደር ሳተርፊልድ ትናንት ከአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን እና የሕብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላም እና ደኅንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶኦዬ ጋር በኢትዮጵያ እና በሱዳን ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

አምባሳደር ሳተርፊል በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከተባበሩት መንግሥት ድርጅት ባለሥልጣናት እና ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር እንደሚነጋገሩ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ ላይ ተመልክቷል። የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ የካቲት 06/2014 ዓ.ም. ለተመሳሳይ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው ይታወሳል።

ልዩ መልዕክተኛው በየተካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ በነበሯቸው የሁለት ቀናት ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች እና ከሰብዓዊ ድርጅት አስተባባሪዎች ጋር ተገናኝተዋል ተብሎ ነበር። ልዩ መልዕክተኛው የካቲት 6 ላይ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በውይይት ለመፍታት በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ንግግር ቀጥሏል ተብሎ የተገለጸበት ወቅት ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሐመድ ረቡዕ የካቲት 02/2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፤ “በአሁኑ ወቅት በእርግጠኛነት የተሻለ ቦታ ላይ ነን። ተጨማሪ ውይይቶችም አሉ” ብለው ነበር። ከተመድ ምክትል ዋና ፀሐፊ መግለጫ በፊት የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በህወሓትና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

አሁን ላይ የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በአዲስ አበባ የሁለት ቀናት ጉብኝት እያደረጉ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግሥት እና በህውሓት መካከል ንግግር እየተደረገ ስለመሆኑ በይፋ የተባለ ነገር የለም። አሜሪካ ጦርነቱ በድርድር መቋጫ እንዲያገኝ ልዩ መልዕክተኛ በመሰየም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ስታደርግ ቆይታለች።

ከጥቂት ወራት በፊት አምባሳደር ፌልትማንን በመተካት የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ስተርፊልድ ተደጋጋሚ ጉዞዎችን ወደ ምስራቅ አፍሪካ እና እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራትን አድርገዋል። ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስ ተከትሎ አሜሪካ በያዘችው አቋምና በወሰደቻቸው እርምጃዎች ምክንያት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የነበረው መልካም ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል።

የአሜሪካ መንግሥት ጦርነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትን ጨምሮ በጦርነቱ ተሳታፊዎች ላይ የቪዛ እገዳ የጣለ ሲሆን፣ እንዲሁም ከሳምንታት በፊት ተግባራዊ የሆነው ኢትዮጵያ ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ ምርቶችን ወደ አሜሪካ ታስገባበት የነበረው የአጎዋ ተጠቃሚነት የእገዳ እርምጃ ወስዷል። ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ ላይ እንዲሁም ከግጭት ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሶች ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ረቂቅ ሕግ አስተዋውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትም አሜሪካ ለአማጺያኑ የሚያደላ መግለጫ እየወጣች እና እርምጃ እየወሰደች ነው በማለት አሜሪካን በወገንተኝነት ሲከስ ቆይቷል።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *