የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ጭና እና ቆቦ በተባሉ አካባቢዎች በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ መግደላቸውን የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ሂዩማን ራይትስ ዋች አስታወቀ።

ድርጅቱ እንዳለው በሁለቱ ስፍራዎች ግድያው የተፈጸፀመው ባለፈው ዓመት ከነሐሴ 25 አስከ ጳጉሜ 04/2013 ዓ.ም. በነበሩት አስር ቀናት ውስጥ መሆኑን ገልጿል። በመጀመሪያ የህወሓት ኃይሎች ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም ጭና ወደተባለችው መንደር በመግባት ከፌደራል ሠራዊትና ከአማራ ኃይሎች ጋር ውጊያ ካካሄዱ በኋላ ቦታውን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት በነበሩ አምስት ቀናት በ15 የተለያዩ ስፈራዎች 26 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በቆቦ ከተማ ጳጉሜ 04/2013 ዓ.ም በአራት የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የትግራይ ኃይሎች 23 ሰዎችን እንደገደሉ የዓይን ምስክሮች ለሂዩማን ራይትስ ዋች የገለጹ ሲሆን፤ ግድያውን የአካባቢው አርሶ አደሮች በህወሓት ኃይሎች ላይ ለፈጸሙት ጥቃት የወሰዱት የበቅል እርምጃ ነው ብሏል። “የትግራይ ኃይሎች በጥበቃቸው ስር ያሉ ሰዎችን በመግደል ለሰው ህይወትና ለጦርነት ሕግጋት ጭካኔ የተሞላበት ግድየለሽነት አሳይተዋል” ሲሉ የሂማን ራይትስ ዋች የቀውስና የግጭት ጉዳዮች ዳይሬክተር ላማ ፋኪህ ስለግድያዎቹ ተናግረዋል።

ጨምረውም “እነዚህ በኢትዮጵያ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች ውስጥ በተካሄዱ ግጭቶች በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ ግድያዎችና ጭፍጨፋዎች ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ምርመራ እንደሚያስፍልግ ያመለክታሉ” ብለዋል። ባለፈው ዓመት ትግራይ ውስጥ በተጀመረው ጦርነት የኢትዮጵያ ሠራዊት ከኤርትራ ሠራዊት እና ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዲሁም ሚሊሻዎች ጋር በመሆን ከህወሓት ጎን ከተሰለፉ የትግራይ ታጣቂ ቡድን ጋር ሲዋጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ሂዩማን ራይትስ ዋችን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በዚህ ጦርነት ትግራይ ውስጥ በሁሉም ኃይሎች በሰብአዊነት ላይ ወንጀሎችና የጦር ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው የተለያዩ መረጃዎችን ሲያወጡ ቆይተዋል። በሐምሌ ወር ወደ አማራ እና አፋር ክልል የተስፋፋው ጦርነቱ በርካታ ሰዎችን እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን፣ በአማራ ክልል ብቻ 3.7 ሚሊዮን ሰዎች ለእርዳታ ጠባቂነት ተዳርገዋል። ሂዩማን ራይትስ ዋች በመስከረም እና በጥቀምት ወር ላይ በጭና ተክለሐይማኖት መንደርና ቆቦ ከተማ ውስጥ ስለተካሄደው ውጊያና የተከሰተውን ለማወቅ ግድያዎቹን ያዩ እማኞችን፣ የሟች ዘመዶችንና ጎረቤቶችን፣ የሐይማኖት አባቶችንና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ 36 ሰዎችን ከርቀት ቃለመጠይቅ ማድረጉን ገልጿል።

ከእነዚህ ውስጥም 19ኙ ጭና እና ቆቦ ውስጥ የትግራይ ኃይሎች በአጠቃላይ 49 ሰለማዊ ሰዎችን ሲገድሉ ማየታቸውንና ከሟቾቹም የ44ቱን ሰዎች ስም መጥቀሳቸውን ገልጾ፣ በተጨማሪም የሟቾቹን ቁጥር ከፍ የሚያደርግ የስም ዝርዝር ማግኘቱን አመልክቷል። በሐምሌ አጋማሽ ላይ ቆቦን የተቆጣጠሩት የትግራይ ኃይሎች ጳጉሜ 04/2013 ዓ.ም ከቆቦ አቅራቢያ ወዳሉ መንደሮች በመሄድ መሳሪያ መፈለግ በጀመሩበት ጊዜ በአርሶ አደሮች ጥቃት ተሰንዝሮባቸው ውጊያ ተካሂዶ ነበር። ከዚያም ወደቆቦ ሲመለሱ እርሻቸው ላይ ሲሰሩ የነበሩ አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ሪፖርቱ አመለክቷል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በቆቦ እና በጭና ውስጥ በህወሓት ኃይሎች ስለተፈጸመው የሰለማዊ ሰዎች ግድያ በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት ላይ ዝርዝር ምስክርነትን አካቷል። በሁለቱ ስፍራዎች በህወሓት ኃይሎች ተፈጸሙ የተባሉትን የሰላማዊ ሰዎች ግድያዎችን በተመለከተ የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎችና ባለሥልጣናት ቀደም ሲል እንደተናገሩት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መገደላቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። ከህወሓት መሪዎች አስተያየታቸውን ለማግኘት ይህንን ሪፖርት መላኩን የገለጸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ምንም ምላሽ እንዳላገኘ ገልጿል።

ከዚህ በፊት በህወሓት ኃይሎች ተፈጸሙ የተባሉ የጅምላ ጥቃቶችና ግድያዎችን ተከትሎ የቡድኑ አመራሮች በሰጡት ምላሽ ኃይሎቻቸው እንዲህ አይነቶቹን ድርጊቶች እንደማይፈጽሙ በማስተባበል በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ ሲጠይቁ ነበር። አንድ ዓመት ባለፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን በሚመለከት የተለያዩ የመብት ተሟጋቾችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል።

በትግራይ ውስጥ ተፈጸሙ ስለተባሉ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ያደረጉት የምርመራ ውጤት በቅርቡ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *