ከትግራይ ክልል ጋር ወደ ሚዋሰነው የአፋር ክልል ገብተው የነበሩት የህወሓት አማጺያን ተሸንፈው ከክልሉ መውጣታቸው ተነገረ።

የፌደራሉ መንግሥትና የአፋር ክልል እንዳሉት ከሐምሌ ወር ወዲህ ወደ አፋር ክልል የገባው የአማጺው ቡድን ኃይል በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊትና በክልሉ ልዩ ኃይል በተወሰደበት እርምጃ ሽንፈት ገጥሞት ከአፋር ክልል እንዲወጣ ተደርጓል። የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ተዋጊዎቻቸው ከአፋር የወጡት ተሸንፈው ሳይሆን ወደሌላ ስፍራ እንዲሰማሩ ተፈልጎ እንደሆነ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አማባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ሐሙስ ረፋድ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት በተወሰደ እርምጃ አማጺው ኃይል ከክልሉ መውጣቱን አመልክተዋል። አምባሳደር ዲና የህወሓት አማጺያን ከአፋር ክልል “ባለን ወታደራዊ መረጃ መሠረት በተወሰደ ወታደራዊ እርምጃ ተሸንፎ ወጥቷል” ሲሉ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ህወሓት ከአፋር ክልል በራሱ ለቆ የወጣው በመከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ ልዩ ኃይል በተወሰደ እርምጃ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል። የአፋር ክልልም እንዲሁ አማጺው ይዟቸው ከነበሩ የክልሉ አካባቢዎች በተከታታይ የተደረጉ ውጊያዎችን ተከትሎ እንዲወጡ መደረጋቸውን በተመለከተ ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ይፋ ሲያደርግ ቆይቷል።

የአፋር ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮ እንዳለው የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረውት ነበሩ ካለው ፈንቲ ረሱ ከሚባለው የክልሉ አካባቢ ሙሉ በሙሉ እንዲወጡ መደረጋቸውን አመልክቷል። ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ተዋጊዎቻቸው ከክልሉ መውጣታቸውን አረጋግጠው ነገር ግን የወጡት ሽንፈት ግጥሟቸው እንዳልሆነ መናገራቸውን ዘግቧል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ካልተጠቀሰ ቦታ በሳተላይት ስልክ ለሮይተርስ “አልተሸነፍንም። በአፋር ክልል ግጭት አልነበረም ስለዚህ የወታደሮች እንቅስቃሴ ከዚያ ወደ አማራ ክልል ተራራማ ስፍራዎች አንቀሳቅሰናል” ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ህወሓት ተዋጊዎቹን ከአማራ እና አፋር አካባቢዎች ማስወጣቱን በትግራይ ቴሌቪዥን አስነግሯል።

ትግራይ ቴሌቪዥን ላይ በተላለፈው መግለጫ ህወሓት ወታደሮች አካባቢዎቹን ለቀው የወጡት የፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪሎችን በጦርነቱ እንዲሳተፉ በማሰማራቱ ነው ብሏል። የፌደራሉ መንግሥት ባለፈው ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች ጥቃት በመሰንዘር በአፋር እና በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን መያዛቸው ይታወሳል።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሎች ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ሚሊሻዎች የህወሓት ኃይሎች ይዘው ከቁባቸው አካባቢዎች ለማስወጣት ከፍተኛ ጦርነት ሲካሄዱ እንደነበር ሲዘገብ ቆይቷል። በዚህም የፌደራሉ መንግሥት የተለያዩ ድሎችን እያስመዘገበ እና ቦታዎችን እየተቆጣጠረ መሆኑን እንዲሁም የህወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው ከነበሩ ቦታዎች ሲለቁ በንጹሃን ላይ ጥቃት መፈጸማቸውንና ንብረት መውደም መዝረፋቸውን ገልጿል።

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ወረዳ ጭና በሚባል አካባቢ የህወሓት ታጣቂዎች ከ120 በላይ ንፁሃን ሰዎችን ስለመግደላቸውን ነዋሪዎችና የወረዳው ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ህወሓት በበኩሉ በወታደሮቹ ተፈጸመ የተባለውን የጅምላ ግድያ ክስን “ሐሰት” ሲል አስተባብሏል።

የትግራይ ጦርነት ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ

በህወሓት እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተነሳው ጦርነት አስረኛ ወሩን ያስቆጠረ ሲሆን ወደ አጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልሎች ተዛምቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ አደጋ አጋልጦ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ አፈናቅሏል። የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች በአጠቃላይ እስከ 7 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሃብ ቀውስ ሊጋለጡ ይችላሉ ብሎ ነበር።

ድርጅቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት በአማራ እና አፋር ክልሎች ወደ 1.7 ሚሊዮን ሰዎችን ለረሃብ አደጋ ሲያጋልጥ ወደ 300ሺህ የሚጠጋ ሕዝብን ደግሞ ከመኖሪያ ቀዬው አፈናቅሏል ይላል። በትግራይ ደግሞ ወደ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ሲል ድርጅቱ አስታውሷል። የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *