በኢትዮጵያ የተከሰቱ እና የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መነሻ አገሪቱ ያለችበት የፖለቲካ ቀውስ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ዶ/ር ዳንኤል አክለውም አገሪቱ ለገባችበት ችግር መፍትሔ መፈለግ ባለመቻሉ ለበርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ሆኗል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመሆን እየመረመረ መሆኑ ይታወቃል። በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ብሔር ተኮር ግጭቶች፣ መፈናቀሎች እንዲሁም ግድያዎች የደረሱ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በርካታ ፖለቲከኞች እና ግለሰቦች በእስር ላይ ይገኛሉ።

ዶ/ር ዳንኤል፤ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ያለው የተካረረ ፖለቲካ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ማጋለጡን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ ውስብስብ መሆኑ፣ በበርካታ ስፍራዎች የሚነሳ ግጭት ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት ማስከተሉ፣ መፈናቀል መብዛቱ፣ እና የንብረት ውድመት መኖሩ የችግሩን መጠን አብሶታል ሲሉ ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ ቀውስ ሳቢያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ግጭቶች ለሰው ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀል እንዲሁም ንብረት መውደም ምክንያት መሆናቸውን አስታውሰዋል። ይህ ግጭት በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም አለመብረዱን የሚናሩት ኮሚሽነሩ፤ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ መሆኗን ይናገራሉ። በአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል የሚረዱ መልካም እርምጃዎች ቢወሰዱም “የፖለቲካ እና የሰብዓዊ መብት ቀውሳችን ግን ገና ብዙ ይቀረዋል” ብለዋል።

በትግራይ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ

በትግራይ ክልል የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በጥምረት እየመረመሩ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውሰዋል። ከኮሚሽኑ እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በሥራ ላይ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች፣ የመንግሥት አስተዳደሮች እና ሌሎችም የመረጃ ምንጮችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እንዲሁም ልዩ ልዩ ማስረጃዎችን እንደሚሰበስቡ አብራርተዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ከዚህ በኋላ የተሰበሰቡትን መረጃዎች ከዓለም አቀፍ እና ከኢትዮጵያ ሕግ አንጻር የመተንተን ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ሥራው ሲጀመር የነበረው እቅድ ይህንን ምርመራ በሦስት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደነበረ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ነገር ግን አንዳንድ ስፍራዎች በሚታሰበው ፍጥነት መድረስ ባለመቻሉ መዘግየት መፈጠሩን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በጥምረት የያዘውን የማጣራት ሥራ እስከ ነሐሴ እና መስከረም ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዳንኤል፤ ነባራዊ ሁኔታዎች የማያግዱ ከሆነ በዚህ እቅድ መሠረት ለማጠናቀቅ እየሠራን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በትግራይ ስላለው የረሃብ ሁኔታ ሲናገሩም፤ የተባበሩት መንግሥታት ያሰማው የማስጠንቀቂያ ደወል የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ በአንክሮ ሊወሰዱት የሚገባው መሆኑን አስረድተዋል። ኮሚሽኑ በትግራይ ካስተዋላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በሆስፒታሎች አካባቢ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን መሆኑንም አንስተዋል።

በኦሮሚያ ሕግን የማስከበር እርምጃ

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ያለው የእስረኞች ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገልጾ ነበር። ኮሚሽኑ በጎበኛቸው የፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው መሆኑንም ገልጾ ነበር። በኦሮሚያ ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ የታሰሩ እንዲሁም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት መለቀቅ የነበረባቸው ነገር ግን ያለ አግባብ ታስረው እንዲቆዩ የተደረጉ እንዳሉ ገልጾ ነበር።

ይህንን ተከትሎም የክልሉ ፖሊስ ተቃውሞውን አሰምቶ ያውቃል። ኦሮሚያ ሰፊ ክልል እንደሆነ፣ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩበት እና ታጣቂዎች ከፍተኛ ፈተና የጋረጡበት ክልል መሆኑን እንገነዘባለን ይላሉ ዶ/ር ዳንኤል። በኦሮሚያ ክልል በሰብዓዊ መብት አያያዝ “አሳሳቢ አዝማሚያዎች አሉ” ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በክልሉ የታጠቁ አማፂያን በንፁሀን ዜጎች ላይ የሚያደርሱትን የደኅንነት ስጋት እና በመንግሥት የፀጥታ አካላት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት እንደሚረዱ ይናገራሉ።

በኦሮሚያ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የታሰሩ ሰዎች ስለመኖራቸው፣ በእስር ላይ ሳሉ ድብደባ የደረሰባቸው ሰዎች እንደሚገኙ እና ተመጣጣኝ ባልሆነ የኃይል አጠቃቀም ሕይወታቸው የጠፋ ሰዎች እንዳሉም ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም የታጠቁ ሰዎች በወሰዷቸው እርምጃዎች ሕይወታቸው የተቀጠፈ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አብራርተዋል።

በኦሮሚያ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያለመከበር ችግር መግጠሙን ያስታወሱት ዶ/ር ዳንኤል፤ እንዲህ አይነት ችግሮች በሌሎች አካባቢዎችም ቢገጥሙም ኦሮሚያ ሰፊ ከመሆኑ እንዲሁም በርካታ ቅሬታዎች ቀርበው ስለነበር የተለየ ትኩረት አድርገው መሥራታቸውን ገልጸዋል። ከኦሮሚያ ባለሥልጣናት ጋር በመቀራረብ መነጋገራቸውን ያስታወሱት ኮሚሽነሩ፤ “አልፎ አልፎ ከተወሰኑ ኃላፊዎች ቀና ያልሆነ ምላሽ ይሰጠናል” ብለዋል። በዚህም የተነሳ በሁሉም የክልሉ ኃላፊዎች ዘንድ ባይሆንም አልፎ አልፎ ሥራቸውን እና የምርመራ ውጤታቸውን ያለመቀበል አዝማሚያ ማየታቸውን አክለዋል።

ኮሚሽኑ ነጻና ገለልተኛ ነው?

ዶ/ር ዳንኤል የኮሚሽኑን ሥልጣን ከተረከቡ ጊዜ አንስቶ ምንም ኣይነት የመንግሥት ተጽዕኖ ኖሮባቸው እንደማያውቅ፤ ቢኖርባቸውም እንደማይቀበሉ በመናገር “ሙሉ በሙሉ ነጻ” መሆናቸውን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ እና ውስብስብ የሰብዓዊ መብቶች ችግር መኖሩን የሚገልጹት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል፤ ኮሚሽኑ ባለው አቅም ከማንኛውም ወገን ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ እየሠራ መሆኑን ይናገራሉ።

ለኮሚሽኑ መለወጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ምክንያት ነው የሚሉት ኮሚሽነሩ፤ በመንግሥት ዘንድ ኮሚሽኑን ነጻና ገለልተኛ የማድረግ ፈቃደኝነት እና ቁርጠኝነት በመኖሩ ይህንን ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን በመንግሥት ዘንድ ያለ ፈቃደኝነት እና ቁርጠኝነት በመጠቀም ኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጁን ማሻሻል፣ የኮሚሽነሮች አመራረጥና አሰያየም ሂደትን ማሻሻል፣ የተቋቋመበትን ዓላማና ተግባር ሰፋ ማድረግ እና ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ ለመሆን የፋይናንስ እና የተቋም አስተዳደር ነጻ እንዲሆን ድንጋጌዎች እንዲካተቱ የማድረግ ሥራ መሰራቱን ይናገራሉ። የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ይናገራሉ።

የኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቦች ተቀባይነት

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎች የጠቆማቸው የማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች አልፎ አልፎ ተቀባይነት ሲያገኙ መመልከቱን ያነሱት ኮሚሽነሩ፤ “እርምጃ ሲወሰድ፣ ማሻሻያ ሲደረግ እንመለከታለን” ቢሉም ነገር ግን ያልተሻሻሉ ነገሮችን ማስተዋላቸውንም ገልጸዋል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ምርመራ አድርጎ፣ በፍርድ ቤት ጭምር የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ከእስር ሊለቀቁ እንደሚገባ የተወሰነላቸው ነገር ግን አሁንም ድረስ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች እንዳሉ ዶ/ር ዳንኤል ይናገራሉ።

ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የታሰሩ፣ ለሕይወት መጥፋት ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው ቡድኖች እንዲሁም ተጣርቶ እርምጃ ያልተወሰደባቸው መኖራቸውንም አስረድተዋል። የፍርድ ቤት ውሳኔ አለማክበር በተደጋጋሚ የተስተዋለ ችግር መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ የፍርድ ቤት ውሳኔን አለማክበር “በምንም አይነት ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው አሠራር ነው” ሲሉ ይናገራሉ።

አክለውም ምንም እንኳ በጥቂቱም ቢሆን መሻሻል የታየ ቢሆንም “ገና ሙሉ በሙሉ መፍትሔ ያላገኘ ችግር መሆኑን በመጥቀስ “መቅረት ያለበት ተገቢ ያልሆነ አሠራር” ነው ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ያሉበት ተግዳሮቶች

እንደ ዶ/ር ዳንኤል ገለጻ ከሆነ ኮሚሽኑ ካሉበት በርካታ ተግዳሮቶች መካከል ቀዳሚው ያለፈ ታሪኩ ነው። ከዚህ ቀደም ይህ ተቋም በነጻነት እና በብቃት ሲሠራ የነበረ ተቋም ባለመሆኑ ተቋማዊ ብቃት የለውም ይላሉ። ይህ ደግሞ በውስን የሰው ኃይል፣ የቴክኖሎጂ እና የሥራ ስልቶችን በአግባቡ ባለመጠቀም የሚገለጽ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። የሰው ኃብት እና የገንዘብ ውስንነት የተቋሙ ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ዶ/ር ዳንኤል ይገልጻሉ።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የበጀት ውስንነት መኖሩ በሚገባ እንዳይሠሩ እንቅፋት ሆኗል። በአገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ችግር የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በጣም የተስፋፋ እንዲሆን ስላደረገው ራሱን የቻለ ፈተና ሆኗል ሲሉም ያብራራሉ። በአገር ውስጥ የተፈጠረው የተለጠጠ ዋልታ ረገጥ የሆነ ፖለቲካ ለሰብዓዊ መብት ሥራ ፈተና መሆኑን ይናገራሉ።

ጫፍና ጫፍ ይዞ የተካረረው የፖለቲካ አስተሳሰብ በብሔር ማንነት ላይ የተቃኘ በመሆኑ በአገር ውስጥ የሚካሄድ ማንኛውም ሥራ እና እንቅስቃሴ በዚያ መነጽር ይታያል ሲሉም ገልጸዋል። የሰብዓዊ መብት ሥራንም በዚያ መነጽር የማየት አዝማሚያ እንደሚስተዋል ዶ/ር ዳንኤል ያስረዳሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሰብዓዊ መብት መስፋፋት፣ መከበርና መጠበቅ የሚሠሩ ተቋሞች ሥራቸው በዚህ መነጽር እየታየ ፈተና እየሆነ መጥቷል ይላሉ።

ዶ/ር ዳንኤል አክለውም በኢትዮጵያ የመንግሥት አስተዳደር ታሪክ የመንግሥት ኃላፊዎችን እና የፀጥታ ኃላፊዎችን በነጻ እና ገለልተኛ ተቋም የመጠየቅ ልምድ አልነበረም ይላሉ። ስለዚህ አሁን የመንግሥት ሥራ ነጻና ገለልተኛ በሆኑ ተቋሞች ተመርምሮ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሲጋለጡ፣ የአጥፊዎች ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ጫና ሲፈጠር ወይም ደግሞ ምክረ ሐሳብ ሲሰጥ “ገና እየተለማመድነው ያለነው ሐሳብ ስለሆነ በተወሰኑ የመንግሥት ኃላፊዎች ዘንድ በጎ ያልሆነ ምላሽ እናገኛለን” ሲሉ ያብራራሉ።