በተመዱ OHCHR፣ በተመዱ የልማት ፕሮግራም (UNDP)፣ እንዲሁም በኦስትሪያ፣ በዴንማርክ፣ በኖርዌይ እና በስዊድን ኤምባሲዎች ትብብር በተዘጋጀው በዚህ መድረክ የተለያዩ የውይይት መነሻ ጽሑፎች እና ጥናቶች ቀርበዋል።
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች (EHRD) ዳይሬክተር፣ አቶ አበራ ኃይለማርያም በምርጫ ዙርያ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ጥምረት (CECOE) አስተባባሪ እንዲሁም የኢሰመኮ ከፍተኛ ባለሞያዎች ከዚህ ቀደም በነበሩ ሀገራዊ ምርጫ ከነበሩ ልምዶች በማጣቀስ በተፈናቃዮች፣ በሴቶች እና በአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ዙሪያ እንዲሁም የተሻለ የሲቪክ ማኅበራት ቅንጅት ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ጽሑፎች አቅርበዋል።
በምርጫ እና በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማኅበራትን የሚያሰባስበው ይህ መድረክ ከነሃሴ ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ሁለት የምክክር እና የውይይት መድረኮች አዘጋጅቷል።
“የዚህ የምርጫ ቅስቀሳቸው አካል መሆን አለበት ብለን የምናስበው የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ውስብስብ ጥልቅ የሆነ የሰብአዊ መብቶች ቀውስ አለ፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው አሸንፈው የሚመረጡ ቢሆን በሰብአዊ መብት ረገድ ምን ቃል እንደሚገቡ ማድመጥ እንፈልጋለን” – የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)
ለአንድ ቀን የቆየው እና በተለይም የሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ሰብአዊ መብቶችን ያማከለ እንዲሆን በሚለው ርዕስ ያተኮረው ሦስተኛው የምክክር መድረክ የሲቪክ ማኅበራቱን የ“2013 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ ስራ ዕቅድ”ን ተወያይቶ በማጽደቅ ተጠናቅቋል።