ለዘመናት በጋዜጦች፣ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮዎች በበላይነት ተይዞ የነበረውንም የመረጃም ሆነ የዜና ምንጭነት ቀይረውታል።

በግለሰብ ደረጃ የተለያዩ ዜናና መረጃዎችን በጽሑፍ፣ በምስልና በቪዲዮ ለበርካታ ሰዎች ለማድረስ ዕድልን ፈጥረዋል።

በዚህም መረጃዎች በቀላሉና በአጭር ጊዜ አገራትን ብቻ ሳይሆን አህጉራትን አቆራርጠው ከበርካቶች ዘንድ ይደርሳሉ።

ነገር ግን በዚህ ሂደት ይህንን የግንኙነት ዘዴ ለዕውቀትና ለበርካታ መልካም ነገሮች ከሚያውሉ ሰዎች ባሻገር ሐሰተኛ ወሬን፣ ጥላቻን፣ ጥርጣሬና ፍርሃትን እንዲሁም ለሥነ ምግባር ተቃራኒና ለሰዎች ደኅንነት አደገኛ የሆኑ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ቡድኖችና ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው።

ይህንንም ለመከላከል የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮቹ ባለቤት የሆኑት ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ የመገናኛ ዘዴዎቻቸውን ከእንዲህ አይነቶቹ መልዕክቶች በተቻለ መጠን ነጻ ለማድረግ የአጠቃቀም ደንቦችን በማውጣት ቁጥጥር እያደረጉ ነው።

በዚህም ሳቢያ ለሰዎች ደኅንነት ጎጂ የሆኑና ሐሰተኛ ወሬዎችን በሚያሰራጩ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ለመውሰድ እየተገደዱ ነው።

ፌስቡክ

ፌስቡክ ከጥቂት ወራቶች በፊት የጥላቻ ንግግር ወይንም ሐሰተኛ ንግግሮች ናቸው ያላቸውን 22 ሚሊዮን በላይ መረጃዎችን አጥፍቷል።

ድርጅቱም ይህንን የሚያደርገው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባቋቋማቸው ማዕከላት ነው።

ይህንንም አማርኛንና ኦሮምኛን ጨምሮ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ቋንቋዎች ላይ ክትትል የሚደረገው ኬንያ ባለው ቢሮ በኩል ነው።

የ’ዊ አር ሶሻል’ እና ፌስቡክ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ በወር አንዴ ፌስቡክን የሚጠቀሙት ሰዎች ቁጥር ከስድስት ሚሊዮን በላይ ነው።

የፌስቡክ የምስራቅ አፍሪካ የማህበራዊ ጉዳዮች ፖሊሲ ኃላፊ የሆነችው ሜርሲ ኢንዴጊዋ “ለፌስቡክ ኢትዮጵያ የማሕበራዊ ሚዲያ ገበያ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላት አገር ናት” ትላለች።

ፌስቡክ በአካባቢው ብዙ ስራዎች እየሰራ ነው የምትለው ሜርሲ፣ ኢትዮጵያ የሚገኙት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አብዛኞቻቸው ዜናንና ሌሎች ክስተቶችን ለማግኘት ወደ ገጻቸው እንደሚመጡ ትናገራለች።

“በተጨማሪም በኢትዮጵያ የእኛ ትኩረት ሰዎች በኛ ፕላትፎርም (መድረክ) እንዴት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፣ ከዚያን በኋላ ደግሞ ኢንተርኔት በማይጠቀሙበት ጊዜ በሚያሳዩት ባህሪ ላይም ትኩረት እንሰጣለን” ብላለች።

ይህም ማለት የጥላቻ ንግግር፣ የሐሰተኛ መረጃ እና ሌሎች ይዘቶችን ለመቆጣጠር እንዲሁም መፍትሔ ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ተናግራለች።

የፌስቡክ ማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች፣ በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚጠቀሙ ግለሰቦች፣ በተደጋጋሚ የሚለጥፏቸው መረጃዎች መሰረዙን በመጥቀስ ቅሬታ ያቀርባሉ።

የተወሰኑ ግለሰቦች ፌስቡክ የአንድ አካል መሳሪያ ነው በማለት ሲተቹ፣ ሌሎች ደግሞ በማንነታቸው ምክንያት ትኩረት ውስጥ እንደገቡ ያምናሉ።

አንዳንድ ጊዜ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ እንዲሁም የአንድ ቋንቋ ቡድን አንድ ላይ በመደራጀት ሌሎች ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።

 

ፌስቡክ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የሐሰተኛ መረጃዎች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣  እንዲሁም በማንነት ላይ ያተኮሩ መረጃዎች በሚለጠፉበት ወቅት እንዴት ይቆጣጠራል?

በድርጅቱ የይዘት ጉዳዮች ኃላፊ (ኮንቴንት ፕሪንሲፕል) ኃላፊ የሆነችው ፈድዛይ ማድዚንጊራ አንድ መረጃ ከፌስቡክ ላይ የሚሰረዘው የተቀመጠውን የማህበረሰብ መስፈርት (ኮሚውኒቲ ስታንዳርድ) ተላልፎ ሲገኝ ነው በማለት ታስረዳለች።

ይህም ፖሊስ በፌስቡክ ገጽ ላይ በግልጽ የሚገኝ በመሆኑ ማንኛውም ሰው አግኝቶ ማንበብ ይችላል የምትለው ፈድዛይ፣ በዚህ መስፈርት ስር በድርጅቱ መተግበሪያ ላይ የሚፈቀዱ እና የማይፈቀዱ ነገሮች በግልጽ መቀመጣቸውን ታስታውሳለች።

“እነርሱም በ26 አበይት ርዕሶች ተከፋፍለው የሚገኙ ናቸው፣ ለዕይታ የሚረብሹ (ግራፊክ ኮንቴንት) የሆኑ ምስሎች ከተለጠፈው ነገር ጋር ሲጋጩ እንዲሁም መልካም ያልሆነ ባህሪ፣ እስከ ጥላቻ ንግግር ድረስ በዝርዝር ይዟል። የፌስቡክ የጥላቻ ንግግር ፖሊሲ ዓላማ ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ትኩረት ተደርጎ የሚለጠፉ መረጃዎችን ማጥፋት ነው” ትላለች።

በተጨማሪም ሰዎች በማንነታቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው ከሆነ በሚል ይህ ፖሊሲ ማስፈለጉን ታብራራለች።

አንድ መረጃ ከፌስ ቡክ ላይ የሚሰረዝበት ቅድመ ሁኔታ ስታነሳ፣ “ለምሳሌ እኔ የዚምባብዌ ዜጋ ነኝ። እና አንድ መረጃ፣ እኔ ከዚምባብዌ ስለመጣሁ አልያም ጥቁር ስለሆንኩ፣ ወይንም ሴት በመሆኔ እኔ ላይ ትኩረት አድርጎ ያስፈራራኛል ወይንም የጥላቻ ንግግር ይለጥፋል ከሆነ ይህንን እናጠፋለን።”

ማንኛውም ሰው ማመልከት ይችላል

ማንኛውም የፌስቡክ ተጠቃሚ ስለ አንድ የፌስቡክ መረጃ ሪፖርት ማድረግ ወይንም ማመልከት ይችላል።

“አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ይህንን ማድረግ እንደማንችል ነው የሚወስዱት” የምትለው ኃላፊዋ፣ አንድ መረጃን ብቻ የተመለከተ ጉዳይ ሪፖርት ማድረግ፣ የግለሰብ ወይንም ገጽን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሪፖርት ማድረግ እንደሚቻል ለቢቢሲ አስረድታለች።።

 

2

የሰዎችን ማንነት የሚለየው ቴክኖሎጂ እያከራከረ ነው

በአንድ ምስል ወይም ቪድዮ ላይ ያሉ ሰዎችን ማንነት የሚለየው ፌስ ሪኮግኒሽንቴክኖሎጂ አሁንም እያከራከረ ነው።

አማዞን ‘ሪኮግኒሽን’ በሚል ስያሜ የሠራው የ ‘ፌስ ሪኮግኒሽን’ ቴክኖሎጂ ለአሜሪካ ፖሊሶች መሸጥ አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ጉዳይ የአማዞን ባለድርሻዎች መካከል አለመግባባት ፈጥሯል።

ባለድርሻዎቹ በአማዞን ዓመታዊው ጉባኤ ላይ ምርጫ በማድረግ ውሳኔ እንደሚያሳልፉም ይጠበቃል።

ባለድርሻዎቹ፤ አማዞን ‘ሪኮግኒሽን’ን ለመንግሥት ተቋማት መሸጥ አለበት? ቴክኖሎጂው የሰዎችን ሰብአዊ መብት ስላለመጋፋቱ በገለልተኛ ወገን ይጠና? የሚሉ ሁለት ጉዳዮች ላይ ምርጫ ያደርጋሉ።

አማዞን ምርጫው እንዳይካሄድ ለማድረግ ቢሞክርም የማስቆም መብት ስለሌለው አልተሳካለትም።

ሜሪ ቤት ጋልጋር የተባሉ ባለሙያ ለቢቢሲ፤ ” ‘ሪኮግኒሽን’ ለመንግሥት ተቋሞች መስጠት የሚያስከትለው ተጽዕኖ ሳይጠና እንዳይሸጥ እንፈልጋለን። ውሳኔውን ለማሳለፍም ባለሀብቶች እንደሚያግዙን እናምናለን” ብለዋል።

 

ቴክኖሎጂው መቶ በመቶ ትክክለኛ መረጃ እንደማይሰጥ ጠቅሰው፤ ጥቅም ላይ ሲውል የሰዎችን መብት ተጋፍቶ እንደሚሰልል ተናግረዋል። “ሰዎች፣ ፖሊሶች እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን እየተመለከቱና እየተከታሏቸው እንደሆነ ከተሰማቸው በነጻነት አይንቀሳቀሱም” ብለዋል።

 

አማዞን በበኩሉ ‘ሪኮግኒሽን’ ያለአግባብ ጥቅም ላይ ውሏል የሚል ሪፖርት ቀርቦ ስለማያውቅ ባለድርሻዎች እንዲደግፉት ጠይቋል።

ድርጅቱ በመግለጫው እንዳሳወቀው፤ ቴክኖሎጂው ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ያግዛል። “የጠፉ ሰዎች እንዲገኙ ይረዳል። ወንጀል መከላከልም ይቻላል። ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ብሎ አዲስ ቴክኖሎጂ ማጣጣል ተገቢ አይደለም” ተብሏል።

 

ወደ 20 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች መረጃ ያለው ቴክኖሎጂው፤ በምስልና ቪድዮ ላይ የታየ ሰውን ማንነት ለማወቅ ያስችላል። የሰዎችን ጾታ ይለያል። ምስል ላይ ያለ ጽሁፍ እንዲተነተንም መረጃ ያቀብላል።

ሆኖም በኤም አይ ቲና ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቶሮንቶ የተሠሩ ጥናቶች፤ ቴክኖሎጂው ሰዎችን በጾታቸውና በቆዳ ቀለማቸው የሚያገል መሆኑን ይጠቁማሉ። ቴክኖሎጂው የነጭ ወንዶችን ማንነት በቀላሉ ለማወቅ ቢረዳም ስለጥቁር ሴቶች ትክክለኛ መረጃ አይሰጥም።

አማዞን እነዚህ ጥናቶች የተሠሩት ቀድሞ በነበረው ቴክኖሎጂ እንደሆነና አሁን መሻሻሉን ይገልጻል። ቢሆንም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የአማዞን ሠራተኞችም ቴክኖሎጂውን ይቃወማሉ።

3

ኮሮናቫይረስ፡ አንዳንዶች በኮሮናቫይረስ ሌሎች ደግሞ በሐሳዊ ዜና ወረርሽኝ እየሞቱ ነው

 

የማኅበራዊ ሳይንት ተመራማሪዎች ሐሳዊ ዜና፣ መላምታዊ ድምዳሜ፣ የሴራ ወሬ ብዙዎችን ዋጋ እያስከፈለ ነው ብለው ይደመድማሉ። ምን ያህል እውነት ነው?

አሁንም ድረስ ኮሮናቫይረስ አውሮፓዊያን የሸረቡት ሴራ እንጂ እውነት አይደለም ብለው የሚያምኑ ሺህዎች ናቸው። አሁንም ድረስ ኮሮናቫይረስን የወለደው 5ጂ ኔትዎርክ ነው የሚሉ አሉ። አሁንም ድረስ ‘አረቄ ኮሮናቫይረስን ድራሹን ያጠፈዋል’ ብለው ጉሮሯቸው እስኪሰነጠቅ የሚጨልጡ በርካቶች ናቸው።

ከኢትዮጵያ እስከ ማዳጋስካር፣ ከታይላንድ እስከ ብራዚል፣ ከአሜሪካ እስከ ታንዛኒያ በሐሳዊ ወሬ ያልናወዘ፣ መድኃኒት ያልጠመቀ የለም።

ሳይንስ መፍትሔ የለውም ብለው ከደመደሙት ጀምሮ አምላክ ያመጣው መቅሰፍት ነው ራሱ ይመልሰው ብለው ሕይወታቸውን በተለመደው መልኩ የቀጠሉ የዓለም ሕዝቦች ብዙ ናቸው።

የሐሳዊ ዜና ምስቅልቅል

ለምሳሌ ብሪያን ሊን እንውሰድ። 46 ዓመቱ ነው። ፍሎሪዳ በሚገኝ ሆስፒታል አልጋ ላይ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ሆኖ ለቢቢሲ ሲናገር ኮሮናቫይረስ መንግሥት ዜጎቹን ሊያዘናጋ የፈጠረው የፖለቲከኞች ሴራ ነው ብሎ ያምን እንደነበር ገለጧል።

“ሁለት ነገር ይሆናል ብዬ ነበር የገመትኩት፤ አንዱ እንዳልኩት የመንግሥት ማስቀየሻ ዘዴ ሆኖ ነበር የታየኝ። በኋላ ደግሞ 5ጂ ኔትዎርክ ነው በሽታውን ያመጣው ብዬ በጽኑ አመንኩ፤ ቀጥሎ በጽኑ ታመምኩ።” ብሪያን ብቻውን አይደለም። ባለቤቱም እንደዛ ነበር ያመነችው። በኋላ ሁለቱም የአልጋ ቁራኛ ሆኑ።

ቫይረሱ ውሸት ነው ብላችሁ እንድታምኑ ያደረጋችሁ ምንድነው? ተብለው ሲጠየቁ “በፌስቡክ ያነበብነው ሐሳዊ ዘገባ ነው ጉድ ያደረገን” ብለዋል በአንድ ድምጽ።

ቫይረሱም ይገድላል፤ ሐሳዊ ዜናም ይገድላል። የቢቢሲ የምርመራ ቡድን የሐሳዊ ዘገባዎችና የሴራ ሽረባዎች ያደረሱትን የጉዳት መጠን ለማወቅ በርካታ አገራትን አስሷል። ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ስለመሆኑም ተረድቷል። ለምሳሌ በሕንድ በኢንተርኔት የተለቀቀ ወሬ ሰው ተደብድቦ እንዲገደል አድርጓል። በኢራን በሐሰተኛ ወሬ ምክንያት መርዝ የጠጡ ብዙ ናቸው። በ5ጂ የሞባይል ኔትወርክ ላይ በተነዛው ወሬ የቴሌኮሚኒኬሽን ኢንጂነሮች ተደብድበዋል፣ የስልክ እንጨቶች በእሳት ተለኩሰዋል።

 

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ምክር

በአሜሪካ አሪዞና የዓሳ ገንዳ ማጽጃ ኬሚካል ኮሮናቫይረስን ይፈውሳል የሚል ዜና ያነበቡ ጥንዶች ኬሚካሉን ጠጥተው ሆስፒታል ገብተዋል።

ለዚህ አንዱ ተጠያቂ የሚሆኑት እንደመጣላቸው ይናገራሉ የሚባሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሳይሆኑ አይቀሩም። ዋንዳና ጌሪ ትራምፕ ስለሚያሻሽጡት ሀይድሮክሲክሎሮኪን በመጋቢት መጨረሻ ላይ ነበር የሰሙት። ቤታቸው ውስጥ አንድ ተመሳሳይ ስም የተጻፈበት ጠርሙስ አገኙ።

ሀይድሮክሲክሎሮኪን አንዳች ተስፋ የሚሰጥ መድኃኒት እንደሆነ ቢነገርም የዓለም ጤና ድርጅት በዚህ መድኃኒት ላይ የሚደረገው ምርምር እንዲቆም አዟል። ለዚህ ውሳኔ ያበቃው በቅርብ የተደረጉ ምርምሮች እንዲያው በሽታው ገዳይ መሆኑን ስላመላከተ ነበር።

የዚህ መድኃኒት ፈዋሽነት ወሬ የተነዛው በመስከረም መጨረሻ በኢንተርኔት ላይ ነበር። አንዳንድ የቻይና ሚዲያዎች ይህ መድኃኒት ጸረ-ቫይረስ ስለመሆኑ የድሮ ያልታደሰ መረጃ ይዘው አራገቡት።

ከዚያ ቀጥሎ አንድ የፈረንሳይ ሐኪም ይህንኑ የሚያጠናክር ነገር ተናገሩ። ቀጥሎ የቴስላ መኪና መስራች ኤሎን መስክ ስለ መድኃኒቱ አዳንቆ አወራ። ዶናልድ ትራምፕ ተከተሉት። ወሬው ወደ ላቲን አሜሪካ ሄደና የአእምሮ ጤናቸው ያጠራጥራል ወደሚባሉት የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ጄየር ቦልሶናሮ ጋር ደረሰ።

ከሁሉም የከፋ ጥፋት የሰሩት ግን ዶናልድ ትራምፕ ሳይሆኑ አልቀሩም። በጋዜጣዊ መግለጫቸውም ሆነ በትዊተር ሰሌዳቸው ስለ ሀይድሮክሲክሎሮኪን ሳይናገሩ ማደር አቃታቸው።

“ቆይ! ብትወስዱት ምን ትጎዳላችሁ?” ሲሉ አበረታቱ። “አንዲት ሴትዮ የእኔን ምክር ሰምታ ዳነች” አሉ። ጋዜጠኞች በጥያቄ ሲያጣድፏቸው ደግሞ “ከመሞት መድኃኒቱን ወስዶ መሰንበት አይሻልም?” ማለት ጀመሩ። ግንቦት ላይ ደግሞ ትራምፕ መድኃኒቱን ራሳቸው እየወሰዱት እንደሆነ ተናገሩ። ይህን ሁሉ ንግግራቸውን ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ሰፊ ሕዝብ ሰምቶ ያጋራዋል። ሚሊዮኖች ይነጋገሩበታል። ሺህዎች ይተገብሩታል።

በናይጄሪያ ይህን መድኃኒት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ታመው የሆስፒታል አልጋ በማጣበባቸው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል።

5ጂ የሞባይል ቴክኖሎጂ ቫይረሱን ያመጣል የሚለው ሴራ

ሐሳዊ ዜናዎችና የሴራ ትንተናዎች የንብረት ጉዳትም አድርሰዋል። ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም 70 የሚሆኑ የሞባይል ስልክ ኔትወርክ ማማዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ 5ጂ ቴክኖሎጂ ነው ቫይረሱን ያመጣው የሚለው ወሬ ነው።

በሚያዝያ ወር ኢንጂነሩ ዳይላን ፋረል ቫን መኪናውን ከተርማስተን ወደ ሌስተር እየነዳ ነበር። በሥራ የተወጠረበት ቀን በመሆኑ ትንሽ የሻይ እረፍት ለማድረግ እያሰበ ሳለ የተቃውሞ ድምጽ ወደሰማበት አቅጣጫ ዞር አለ።

መጀመርያ ያሰበው ተቃውሞው ወደ ሌላ ሰው ያነጣጠረ እንደነበረ ነው። ለካንስ “5ጂ ይውደም” የሚለው ተቃውሞ ወደሱ የሥራ መኪና ያነጣጠረ ነበር።

“አንደኛው ተቃዋሚ ወደእኔ ተጠግቶ ዘለፈኝ፤ አንተ ሞራል የሌለህ ሰው ነህ፤ 5ጂ ሕዝብ እየጨረሰ ነው” አለኝ። በጣም አስፈሪ ነበር፤ ሊደበድቡኝ ሲሉ ፈጣሪ ነው ያተረፈኝ፤ የመኪናዬ በር ዝግ ነበር።”

በ5ጂ ቴክኖሎጂ ዙርያ ብዙ የሴራ ትንተናዎች በድረ ገጾች ለዓመታት ሲነገሩ ነበር፤ ይህ ነገር ሄዶ ሄዶ ከኮሮናቫይረስ ጋር መገናኘቱ ግን አስገራሚ ነው።

ሌላው ቀጣዩ ስጋት እንደው ተሳክቶ ለተህዋሱ ክትባት ቢፈጠር እንኳ ሚሊዮኖች ለመከተብ ፍቃደኛ ላይሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል። አንዱ ምክንያት በፌስቡክ ገና ከወዲሁ የሚነዛው ወሬ ነው። መንግሥታት የሕዝብ ቁጥርን ለመቀነስ ፈልገው ነው ቫይረሱን የፈጠሩት፤ አሁን ደግሞ በክትባት ሊጨርሱን ነው ብለው የሚያምኑ በርካታ ናቸው።

‘ቢልጌትስ ሀብቱን ለመጨመር ሲል ነው ቫይረሱን ፈጥሮ ክትባቱን ያመጣው’ ሊሉ የሚችሉ ሺህዎች አሉ።

በሴራ ትንታኔ ያምን የነበረው የፍሎሪዳው ብሪያን ከሆስፒታል አልጋ ላይ ሆኖ መልዕክት አለኝ ይላል።

“አትጃጃሉ፤ እኔን አይታችሁ ተቀጡ!”

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *