• ኤጀንሲዎችያለ ሚኒስቴሩና ተቀባይ አገሮች ስምምነት መላክ እንደሚችሉ ተገልጿል

ዜጎችን ለውጭ አገር ሥራ የሚልኩ ኤጀንሲዎች የዜጎችን ሙያ የሚወስን ደረጃ ሊወጣላቸው መሆኑ ተገለጻ፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ያፀደቀው የኢትዮጵያ የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ረቂቅ አዋጅ፣ በአዋጅ 1246/2013 የተካተቱ አንቀጾችን ያሻሻለና አዳዲስ አንቀጾችን ያካተተ ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ ለውጭ አገር የሥራ ሥምሪት ዜጎችን የሚልኩ ኤጀንሲዎች ከአንድ እስከ አምስት ደረጃዎች በማውጣት ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚያደርግ ሲሆን፣ የሚልኳቸውን ዜጎች ሙያ የሚወስን መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በዚህም መሠረት ደረጃ አንድ ፈቃድ የሚወስድ ኤጀንሲ በሁሉም ዓይነት የሙያ ዘርፎች ዜጎችን መላክ የሚችል ሲሆን፣ ደረጃ አምስት ፈቃድ ያወጣ ኤጀንሲ ግን ለቤት ውስጥ ሥራ (የቤት ሠራተኞችን) የሚሄዱ ዜጎችን ብቻ እንደሚልክ ይደነግጋል፡፡

የሠለጠነ የሰው ኃይል ለመላክ በሚኒስቴሩና በተቀባይ አገር ከሚገኘው አቻ ሥልጣን ካለው የመንግሥት ተቋም ወይም ዕውቅና ካለው አሠሪ ኩባንያ፣ የሁለትዮሽ ስምምነት ወይም መግባቢያ ሰነድ ሲኖር ነው ተብሎ በአዋጅ 1246/2013 የተደነገገው አንቀጽ፣ በረቂቅ አዋጁ እንዲቀር የተደረገ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት ስምምነትም ሆነ መግባቢያ ሰነድ ሳይኖር ለሠለጠነ የሰው ኃይል ሥራ አፈላልጎ ማግኘት የቻለ ኤጀንሲ፣ የሥራ ዕድሉ ወዳለበት አገር መላክ የሚያስችል ፈቃድ ያገኛል፡፡

የሠለጠነ የሰው ኃይል ወደ ውጭ አገር ሲላክ ኮሚሽን ስለማይከፈልበት፣ ከባንኮች ጋር ትስስር በመፍጠር የባንክ ዋስትና እንዲሰጣቸው፣ የወጣባቸውን ወጪ ከባንኩ ጋር በሚኖራቸው ስምምነት እንዲመልሱ የሚደረግበት አሠራር እንዲኖር ረቂቅ አዋጁ ይደነግጋል፡፡

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ለውጭ አገር የሥራ ሥምሪት የሚላኩ ግለሰቦችን፣ ኤጀንሲዎች ከደላሎች ይወስዱ የነበረበትን አሠራር ረቂቅ አዋጁ አስቀርቷል፡፡ በዚህም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለውጭ አገር የሥራ ሥምሪት መሄድ የሚፈልጉ ዜጎችን ጥሪ በሚያደርገው መሠረት፣ እንዲመዘገቡ እንደሚደረግና ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ተደንግጓል፡፡ ከ500 በላይ በሚሆኑ የሥልጠና ተቋማት ለ21 ቀናት ሥልጠናቸውን የወሰዱ ዜጎች መረጃዎቻቸውን በዲጂታል በማስቀመጥ፣ ኤጀንሲዎች በሚፈልጉት መሥፈርት መሠረት እንዲመደቡ ጥያቄ በማቅረብ እንዲወስዱ እንደሚደረግ ተደንግጓል፡፡

ይህን አሠራር ሳይከተል ከደላላ ግለሰቦችን በመቀበል ወደ ውጭ አገሮች ለሥራ ለመላክ የሚሞክር ኤጀንሲ ከተገኘም፣ በኤርፖርት በሚደረግ ክትትል እንዳያልፉ ይደረጋል ተብሏል፡፡ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢሚግሬሽን አገልግሎትን ጨምሮ ከሰባት ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሠራ ተመላክቷል፡፡

ሌላኛው በረቂቅ አዋጁ የተካተተው ኤጀንሲዎች የሚያገኙትና ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡትን የውጭ ምንዛሪ የሚመለከተው አንቀጽ ነው፡፡ ይህም ሚኒስቴሩ በሚያሠራው ጥናት መሠረት አንድ ኤጀንሲ ለሥራ ሥምሪት ወደ ውጭ አገሮች ሲልክ፣ ኢትዮጵያ ልታገኝ የሚገባት የውጭ ምንዛሪ ምን ያህል መሆን እንዳለበት በጥናቱ መሠረት ኤጀንሲው እንደሚደራደር ተደንግጓል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2008 ዓ.ም. የወጣውን የውጭ አገር የሥራ ሥምሪት አዋጅ ለሁለተኛ ጊዜ ያሻሻለው ሲሆን፣ ረቂቅ አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከመፅደቁ በፊት ኤጀንሲዎች ውይይት እንዳላደረጉበትና ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት እንዲላክላቸውና አስተያየታቸው ታሳቢ እንዲደረግ ቢጠይቁም መመልከት እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ሲያፀድቅ፣ በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መብታቸው፣ ደኅንነታቸውና ክብራቸው በዘላቂነት መጠበቁን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲያስችል መሆኑን አስታውቋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብር መንገድ ከአውሮፓ፣ ከእስያና ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ለሥራ ሥምሪት ድርድሮች እየተደረጉ እንደሆነ መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ከኩዌት፣ ከሳውዲ ዓረቢያ፣ ከኳታር፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከጆርዳን ጋር የተደረገው ስምምነት በቅርቡ እንደሚጀምር ሚኒስትሯ አስታውቀው ነበር፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *