በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በ10 ቀናት ውስጥ 32 አሽከርካሪዎች መታገታቸውን፣ የጣና የአሽከርካሪዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡
አሽከርካሪዎች እየደረሰባቸው ባለው ዕገታና ዘረፋ ምክንያት ቀደም ሲል ውሎና አዳራቸውን ሲጓዙባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ማቆማቸውን የጣና አሽከርካሪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ ሰጡ ብርሃኑ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ በተለይ የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎች እስከ ቀኑ 10፡00 ሰዓት ብቻ እንደሚንቀሳቀሱ የተናገሩት አቶ ሰጡ፣ በዚህ ሁኔታም ቢሆን የአሽከርካሪዎች ዕገታ መበራከቱንና ባለፉት አሥር ቀናት ብቻ 32 አሽከርካሪዎች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መታገታቸውን ተናግረዋል፡፡
አሽከርካሪዎቹ ምዕራብ ጎጃም ዱር ቤቴ አካባቢ፣ ከጨጭሆ እስከ ወረታ፣ ከኢንጅባራ ቻግኒ መንገድና ዓለም ሳጋት፣ እንዲሁም ከጎንደር መተማ ባለው መንገድ ሲያሽረክሩ መታገታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ ከደቡብ ጎንደር ጨጨሆ እስከ ጋይንት ወረታ መገንጠያ ድረስ ያለው መንገድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያሉት አቶ ሰጡ፣ በአጠቃላይ በደቡብ ጎንደር ዞን ያለው እንቅስቃሴ ለአሽከርካሪዎች በጣም አስቸጋሪ መሆኑን አክለዋል፡፡
‹‹የጭነት ተሽከርካሪዎች ነዳጅና መሰል ጭነቶችን ይዘው በመንግሥት ኃይል ታጅበው ነው የሚያልፉት፤›› ያሉት ዋና ፀሐፊው፣ በቅርቡ ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በመሣሪያ ተመተው መዘረፋቸውን ተናግረዋል፡፡
ለወራት ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ የነበረው ከጎንደር መተማ ያለው መንገድ በቅርቡ መከፈቱን የገለጹት አቶ ሰጡ፣ ነገር ግን ዕገታው መቀጠሉን አክለዋል፡፡
መንገዱ ሲከፈት አሽከርካሪዎች በእጀባ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሰጡ፣ ነገር ግን እጀባው በመቅረቱ ዕገታው መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በጎንደር መተማ ባለው መንገድ በሬ ጭነው ይጓዙ የነበሩ ነጋዴዎችን ይዞ ይጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ፣ አሽከርካሪውንና ረዳቱን ጨምሮ አምስት ሰዎች መታገታቸውን የተናገሩት አቶ ሰጡ፣ በፀጥታ ችግር የተዘጉ መንገዶች ሲከፈቱ ቀደም ሲል የነበረው ችግር ወይም የተዘጋበትም ምክንያት ተለይቶ ችግሩ ሲፈታ ለሥራ ክፍት መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከመሸ ማሽከርከር ብርቅ ሆኗል ያሉት አቶ ሰጡ፣ ቀደም ሲል አሽከርካሪዎች ከአዲስ አበባ ምሽት 3፡00 ሰዓት ተነስተው ሌሌቱን ተጉዘው ሳይነጋ ዓባይን ተሻግረው ያድሩ እንደነበር የሚያስታሱት አቶ ሰጡ፣ ዛሬ ላይ ግን ከ12፡00 ሰዓት በኋላ የትም መንቀሳቀስ እንደማይቻል አብራርተዋል፡፡
‹‹ከመሸ ከከተማ ወደ ከተማ መንቀሳቀስ ታሪክ ሆኗል፤›› የሚሉት አቶ ሰጡ፣ ቀደም ሲል 24 ሰዓት ሙሉ ክፍት የነበሩ መንገዶች ዛሬ ላይ ከ10፡00 ሰዓት በላይ መጓዝ እንደማይቻል አክለዋል፡፡
‹‹ለአሽከርካሪዎችም ሆነ ለተሽከርካሪዎች ተመራጭ ጊዜ ምሽት እንደሆነ የሚያስረዱት አቶ ሰጡ፣ ነገሮች ተቀያይረው ሲመሽና አየሩ ሲቀዘቅዝ አጋቾች ቀድመው ይወጣሉ፤›› ሲሉ በአሽከርካሪዎች ላይ ያለውን ፈተና ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሰሊጥ ከጎንደር ጭነው ወልዲያ ገብተው ያድሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሰጡ፣ ዛሬ ላይ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡
በሁለት ቀናት ጂቡቲ ተገብቶ ይታደር ነበር ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ ዛሬ ላይ ግን መንገዱ ሰላም ባለመሆኑ ከአራት ቀናት ያላነሰ ጊዜን እንደሚፈጅ አብራርተዋል፡፡
ተሽከርካሪዎች 24፡00 ሰዓት ሊሠሩ ይገባል የሚሉት አቶ ሰጡ፣ የሚበላሹ ሸቀጦችን ይዘው መንገድ ላይ የሚጉላሉ አሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም በወቅቱ መድረስ ያለባቸው ግብዓቶች በወቅቱ ባለመድረሳቸው የዋጋ ንረት እንዲጨምርና ዕቃዎች እንዲበላሹ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
አሽከርካሪዎች ለኬላ፣ ለተሽከርካሪ መቆሚያ ኪራይና ሌሎች በጉዞ ላይ የሚያጋጥሙ ወጪዎችን ለማካካስ ከሚጭኑት ሸቀጥ ላይ ዋጋ መጨመራቸው አይቀርም የሚሉት ዋና ጸሐፊው፣ ይህ ደግሞ በማኅበረሰቡ ላይ በየጊዜው ጫና እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡
‹‹አሽከርካሪዎች የቢሮ ሠራተኞች ሆነዋል፤›› የሚሉት አቶ ሰጡ፣ ከባህር ዳር ጎንደር ከባህር ዳር ደሴ በሌሊት ሲሠራባቸው የነበሩ መንገዶች እንደነበሩ ጠቅሰው ዛሬ ላይ መቆማቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ሕገወጥ ናቸው ተብለው ተነስተው የነበሩ ኬላዎች በድጋሚ ተደራጅተው ገንዘብ እየሰበሰቡ መሆናቸውን አቶ ሰጡ ተናግረዋል፡፡
ኬላዎቹ ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ፈቃድ ያላገኙ ሕገወጥ ናቸው ያሉት አቶ ሰጡ፣ አሽከርካሪዎችን ለወጪና ለእንግልት የሚዳርጉ ከመሆናቸውም ባሻገር፣ ለሸቀጦች ዋጋ መጨመር የራሳቸው አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡