የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያበቃም የዘፈቀደ እስር መቀጠሉን፣ በጋምቢያ ባንጁል ከተማ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ሰብዓዊና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን ጉባዔ ላይ አቀረበ፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚል በአማራ ክልልና እንደ አስፈላጊነቱ የሚፈጸም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት ጥር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የተራዘመው ጊዜ በግንቦት 2016 ዓ.ም. መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት የታዩ የሰብዓዊ መብት አፈጻጸሞችና ክስተቶችን ለጉባዔው ያቀረቡት የኢሰመኮ የሲቪል ፖለቲካና ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጅብሪል (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ኮሚሽነር አብዲ (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አዎንታዊ ሒደቶች ያሏቸውና የሽግግር ሒደቱን ወደ ሥራ ለማስገባት የልዩ ችሎት ቢሮ፣ የእውነት አፈላላጊ ኮሚሽን፣ የምርመራ ኮሚሽንና ለልዩ ፍርድ ቤት የሚጠቅሙ አራት ሕጎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የማቆያ ቦታዎች የተጨናቀቁና ንፁህ መሠረተ ልማት የሌላቸውና በሥርዓቱ ያልተያዙ መሆናቸውን የገለጹት አብዲ (ዶ/ር)፣ በሕገወጥ ተግባር የተሳተፉ ሕፃናት ጉዳያቸው የሚታይበት ተቋማት አለመኖራቸውን፣ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ተጎጂዎች ማቆያ ማዕከላት አለመኖርና ያሉትም አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ስደተኞች ጥገኝነት ለማግኘት የሚረዳቸው በቂ ሕግ አለመኖሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በመንግሥት በኩል ግጭትን ለማስወገድ ሁነኛ ዕርምጃ አለመውሰድና እየጨመረ የመጣ ተፈጥሯዊ አደጋ ለአገር ውስጥ ፍልሰት ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡- Advertisement የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች የትምህርት፣ ሠርቶ የመኖር፣ የምግብና የጤና አገልግሎት የማግኘት መብትን ለመረጋገጥ እንቅፋት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የተናገሩት አብዲ (ዶ/ር)፣ ለጉባዔው ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭትን እንዲያቆምና አስገድዶ መሰወርን በወንጀል ተጠያቂ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የሚዲያ ሕጉን ጨምሮ ሌሎች አገራዊ ሕጎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የተጣጣሙ እንደሆኑና ለሚዲያ፣ ለሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ለሲቪክ ማኅበራትና ለሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ምቹና ምኅዳር እንዲፈጠር ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት የማቆያ ሥፍራዎችን ምቹ እንዲያደርግ፣ ፆታዊና ወሲባዊ ጉዳት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ማቆያ ማዕከላት ተደራሽና በሙሉ አቅማቸው እንዲንቀሳቀሱ፣ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ የትምህርትና የጤና ማዕከላትን ለመገንባት የተጠናከረ ሥራ እንዲከናወን፣ እንዲሁም የከተማ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በጉባዔው የተገኙት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድኅ) ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በትግራይ ክልል የነበረውን ጦርነት ጨምሮ አሁን ቀጥሏል ባሉት በአማራ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጦርነት የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጀቶችን ሥራ በእጅጉ ገድቦታል ብለዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚጠበቅበት ፍጥነት አልሄደም ያሉት አቶ መሱድ፣ መንግሥት አካታችና አሳታፊ የሆነ ውይይት በፌዴራልና በክልል ደረጃ ከሚገኙ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *