በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ እና ምሥራቅ አርሲ ዞኖች ታጣቂዎች በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀሳውስት እና ምዕመናን ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የቤተክርስቲያኗ ምንጭ ገለጹ።

በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በዶዶላ የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሁለት አገልጋዮች ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸው ሰኞ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም. ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን የቤተክርስቲያኗ ምንጮች ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው እሁድ መጋቢት 15/2016 ዓ.ም. አንድ የ80 ዓመት ሴት አዛውንት እና ሌላ ወጣት ምሥራቅ አርሲ ውስጥ በአስቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን በደኅንነት ስጋት ምክንያት ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አባት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እኒህ የሃይማኖት አባት እንደሚሉት ታጣቂዎች ወጣቷን እናት ከገደሉ በኋላ ባለቤቷን እና ልጇን አግተው ወስደዋል።

ከሁለቱ እናቶች ግድያ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በምሥራቅ አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በሚገኘው ማሊንጮ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ላይ ዘረፋ ተፈጽሟል ብለዋል።

ይህ የቤተክርስቲያን አገልጋይ በአካባቢው ክርስቲያኖች የሆኑ ዜጎች የደኅንነት ስጋት ስላለባቸው አካባቢውን ጥለው በመውጣታቸው አሁን ቤተ-ክርስቲያኑ በምን ደረጃ እንዳለ እንኳ አይታወቅም በማለት በቦታው ስላለው ሁኔታ ገልጸዋል።

በምሥራቅ አርሲ ዞን የቤተክርስቲያኗ አገልጋይ የሆኑት ቄስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቤተክርስቲያንን እና ምዕመናንን ዒላማ ባደረጉ ጥቃቶች ከመስከረም 2016 ዓ.ም. ወዲህ በአካባቢው ከ80 ያላሱ ሰዎች ተገድለዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት መጋቢት 8/2016 ዓ.ም. ደግሞ አንድ ቄስ ከእነ ባለቤታቸው በዚሁ ዞን ሽፎ በሚባል አካባቢ መገደላቸውን የቤተክርስቲያኗ ምንጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“እነዚህ ጥቃቶች ቤተክርስቲያን እና ክርስቲያኖችን ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። ድርጊቱን ስንመለከት ትኩረታቸው ቤተክርስቲያንን፣ አገልጋዮች እና ምዕመናን ላይ ነው” በማለት ታጣቂዎቹ ዒላማ እያደረጓቸው ነው ያሏቸውን ወገኖች ገልጸዋል።

በአካባቢው በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በተመለከተ ፈጻሚው ማን እንደሆነ በግለጽ እንደማያውቁ የሚናገሩት ቀሳውስት እና ምዕመናን፣ የመንግሥት አካላት ግን አማጺውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን በተጠያቂነት ይከሳሉ።

“ችግሩ ስር የሰደደ ስለሆነ የፀጥታ አካላት ቢሯሯጡም ምንም ማድረግ አልቻሉም። ጥቃት አድራሾቹን መንግሥት ሸኔ ናቸው ይላል። እኛ ደግሞ ይሄ ነው ማለት የሚያስችለን ምንም ዓይነት መረጃ የለንም” ሲሉ በስፍራው የሚገኙት የሃይማኖት አባት ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሌለኛው የአርሲ ዞን በምዕራብ አርሲ ሁለት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ከአምስት የቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር መገደላቸው ተዘግቧል።

የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ቴሌቪዥን በምዕራብ አርሲ ዞን የሚገኘው የደብረ ቅዱሳን ቅዱስ ገ/ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሁለት አገልጋዮች ከአምስት ቤተሰቦቻቸው ጋር በታጣቂዎች በጥይት መገደላቸውን ዘግቧል።

በሁለቱ አገልጋዮች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ ግድያው የተፈጸመው እሁድ መጋቢት 16/2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ መሆኑን የአካባቢው ምዕመናን ጠቅሶ የቴሌቪዥን ጣቢያው ዘግቧል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቤተክህነት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍን በምዕራብ አርሲ ውስጥ ስለተፈጸመው ግድያው መስማታቸውን፤ ነገር ግን ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞኖች ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሰል ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው ኅዳር ማብቂያ ገደማ አርሲ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎች 36 ምዕመናን መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ባወጣችው መግለጫ ማውገዟ ይታወሳል።

ቤተክርስቲያኗ በምዕመኖቿ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ባለቻቸው ጥቃቶች ከተፈጸሙት ግድያዎች በተጨማሪ በቤተክርስቲያን እና በምዕመናን ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጻ ነበር።

በወቅቱም የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጠው፤ ጥቃቱን መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መፈጸሙን ተናግረው ነበር።

ሰሞኑን የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ቢቢሲ ከኦሮሚያ ክልል እና ከዞኖቹ ባለሥልጣናት መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፤ እነሱም ክስተቱን በተመለከተ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *