በምሥራቅ ወለጋዋ ነጆ ከተማ ተወልዶ ያደገው ኦብሳ አባተ፣ አሁን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዛይድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሜታ ቨርስ እና አፕላይድ ኤአይ ረዳት ተመራማሪ ነው።

ኦብሳ ወላጆቹ ከሕጻንነቱ ጀምሮ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኝ መጣራቸውን ያስታውሳል።

አዳማ በሚገኘው የኦሮሚያ ልማት ማኅበር አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረው ኦብሳ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በጥሩ ውጤት ሲያጠናቅቅ፣ እኤአ በ2019 ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝቶ ሄደ።

በኤምሬትስ ትምህርቱን በጥሩ ሁኔታ በማጠናቀቁ በተማረበት ዩኒቨርስቲ የተመራማሪነት ዕድል አግኝቷል። አገሪቱም ነጻ የመኖርያ ፈቃድ ሰጥታዋለች።

ይህ ስኬት ግን የኦብሳ አባተ ብቻ አይደለም።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው እየተማሩ ይገኛሉ።

እነዚህ ተማሪዎች በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥታት ስምምነት መሠረት የትምህርት ዕድል የተመቻቸላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ በግላቸውም ወደ ባሕረ ሰላጤዋ አገር የሄዱም ይገኙበታል።

ምንዳ በለጠ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። ምንዳ በአቡ ዳቢ በሚገኘው ኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ተመርቋል።

ምንዳ የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በሚማርበት ትምህርት ቤት ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች በኤምሬትስ ነጻ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን በማየቱ ነበር እርሱም የሞከረው።

“ቀድሜ አመልክቼ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት እና የክፍል ውጤትን አይተው ነው የነጻ ትምህርት ዕድሉን የሰጡኝ” ይላል።

ምንዳ አዲስ አበባ ውስጥ የመሰናዶ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነበር። ወደ አቡ ዳቢ ኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ሲያመራ ደግሞ በተቃራኒው ኢኮኖሚክስ ለመማር ነበር የመረጠው። ይህ ለምንዳ በመጠኑ ከብዶት ነበር።

ምክንያቱም በመሰናዶ ትምህርቱ ያልተማረው በመሆኑ ከኢኮኖሚክስ ጋር እንደዲስ መተዋወቅ ነበረበት። ያም ቢሆን ግን “በልዩ ትኩረት ትምህርቴን ስለተከታተልኩ በስኬት ለማጠናቀቅ በቅቻሉ።”

ምንዳ በኒው ዮርክ ዩኒቨርስቲ በነበረው ቆይታ በክፍል ትምህርት ያገኘው ውጤት እና በሠራቸው የተለያዩ ጥናቶች ያስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ተገምግሞ በዩኒቨርስቲው የሥራ ዕድል አግኝቷል።

“ለምረቃ ስደርስ የተሻለ ጥናት አቅርቤ ነበር። አማካሪዎቼ እና በዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገኙ ፕሮፌሰሮች ጥናት ወረቀቴን አይተው ስለወደዱት በጥናት ዘርፍ ረዳት ተመራማሪ ሆኜ እንድሠራ ዕድል ሰጡኝ።”

ምንዳ በተማረበት የአቡ ዳቢ ኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ከ126 አገራት ከመጡ ተማሪዎች ይማራሉ። በዚህም ሳቢያ የቋንቋ፣ የባህል እና የእምነት ሰፊ ልዩነት ስላለ ተከባብሮ አብሮ መማር እና መሥራትን የበለጠ እደተማረበት ይናገራል።

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እያደገ ያለው ምጣኔ ሃብት እና ቴክኖሎጂ የተነሳ በአገሪቱ የሚማሩ ተማሪዎች ትልቅ ልምድ ለመቅሰም ዕድል ማግኘታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤምሬትስ ከፈጸሟቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት ስምምነቶች መካከል አንዱ የትምህርቱ ዘርፍ ነው።

ይህን ግንኙነት መሠረት በማድረግ የኤምሬትስ መንግሥት የኢትዮጵያ ወጣቶች በትምህርት እና በክህሎት ብቁ እንዲሆኑ ነጻ የትምህርት ዕድል ከፍቷል ሲሉ በአገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዑመር ሁሴን ይናገራሉ።

በአሁኑ ወቅት ከ300 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተለያዩ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በተለይ ደግሞ አቡ ዳቢ እና ዱባይ ውስጥ፣ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ይማራሉ።

ከተመረቁ በኋላም በተለያዩ የሕክምና እና የትምህርት ተቋማት ውስጥ በሙያቸው እያገለገሉ ያሉም መኖራቸውን እና ይህም የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየጠነከረ በመምጣቱ የተገኘ ዕድል ነው ይላሉ አምባሳደሩ።

የትምህርት ዕድል በባሕረ ሰላጤዋ አገር

በ2015 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 273 ተማሪዎች በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተሟላ ነጻ የትምህርት ዕድል ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መመቻቱ ተገልጾ ነበር።

ይህ ግን የመጀመሪያው አልነበረም።

እነ ኦብሳ እኤአ በ2019 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ነጥብ ካስመዘገቡ እና በኤምሬትስ ነጻ የትምህርት ዕድል ካገኙ 240 ተማሪዎች መካከል 40 የሚሆኑት የተሰጠውን የመግቢያ ፈተና አልፈው የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝተዋል።

መባ በዛብህ በአዲስ አበባ ናዝሬት ትምህርት ቤት ነው የተማረችው። በ2022 (እአአ) የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሙሉ የትምህርት ዕድል ከሰጣቸው 273 ተማሪዎች መካከል አንዷ ነች። መባ በአቡ ዳቢ ዛይድ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ ተማሪ ናት።

ከዚህ በፊት ወደ አውሮፓ የትምህርት ዕድሎችን በተለይ ደግሞ ጣልያን እየሞከረች እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ይህንን ዕድል ሳገኝ የተደበላላቀ ስሜት ነው የተሰማኝ። እዚህ መጥቼ ካየሁ በኋላ ግን ዩኒቨርስቲው የምዕራባውያንን ተቋማት ቢበልጥ እንጂ እንደማያንስ ነው የገባኝ።”

የትምህርት ዕድሉን እንዳገኘች “ትምህርቱ ያን ያክል ሊሆን ስለሚችል ይቅርብሽ ያሉኝ ሰዎች ነበሩ” ያለችው መባ፣ አሁን ያለውን ሁኔታ ሲመለከቱና ሳስረዳቸው ግን እነዚያው ሰዎች “እንኳንም ሄድሽ እያሉኝ ነው” ትላለች።

መባ ከትምህርቱ በተጨማሪ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ብዙ ኢትዮጵያውያን በመኖራቸው እና የአገሬው ሰውም በጣም ተባባሪ ስለሆነ “ለመላመድም ሆነ በትምህርቴ ላይ ለማተኮር አልተቸገርኩም” ብላለች።

የኤምሬትስ ኢኮኖሚ እና ቴክኖሎጂ ዓለምን እያስደመመ ነው የምትለው መባ፣ የተሻለ የትምህርት ዕድል ከፍቶልኛል ትላለች።

ቦንቱ ይስሙ በበኩሏ በኤምሬትስ የነጻ ትምህርት ዕድል ማግኘቷን ከሰማች በኋላ ሀሳቧ ለሁለት መከፈሉን ታስታውሳለች።

“የተሻለ ትምህርት እንደሚፈልግ ተማሪ ይህንን ዕድል በማግኘቴ ደስ ብሎኛል። የሙስሊም አገር በመሆኑ ግን በባህል፣ በእምነት እና ማኅበራዊ ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል ብዬ ፈርቼ ነበር። እዚህ ከመጣሁ በኋላ ያየሁት ግን ተቃራኒውን ነው።”

ቦንቱ በጤና ትምህርት ክፍል ስር ፐብሊክ ሄልዝ እና ኒውትሬሽን ተምራ በቅርቡ ተመርቃለች።

“በትምህርቴ መሠረታዊ የሆነ ነገር ስለማውቅ ብዙም አልከበደኝም። እንዲያውም ልምድ ባላቸው መምህራን እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት ስለሚሰጠን በጥሩ ውጤት ትምህርቴን መጨረስ ችያለሁ።”

ኦብሳ “ብዙ ጥናቶች ውስጥ የመሳተፍ ዕድል አግኝቻለሁ። ከአምስት ጥናቶች በላይ ሰርቼ ሁለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁ ጆርናሎች ላይ ታትመዋልኛል” ይላል።

ወደ አሜሪካ በመጓዝም በዓለም አቀፍ የምርምር ውጤቶች ፕሮግራም ላይ በመገኘት አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ላይ የሠራውን ጥናት የማቅረብ ዕድል አግኝቷል።

“ይህ ሁሉ እዚህ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ለጥናት እና ምርምር ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጡ የሚያሳይ ነው።” ይላል ኦብሳ።

በኤምሬት የሚማሩ ኢትዮጵውያን ምን ያገኛሉ?

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት በኢንቨስትመንት ውስጥ የተሻለ ተሳትፎ ለሚያደርጉ እና በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ግለሰቦች የመኖርያ ፈቃድ ‘ጎልደን ቪዛ’ በመስጠት ይታወቃል።

ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችም የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች ሆነዋል። ትምህርታቸውን የጨረሱት ምንዳ፣ ቦንቱ እና ኦብሳ ጎልደን ቪዛ ተሰጥቷቸዋል።

ቦንቱ በአገሪቷ ውስጥ እያደገ ያለውን የቴክኖሎጂ ዘርፍ በአካል በመገኘት እና በማየት ልምድ ለመቅሰም ዕድል እንዳገች እና የተለያዩ ጥናቶችን እንድታካሂድ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላት ትናገራለች።

“በቴክኖሎጂ አገርን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል በተጨባጭ አይቼ ተምሬያለሁ፤ ይህ ደግሞ አስተሳሰቤን በጣም ቀይሮታል” ትላለች።

ቦንቱ በአጠቃላይ ኤምሬትስ ውስጥ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተዘዋውሮ በማየት ልምድ ከመቅሰሟ በተጨማሪ የሠራችውን ጥናት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በመሄድ አቅርባለች።

ምንዳ ውድድሩ ከብዙ አገራት ከመጡ ተማሪዎች ጋር ስለሆነ “ከዓለም አቀፍ ተማሪዎች ጋር በመወዳደር ራሴን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማዘጋጀት አግዞኛል” ብሏል።

በተለይ “ለችግሮች በራሴ መፍትሔ እንድሰጥ አድርጎኛል” የሚለው ምንዳ፣ አሁን የምርምር ሥራውን እያከናወነ ሲሆን፣ በዚሁ ቀጥሎም ሦስተኛ ዲግሪ [ፒኤችዲ] የመማር ሃሳብ አለው።

መባ ደግሞ የጀመረችውን የፋይናንስ ትምህርት በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ ኢትዮጵያ ውስጥ በተማረችበት ሙያ የራሷን አሻራ ለማሳረፍ ማቀዷን ገልጻለች።

በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተወካይ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር አብዱልናስር ሀሮ እነዚህ ተማሪዎች ባገኙት ልምድ አገራቸውን እንዲጠቅሙ ኢምባሲ እና መንግሥት አንድ ላይ እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ።

“በቅርቡ እነዚህ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተለያዩ ዩኒቨርስቲ ለሚማሩ ተማሪዎች መጽሐፍቶች እና የጥናት ሥራዎችን በመሰብሰብ ወደ አገር ቤት ልከዋል። እኛ ደግሞ እነዚህ መጽሐፍቶች እና ጥናት ወረቀቶች ለኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች እንዲደርሱ አድርገናል” ብለዋል።    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *