Month: January 2021

ኢሰመጉ በኦሮሚያ ክልል እየደረሱ ያሉ ግድያዎችና ማሰቃየቶች አሳስበውኛል አለ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ አካባቢዎች እየደረሱ ያሉ ግድያዎች፣ ድብደባና ማሰቃየት፣ እንዲሁም ሕገወጥ እስራቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸው እጅግ አሳስቦኛል አለ፡፡ ኢሰመጉ ማክሰኞ ታኅሳስ 27 ቀን…

መንግሥት ፈጣን ዕርምጃ ካልወሰደ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሊፈጸም እንደሚችል የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ

ከድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ አስቀድሞ ማንነትን የለየ የማጥቃት አዝማሚያ እንደነበር አስታውቋል የፀጥታ መደፍረስ በተከሰተባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ወንጀል ምልክቶች መስተዋላቸውንና መንግሥት ፈጣን የጥንቃቄ ዕርምጃ ካልወሰደ፣ በኢትዮጵያ ሊፈጸም እንደሚችል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች፣ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መበቶች ጥስቶችን በተመለከተ ያካሄደውን ሰፊ የምርመራ ውጤት ዓርብ ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በወቅቱም የድምፃዊውን ግድያ ተከትሎ ምርመራውን ባደረገባቸው አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያሟሉ ድርጊቶች አለመከሰታቸውን አስታውቋል። የድምፃዊውን ግድያ ተከትሎ ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው 40 አካባቢዎች የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች፣ ጭካኔና ግፍ የተሞላባቸው፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች መሆናቸውን አስታውቋል።   የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የምርመራ ሪፖርቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፣ የድምፃዊ ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የተፈጸመውም ሆነ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች የተስተዋሉ የግፍና የጭካኔ ወንጀሎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል የመከሰት አደጋን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው ብለዋል። ‹‹ኮሚሽኑ እስካሁን በተከታተላቸው የፀጥታ ችግሮች፣ ጭካኔና ግፍ የተሞላባቸው ወንጀሎች ቢፈጸሙም፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያቋቁሙ ናቸው ብሎ አያምንም፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ነገር ግን እየታዩ ያሉ ጭካኔ የተሞላባቸው የወንጀል ድርጊቶች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል አደጋ ምልክቶች ናቸው ብለዋል። በመሆኑም መንግሥት ጭካኔና ግፍ የተሞላባቸው ወንጀሎችን ለመከላከል፣ ብሔራዊ ስትራቴጂ ቀርፆ መንቀሳቀስ እንዳለበት ምክረ ሐሳብ መቅረቡን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምርመራ በ40 የኦሮሚያ አካባቢዎች ባሰባሰበው መረጃ መሠረት፣ የድምፃዊውን ሞት ተከትሎ በነበሩት ሦስት ተከታታይ ቀናት በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ፣ በአጠቃላይ የ123 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ቢያንስ በ500 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን፣ በግለሰቦች፣ በንግድ ድርጅቶችና በመንግሥት ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን አስታውቋል። ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች ውስጥ 35 ያህሉ በሁከቱ በተሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች የተገደሉ መሆናቸውን፣ እነዚሁ አካላት በ306 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን፣ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ዕርምጃ ደግሞ ቢያንስ 76 ሰዎች መገደላቸውንና ከ190 በላይ ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውቋል። በሌላ በኩል በፀጥታ መደፍረሱ ወቅት በተከሰተ ፍንዳታ፣ ቃጠሎና መሰል አደጋዎች 12 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ገልጿል። ‹‹በዚህ መጠነ ሰፊ ጥቃት የተሳተፉት ብዙ ቁጥር ያላቸው ከቦታ ቦታ በቡድን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ሲሆኑ በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራና በመጥረቢያ ሰዎችን ደብድበዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ ፍፁም ግፍና…