በደቡብ ክልል ምዕራባዊ ክፍል፣ በአሁኑ የክልል አወቃቀር በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው ሸካ ጫካ በርካታ የተፈጥሮ ሀብትን በውስጡ ይዟል።
ይህ በቡና እና በተለያዩ የቅመማ ቅመም ምርት የሚታወቀው የሸካ ጫካ ለጫቡ ማኅበረሰብም መኖሪያ ነው።

በእርግጥ ማኅበረሰቡ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በጋምቤላ ክልሎች ውስጥ ተበታትኖ ነው የሚኖረው።

ጎረቤቶቹ ደግሞ የሸክቾ እና የመዠንገር ሕዝቦች ናቸው።

የጫቡ ማኅበረሰብ ከራሱ አልፎ በአካባቢው የሚነገሩ የመጃንግ፣ ሸክቾ፣ ኦሮምኛ እና አማርኛ ቋንቋዎችን ይናገራል።

ይህ በቁጥር አነስተኛ የሆነው የጫቡ ማኅበረሰብ የተለያዩ ምሁራን ባደረጉት ጥናት የቋንቋው ተናጋሪ ሕዝብ ከ600 እስከ 1000 እንደሚሆን ግምታቸውን አስቀምዋል።

በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል የሥነ ልሳን መምህር የሆኑት እና በጫቡ ቋንቋ ላይ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት ክበበ ፀሐይ (ዶ/ር) በበኩላቸው የቋንቋው ተናጋሪዎች 740 ናቸው ይላሉ።

ክበበ (ዶ/ር) የጫቡ ማኅበረሰብ በቁጥር ምን ያህል ነው የሚለውን ለማወቅ “መጠነኛ የቤት ለቤት ቆጠራ” ለማካሄድ መሞከራቸውን ይናገራሉ።

በዚህም 306 አባራዎችን ለማዳሰስ መሞከራቸውን እና 890 ጫቡ ነን ያሉ የማኅብረሰብ አባላትን እንዳገኙ ጠቅሰው 740 ያህሉም ቋንቋውን እንደሚናገሩ ለይተዋል።

ጫቡ ወይንም ጻቡዎች የት ይኖራሉ?

በአብዛኛው የሥነ ልሳን ተመራማሪዎች ዘንድ የጫቡ ቋንቋ እና ማኅበረሰብ ሻቦ ከዚያ በፊት ደግሞ ሚኪየር ሌላ ጊዜ ደግሞ ሳቡየ እየተባለ ሲጠራ ቆይቷል።

ሚኪየር እና ሳቡየ መዠንገሮች የቋንቋውን ተናጋሪ ማኅበረሰብ የሚጠሩበት እንደሆነ ክበበ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።

ሚኪየር የሚለውን አጠራር ግን የጫቡ ማኅበረሰብ ጸያፍ አድርጎ የሚቆጥረው ነው።

ሳቡየ የመዠንገር ማኅበረሰብ አባላት ብሔረሰቡን ለመጥራት አሁንም እንደሚጠቀሙበት ምሁሩ ይናገራሉ።

ለረዥም ጊዜ ማኅበረሰቡ የሚናገረው ቋንቋም ሆነ ራሱ ማኅበረሰቡ ሻቦ እየተባለ ሲጠራ የነበረ ቢሆንም በምርምር ሥራቸው ወቅት ጫቡ እንደሚባሉ አጥኚው አረጋግጠዋል።

አክለውም “ጫቡ ወይንም ጻቡ ማኅበረሰቡ ራሱን የሚጠራበት ስያሜ ነው” ብለዋል።

የጫቡ ማኅበረሰብ የሚኖርበትን ጫካ ጫዊ፣ ቋንቋውን ደግሞ ‘ጫዊ ካው’ [የጫቡ ቋንቋ እንደማለት] ሲል ይጠራል።

የጫቡ ማኅበረሰብ አባላት የሚኖሩት በሁለት ተጎራባች ክልሎች ውስጥ ነበር።

አንደኛው ክልል ጋምቤላ ሲሆን፣ የመዠንገር ዞን ውስጥ ጎደሬ እና መንገሺ ወረዳዎች ውስጥ ይገኛሉ።

በዋናነት በመንገሺ ወረዳ በበርካታ ቀበሌዎች ውስጥ ሲገኙ፣ በጎደሬ ግን በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ብቻ ሰፍረዋል።

በሌላ በኩል በደቡብ ምዕራብ ክልል ውስጥ በሸካ ዞን በአንደራቻ ወረዳ ውስጥ ገይ እና ሽራ እንዲሁም ሸካ በዶ በሚባሉ ሦስት ቀበሌዎች ውስጥ ይገኛሉ።

ማኅበረሰቡ ከዚህ ቀደም በአደን፣ ሥራሥር በመልቀም እና ንብ በማነብ ይተዳደር ነበር።

አሁን ይኖሩበት የነበረው የደን ይዞታ እየተመናመነ፣ ለቡና እና ለሌሎች ልማቶች እየተሰጠ ሲመጣ እነርሱ ወደ መሀል እየተገፉ የአኗኗር ሁኔታቸውን ለመቀየር መገደዳቸውን ይናገራሉ።

“ከዚህ ቀደም ለአደን አመቺ በሆኑ ቦታዎች ተበታትነው ይኖሩ የነበሩት ጫቡዎች አሁን ግን በሁኔታዎች አስገዳጅነት በመደሮች እየተሰባሰቡ መኖር ጀምረዋል።”

ማኅበረሰቡ ከድሮ ጀምሮ በቆሎ የሚያመርት ሲሆን አሁን ደግሞ ጎደሬ፣ ሚቲ የሚባሉ የሥራሥር ዓይነቶችን ያመርታሉ።

ቡና፣ ሸንኮራ እና ሙዝም ማምረት መጀመራቸውን ተመራማሪው ይናገራሉ።

የጫቡ ባሕላዊ አባት

‘የጫቡ ቋንቋ እየጠፋ ነው’

አንድ ቋንቋ ሊጠፋ የመቃረቡን አዝማሚያ ለመጠቆም ከተቀመጡ መስፈርቶች መካከል አንዱ ሕጻናት በአፍ መፍቻነት ይጠቀሙበታል ወይ? የሚለውን ነው የሚሉት ክበበ (ዶ/ር)፤ የማኅበረሰቡ አባል ሆነው ቋንቋውን የማይናገሩ፣ እንዲሁም በሁለተኛ ቋንቋነት የሚናገሩት መኖራቸውን በመጥቀስ “ቋንቋው እየጠፋ ነው” ይላሉ።

ተመራማሪው በጥናታቸው ወቅት ወደ ጫቡዎች መንደር ሲመላለሱ ያስተዋሉት ነገር ቢኖር፣ ማኅበረሰቡ ወደሚኖርበት አካባቢ የእርሻ መሬት ፍለጋ በሚል ሌሎች ሕዝቦች መጥተው እየሰፈሩ በመሆኑ ጫቡዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በቦታው ላይ ያገኟቸውም ቢሆኑ ጎረቤቶቻቸው የሆኑት የሸካቾ ቋንቋን እንጂ የጫቡ ቋንቋን በዋናነት የሚናገሩ አይደሉም ሲሉ ቋንቋው የመጥፋት አደጋ ምን ያህል እንደተጋረጠበት ያስረዳሉ።

የጫቡ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው ወደ ሌላው ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ የሚጠቀሙት ከራሳቸው ውጪ ያሉ የጎረቤቶቻቸውን ቋንቋ ነው ይላሉ።

ሌላው አዲስ የሚወለዱ ሕጻናት በአፍ መፍቻነት ቋንቋውን መልመድ እየቀነሱ መምጣታቸው ቋንቋው እየጠፋ ስለመሆኑ ማስረጃ መሆኑን ያነሳሉ።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ ከሆነ ከሕጻናቱ ውጪ አዋቂዎች ልሳነ ብዙ መሆናቸውን በመጥቀስ ይህ ራሱ ቋንቋው አደጋ ላይ ስለመሆኑ ምልክት ነው ይላሉ።

በዚህም እነርሱ የሌሎቹን ማኅበረሰቦች ቋንቋ መናገር ቢችሉም ሌሎቹ ግን የእነርሱን ቋንቋ ባለመቻላቸው ከተለያዩ ማኅበረሰቦች ጋር በሚሆኑ ጊዜ የራሳቸውን ቋንቋ የመጠቀም ዕድላቸው ዝቅተኛ አድርጎታል።

ቋንቋው እየጠፋ ለመሆኑ ማስረጃ ይሆን ዘንድ ተመራማሪው ሳይንሳዊ መላምቶችን ያስቀምጣሉ።

” አንድ ቋንቋ የመጥፋት ደረጃ ላይ ደረሰ ሲባል ከመቶ ሺ በላይ ስጋት የሌለበት (safe)፣ ከ50ሺ-100ሺ ስጋት ያለበት (vulnerable)፣ ከ10-50ሺ አደጋ ላይ ያለ (definitely endangered)፣ ከ1-10ሺ በከፋ ሁኔታ አደጋ ላይ ያለ (severely endangered)፣ ከ1ሺ በታች የሞት አፋፍ ላይ ያለ (critically endangered) ቋንቋ ነው ይባላል”

ቋንቋው ትምህርት የማይሰጥበት፣ በየትኛውም መገናኛ ብዙኃን ላይ የማይነገር በመሆኑ እየጠፋ ነው ማለት ይቻላል ሲሉ ክበበ (ዶ/ር) ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

“የትኛውም ቋንቋ ሲጠፋ የአንድ አገር ትልቅ ሀብት፣ ቅርስ እንደጠፋ ነው የሚቆጠረው” የሚሉት ተመራማሪው ምክንያቱንም ሲያስረዱ “አንድ ማኅበረሰብ በቋንቋው ወጉን፣ ባህሉን፣ ፍልስፍናውን፣ የዘመናት እውቀቱን፣ ጥበቡን፣ ልማዱን የያዘበት ሰነዱ ነው” ይላሉ።

ስለዚህ አንድ ማኅበረሰብ የራሱን ቋንቋ እየጣለ ሌላ መናገር ሲጀመር የራሱን ማንነት፣ ዕሴት እና ባህል እየተወ የሌላ ሕዝብ ማንነት እና ባሕልን እየወሰደ ይኖራል ሲሉ የሚፈጠረውን ጉድለት ያስረዳሉ።

“አንድ ቋንቋ ሲጠፋ በሌሎች አብያተ መጻሕፍት ውስጥ የሌሉ በርካታ ውድ ውድ መጽሐፍት ያሉት ትልቅ ቤተ መጻሕፍት እንደተቃጠለ ነው የሚቆጠረው።”

ጫቡ

ጫቡ – ቀደምት አፍሪካዊ የቋንቋ ቤተሰብ

ለሥነ ልሳን ተመራማሪው የጫቡ ቋንቋ በአገሪቱ ካሉ ቋንቋዎች ለየት የሚያደርገው ገጽታ አለው ይላሉ።

“ጫቡን ለየት የሚያደርገው አንዳንድ ምሁራን እንደሚያስቀምጡት አሁን ባለው የቋንቋ ምደባ በአራቱ የአፍሪካ የቋንቋ ቤተሰቦች ውስጥ አለመካተቱ ነው።”

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩት ቋንቋዎች በቤተሰብ ይመደቡ ቢባል አፍሮ ኤሲያዊ እና አባይ ሰሀራዊ (“Nilo-Saharan) ብቻ ናቸው።

ሰሜቲክ፣ ኩሽቲክ እና ኦሞቲክ የአፍሮ ኤሽያዊ ቤተሰብ ንኡሳን ዘሮች ናቸው።

ሌላው በአፍሪካ የሚነገሩ ሁለት የቋንቋ ቤተሰቦች ደግሞ ኮይሻን እና ናይጀር ኮንጎ የሚባሉ የቋንቋ ቤተሰቦች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

ጫቡ ግን በተለያዩ ምሁራን በተደረጉ ምርምሮች በአፍሪካም ሆነ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ከሚነገሩ የቋንቋ ቤተሰቦች ውስጥ እንደማይካተት እንደተደረሰበት ክበበ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።

በእርግጥ ከዚህ ቀደም ቋንቋውን የመጃንግ ቋንቋ አንድ ዘዬ ነው ያሉ፣ በከፊል አባይ ሳህራዊ (ናይሎ ሳህራን) ውስጥ የመደቡ ምሁራን ቢኖሩም፣ አሁን ግን በተደረጉ ዝርዝር ጥናቶች ቋንቋው ከዚህ ቤተሰብም እንደሚለይ እንደተደረሰበት ተመራማሪው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

እንደ አንዳንድ ምሁራን ገለጻ ከሆነ ይላሉ ክበበ (ዶ/ር)፣ ጫቡ የሚመደበው በአምስተኛ የቋንቋ ቤተሰብነት ነው ሲሉ ያስቀምጡታል።

“ጫቡ ምናልባትም አንድ የጠፋ ቀደምት አፍሪካዊ የቋንቋ ቤተሰብን የሚወክል ነው ተብሎ ይታሰባል።”

የጫቡ ማኅበረሰብ “የጫካው ቀደምት ነዋሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ” ተብሎ እንደሚታመን የሥነ ልሳን ምሁሩ ክበበ (ዶ/ር) አክለው ያስረዳሉ።

እንዲሁም የአንድ ቋንቋ ቤተሰብን ባህሪያት ብቻውን ይዞ የሚገኝ በማለት “ምናልባትም ስለዚያ የቋንቋ ቤተሰብ ማውራት ሲፈለግ ብቸኛ መረጃ የሚሰጠን ነው” ይላሉ።

የጫቡ ቋንቋ መጥፋት ከፍተኛ ኪሳራ ነው የሚሉት ምሁሩ፣ ይህንንም ሲያስረዱ “ይህ አንድ የጠፋ የቋንቋ ቤተሰብን የሚወክል ከሆነ፣ የያዘው መረጃ የጠፋውን የቋንቋ ቤተሰብ ማግኘት የሚያስችል ሌላ ግብዓት የሚሆን ቋንቋ ስለሌለ የጫቡ መጥፋት ከሌሎችም በላይ ነው።”

የጫቡዎች ባህል

ጫቡዎች እንደዛሬው በሁለት ክልሎች በተለያዩ ቀበሌዎች ተበታትነው ከመኖራቸው በፊት መገኛቸው የሸካ ጫካ እምብርት እንደሆነ ያምናሉ።

ጫቡዎች ያደኑትን የዱር እንስሳ ከማኅበረሰባቸው አባላት ጋር ተካፍሎ መብላት ባህላቸው ነው።

ምንም እንኳ አሁን አሁን እንሰት፣ ሙዝ፣ በቆሎ፣ ካሳቫ፣ ሸንኮራ እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን እና ሥራ ሥሮችን ቢያመርቱም ለገበያ የሚያቀርቡት ግን የጫካ ማር ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።

ጫቡዎች የእንሰት ተክልንም ቢሆን ለምግብነት መጠቀም አለመጀመራቸውን ተመራማሪው በጥናታቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ጫቡዎች ከራሳቸው ማኅበረሰብ አባላት ውጪ ከሸክቾ፣ ከከፋ እና ከኦሮሞ ብሔረሰቦች ጋር ተጋብተው ይኖራሉ።

በጫቡዎች ዘንድ ሴት ልጅ በጣም የተከበረች ነች የሚሉት ምሁሩ፣ ሴትን መተናኮል የሚያስከትለው “ሞት ነው” ይላሉ።

በሸካ ጫካ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ወንዶች ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጥቃት ይደርስብናል ብለው ቢሰጉም፣ ሴቶች ግን ከዚህ ስጋት ነጻ ሆነው እንደሚንቀሳቀሱ ይናገራሉ።

በጋለ ጠብ ውስጥ ሴቶች ለመገላገል ቢገቡ፣ ጠቡ የሚበርድበት እና የሚቆምበት ሁኔታ መኖሩንም ይናገራሉ።

በቋንቋውም ላይም ቢሆን ይህንን የሚያመለክት መዋቅር መኖሩን ይናገራሉ።

በማኅበረሰቡ ወንዶች የሐዘናቸውን ጥልቀት ሲገልጹ በሚፈሰው እንባቸው ብዛት ሳይሆን ግንባራቸውን በጦር በመምታት በሚፈሳቸው ደም መጠን ነው።

“በጠለፋ ያገባ ወንድ ከልጅቱ አባት ጋር ሲታረቅ አባትየው ፍም እሳት አንስቶ ለጠላፊው በመስጠት፣ ሁለቱም እየተቃጠሉ ጨብጠውት በቃጠሎው እርቁ ይጸናል” ይላሉ።

የጫቡ ወንድ ያለ ሚስቱ ፈቃድ የፍቅር ግንኙነት መፈጸም አይችልም። ለሚስቱ የዘረጋላትን ሽመል ስትቀበለው ብቻ ለግንኙነት ፈቃደኛ መሆኗን ያውቃል።

በቀደመው ባህል የጫቡ ሴት ማርገዟን እንዳወቀች ወልዳ ልጁ በእግሩ ድክ ድክ ማለት እስኪጀምር ከቤቱ ርቆ ይሄዳል።

ምንም እንኳ አባወራው ከቤቱ በሚርቅበት ወቅት በአደን ያገኘውን ሥጋ ለሚስቱ የሚልክ ቢሆንም፣ ነፍሰጡር የሆነችው ሴት ሥራ ሥር እየተመገበች ለብቻዋ ትቆያለች።

ይህ ባህል አሁን የቀረ ቢሆንም፣ በእርግዝና ወቅት ግን ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደማይፈጽሙ የማኅበረሰቡ አባቶች ያስረዳሉ።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *