የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት “አንድ ትሪሊዮን [ብር] የሚጠጋ” እንዲሆን ወሰነ። ለቀጣዩ በጀት ዓመት የተዘጋጀው የአገሪቱ በጀት 971.2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ቢቢሲ ከገንዘብ ሚኒስቴር ምንጭ ተረድቷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀጣዩ ዓመት በጀት ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳለፈው ዛሬ አርብ ግንቦት 30/2016 ዓ.ም. እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የ2017 ዓ.ም. በጀት የተዘጋጀው የዘንድሮው የፌደራል መንግሥትን የፕሮግራም በጀት አፈጻጸም መነሻ በማድረግ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

የመንግሥት የፋይናንስ አቅም እና ተጠባቂ ገቢዎችም በበጀት ዝግጅቱ ውስጥ ታሳቢ የተደረጉ ጉዳዮች እንደሆኑ ተገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፤ “[በጀቱ] አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ተልዕኮ እና ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ወጪ በመገምገም እንዲዘጋጅ ተደርጓል” ሲል የቀጣዩ ዓመት በጀት ዝግጅት በግብዓትነት የወሰደውን ሌላኛውን ጉዳይ ጠቅሷል።

በእነዚህ መነሻዎች የተዘጋጀው የቀጣይ ዓመት የአገሪቱ በጀት፤ መደበኛ እና ካፒታል ወጪዎችን እንዲሁም ለክልሎች የሚሰጥ እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ የሚውል ድጋፎችን የያዘ እንደሆነ መግለጫው ያስረዳል። ተጠባባቂ ወጪም በበጀቱ ውስጥ መካተቱንም አክሏል።

እነዚህን ወጪዎች ያካተተው እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው በጀት “ወደ አንድ ትሪሊየን [ብር] የሚጠጋ” እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።

“ምክር ቤቱም በቀረበው የፌዴራል መንግሥት የ2017 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል” ሲል የምክር ቤቱን ውሳኔ አስታውቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ የበጀቱን ትክክለኛ ቁጥርም ሆነ የበጀቱን ድልድል አልጠቀሰም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ምንጭ ለቀጣዩ ዓመት የተዘጋጀው በጀት 971.2 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ገልጸዋል። ለ2017 በጀት ዓመት የተዘጋጀው ይህ የገንዘብ መጠን ከዘንድሮው ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የ169.5 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው።

የዘንድሮው ዓመት በጀት ሲጸድቅ ከ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት ጋር የነበረው ብልጫ የ15.04 ቢሊዮን ብር ነበር። የ2016 ዓ.ም. በጀት ሲዘጋጅ የመንግሥት መደበኛ ወጪ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የካፒታል ወጪ በአንጻሩ ከ2015 ዓ.ም. አንጻር እንዲቀንስ ተደርጎ ነበር።

ከ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት አንስቶ ያሉት ሦስት ዓመታት የበጀት ድልድል ሲታይ በበጀቱ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የፌደራል መንግሥት መደበኛ ወጪ ነው።

በመጪው የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመትም “ባለው የበጀት ጥበት” ምክንያት አዳዲስ የካፒታል ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የበጀት ዕቅድ ስሚ በተካሄደበት ጊዜ እንደተገለጸ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

የዩኒቨርስቲዎች የበጀት ዕቅድ በቀረበበት ወቅት ደግሞ “በአፈጻጸማቸው የተሻሉትን ፕሮጀክቶች ለይቶ ማጠናቀቅ እና ዝቅተኛ አፈጻጸም ኖሯቸው የተቋረጡትን ደግሞ ባሉበት እንዲቆዩ ማድረግ የመጪው ዓመት የበጀት አቅጣጫ” እንደሆነ ተገልጾ ነበር።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *