“ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ የፖለቲካ ቡድን” በፓርቲነት ለመመዝገብ የሚያቀርበውን ማመለከቻ ውድቅ የማድረግ ሥልጣንን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማይሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 27/2016 ዓ.ም. ለተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበው እና በሥራ ላይ ያለውን “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ” የሚያሻሽለው ረቂቅ ከአምስት ዓመታት በፊት የወጣውን የምርጫ አዋጅ የሚያሻሽል ነው።

ማሻሻያው ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ተሳትፎ የነበረ ፖለቲካ ቡድን በፓርቲነት የሚመዘገብበትን ሂደት እና የምርጫ ቦርድን ሥልጣንን ያካተተ ሲሆን፣ የምዝገባውን ጥያቄው ውድቅ የማድረግ ሥልጣንን ግን ለቦርዱ አልሰጠም።

ነገር ግን በቀረበው የአዋጁ ማሻሻያ ላይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የገባን ፓርቲ “በልዩ ሁኔታ” ለሁለት ዓመታት “ልዩ ክትትል” እንዲያደርግ ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ቢቢሲ የተመለከተው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ማሻሻያው ያስፈለገው “ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ . . . ፍላጎት ቢያሳዩ እነዚህን አካላት ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ሥርዓት” በነባሩ አዋጅ ባለመካተቱ መሆኑን ያትታል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበው ረቂቅ በነባሩ አዋጅ ውስጥ ያሉ ሦስት አንቀጾች ላይ አዳዲስ ንዑስ አንቀጾችን ጨምሯል።

አዲስ ንዑስ አንቀጽ የተጨመረበት የመጀመሪያው የአዋጁ ድንጋጌ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ የሚመለከተው የነባሩ አዋጅ አንቀጽ ነው።

ማሻሻያው “ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባር” ውስጥ ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በፓርቲነት ሊመዘግብ የሚችልበትን ሂደት ያስቀምጣል።

የአዋጁ ማሻሻያ “ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ይላል።

በፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ ስለሚቀርብ ማመልከቻ የሚደነግገው የአዋጁ አንቀጽም አዲስ ንዑስ አንቀጽ ተጨምሮበታል።

በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ የሚያመለክት ቡድን፤ “ከምዝገባ ማመልከቻ በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም፣ የፖለቲካ ፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ፣ የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች ስም እና አድራሻ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች በኃላፊነት ለመሥራት መስማማታቸውን የሚያስረዳ በፊርማቸው የተረጋገጠ ሰነድ” ማቅርብ እንደሚኖርበት ማሻሻያው አመልክቷል።

በተጨማሪም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ኃላፊነት የሚያትተው አንቀጽ ስር ሁለት ንዑስ አንቀጾች ተካትተዋል።

በእነዚህ ንዑስ አንቀጾች መሠረት ምርጫ ቦርድ “በአመጽ ተግባር” ሲንቀሳቀስ የነበረ ቡድን ማመልከቻቸውን ባቀረበ 15 ቀናት ውስጥ ቦርዱ ምዝገባውን እንደሚፈጽም ሰፍሯል።

በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ “በዚህ ድንጋጌ መሠረት ምርጫ ቦርድ የቀረበውን ማመልከቻ ውድቅ የማድረግ ምርጫ አልተቀመጠለትም ማለት ነው” ይላል።

ቦርዱ በመደበኛው ሥርዓት በፓርቲነት ለመመዘገብ ማመልከቻ የሚያቀርቡ ቡድኖችን ጥያቄ ውድቅ የማድረግ ሥልጣን አለው።

ማብራሪያው አክሎም “ቦርዱ አመልካቹን በቀጥታ ያለምንም ማጣራት የሚመዘግበው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ክትትል እና ቁጥጥር የሚያደርግበት ሥርዓት ተደንግጓል” ይላል።

የቦርዱን ክትትል አፈጻጸም በተመለከተ የአዋጅ ማሻሻያው፤ “በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተመዝገበው ፓርቲ የፖለቲካ ሰነዶች ከዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ፣ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ወይም ሌሎች መሰል የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ለፓርቲው አስፈላጊውን ትዕዛዝ ይሰጣል።”

ቦርዱ በቀሪዎቹ ጊዜያት የፖለቲካ ፓርቲው “ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ” ክትትል የማድረግ እና ግብረ መልስ የመስጠት ኃላፊነት አለበት።

የማሻሻያ ረቂቁ አክሎም “ፓርቲው በተሰጠው ግብረ መልስ መሠረት መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ካላስተካከለ እና ጉልህ የሕግ ጥሰት የፈፀመ ከሆነ ቦርዱ የተለየ አካሄድ ሳይከተል የፓርቲውን ምዝገባ የመሰረዝ ሥልጣን ይኖረዋል” ሲል ያክላል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነትን ያበቃው በመንግሥት እና በህወሓት መካከል ከተደረሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል።

ይህ የምርጫ አዋጅ ማሻሻያ እንዲደረግ ምክንያት የሆነው ይኸው የህወሓትን ጥያቄን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የሕግ መሠረት ባለመኖሩ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

በሥራ ላይ ያለው የምርጫ አዋጅ “የፖለቲካ ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር፣ ከሙስና ጋር ተያያዥነት ያላቸው የወንጀል ድርጊቶች እና የማጭበርበር ድርጊቶች የፈጸመ እንደሆነ” ከምዝገባ ሊሰረዝ እንደሚችል ይደነግጋል።

ቦርዱ ይህን ድንጋጌ በመጥቀስ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) ሕጋዊ ሰውነት ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት በጥር 2013 ዓ.ም መሰረዙ ይታወሳል።

ምርጫ ቦርድ በወቅቱ “የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉም” ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ እና ህወሓት የተጣለበት የሽብርተኝነት ፍረጃ ከተነሳ በኋላም፤ ምርጫ ቦርድ የፓርቲው ሕጋዊ እውቅና እንዲመለስ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ መቆየቱ ይታወሳል።

ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ ይህንኑ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ለህወሓት መሰረዝ ምክንያት የሆነው “ኃይልን መሠረት ያደረገው የአመጻ ተግባር” እንደሌለ ጠቅሷል።

ይሁንና በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ላይ የፓርቲውን ሕጋዊ እውቅና ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች ባለመኖራቸው ጥያቄው “በሕግ የተደገፈ ሆኖ እንዳላገኘው” ቦርዱ አስታውቆ ነበር።

ህወሓት በድጋሚ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ በፖለቲካ ፓርቲነት መንቀሳቀስ የሚችለው “በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ” እንደሆነም በቦርዱ ውሳኔ ላይ ተጠቅሷል።

ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ግን በህወሓት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ህወሓት ከዚህ ውሳኔ መገለጽ ከቀናት በኋላ ባወጣው መግለጫ ውሳኔው “በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የሆነውን የህወሓት ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ” ያለመ ነው በሚል ምርጫ ቦርድን ከስሶ ነበር።

ውሳኔውን “በሕግም በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም” ሲል ያጣጠለው ህወሓት፤ የቦርዱ ውሳኔ “የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የሰላም መንገድ ለመደገፍ ሕግን በአወንታዊ የትርጉም ሥርዓት ከመረዳት ይልቅ፤ ቴክኒካዊ በሆነ አረዳድ” ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቅሶ ነበር።     ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *