በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ሆሮ ጉዱሩ ውስጥ የእርሻ ማሳ ላይ ወድቋል የተባለ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ተንቀሳቃሽ ምሥል እና ፎቶ በስፋት ሲሠራጭ ነበር።

የቢቢሲ ቬሪፋይ (የመረጃ ማጣሪያ) ቡድን አባላት ከጦርነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ከሚተነትኑ ባለሙያዎች ጋር በመሆን እነዚህ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሠራጩ ምሥሎችን ፈትሸው ወድቋል የተባለው ድሮን ባይራክተር ቲቢ 2 የተባለ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውል እንደሆነ አረጋግጠዋል።

ሲባይላየን የተሰኘው እና በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ባደረገው ተቋም የሚሠሩት ቤኔዲክት ማንዚን ደግሞ በምስሉ ላይ የሚታየው “ንብረትነቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሆነ ቲቢ2 ባይራክተር ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለሙያው አክለውም “ኢትዮጵያ፤ ቱርክ፣ ኢራን እና ቻይና ሠራሽ የሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አንስቶ መጠቀም መጀመሯ ይታወቃል” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በቅድሚያ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ በማስከተልም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ውስጥ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች ላይ በሚያካሄዳቸው ዘመቻዎች ላይ በስፋት እንደሚጠቀም ባለሙያው አክለዋል።

የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላም ሠራዊታቸው ድሮኖችን በታታቂዎች ላይ እንደሚጠቀም ከወራት በፊት መናገራቸው ይታወሳል።

ማኬንዚ ኢንተለጀንስ የተባለው ተቋም ባለሙያ የሆኑት ዴቪድ ሄዝኮት ደግሞ፣ በምስሉ ላይ የሚታየው ባይራክታር ቲቢ2 የተሰኘው ሰው አልባ አውሮፕላን መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አክለውም “ምንም እንኳ ይፋዊ መረጃ ባይኖርም የኢትዮጵያ አየር ኃይል በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንዳሉት ይነገራል። ይህ ደግሞ ከእነርሱ መካከል አንዱ ስለመሆኑ ብዙም አጠራጣሪ አይደለም” ብለዋል።

ቤኔዲክት “በሰው አልባ አውሮፕላኑ ጎን ላይ ‘ዴንጀር ፕሮፔለር’ የሚል ጽሑፍ አለው፤ ይህ ደግሞ ባይራክተር2 ድሮኖች ላይ የሚገኝ ነው” ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከቱርክ ሠራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተጨማሪ እኤኤ በ2021 ኢራን ሠራሽ ሞሃጀር-6 ድሮኖች ባለቤት መሆን ችሏል።

ኢትዮጵያ ምን ያህል ሠው አልባ አውሮፕላን ባለቤት እንደሆነች እስካሁን ድረስ በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሆሮጉዱሩ ወድቋል ስለተባለው ስለዚህ ሰው አልባ አውሮፕላን እስካሁን ድረስ ያለው ነገር የለም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለቱም ባለሙያዎች ሰው አልባ አውሮፕላኑ በመሳርያ ተመትቶ ስለመውደቁ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ በምሥሉ ላይ እንደሌለ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ዴቪድ “ተመትቶ የወደቀ አይመስለኝም” ብለዋል።

የሲባይላየን (Sibylline) ድርጅት ባለሙያው ቤኔዲክት ደግሞ “ተመትቶ ስለመውደቁ የሚያሳይ ምንም ዓይነት መረጃ የለም። ሰው አልባ አውሮፕላኑ ሙሉ በሙሉ አልወደመም። የደረሰበት ትልቅ ጉዳት በፍጥነት እየበረረ ባለበት ወቅት በመከስከሱ የመጣ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ባለሙያዎቹ ሰው አልባው አውሮፕላን በአካባቢው ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ለማጥቃት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰው፣ “በመሳርያ ተመትቶ ወደቀ ብንል የወደቀው ሰው አልባ አውሮፕላን ላይ ከባድ ጉዳት መመልከት መቻል ነበረብን” ይላሉ።

አክለውም “በአነስተኛ መሳርያ ተመትቶ ቢሆን እንኳ በአካሉ ላይ ጭረት መታየት ነበረበት” ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋራው ምሥል ላይ ከወደቀው ባይራክተር ቲቢ 2 ድሮን ጎን ሁለት ያልፈነዱ ሚሳኤሎች ይታያሉ።

የቢቢሲ ቬሪፋይ ቡድን አባላት ሁለቱ ሚሳኤሎች ሰው አልባ አውሮፕላኑ ታጥቋቸው የነበሩ ኤምኤኤም-ኤል (MAM-L) የተሰኙ ሚሳኤሎች መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አክለውም ሰው አልባ አውሮፕላኑ የተከሰከሰበትን ሁኔታ አይቶ ሚሳኤሎቹ ሳይተኮሱ መቅረታቸውን መናገር እንደሚቻል ገልጸዋል።

የሲባይላየን ተቋም ባለሙያ ቤኔዲክት፣ ሰው አልባ አውሮፕላኑ ተሸክሞት መብረር እንዲችል የተሠሩት ሚሳኤሎች (MAM-L) እንደሚባሉ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ሳይተኮሱ የወደቁት ሚሳኤሎች በደርስባቸው ስብራት የተነሳ አሁን በቀጥታ አገልግሎት ላይ ላይውሉ ቢችሉም የመጠገን ዕድል ግን አላቸው ሲሉ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩትን ተንቀሳቃሽ ምሥል እና ፎቶ መሠረት በማድረግ ሰው አልባ አውሮፕላኑ መቼ እና የት እንደተከሰከሰ ለጊዜው ማረጋገጥ አልቻለም።

ባይራክተር 2 ምን ያህል ይጓዛል?

ይህ 150 ኪሎ ግራም የሚመዝን ተተኳሽ ተሸክሞ መጓዝ የሚችለው ባይራክተር ቲቢ2 ድሮንን በ300 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ በመሆን መቆጣጠር ይቻላል።

ይህም ማለት ከመቆጣጠሪያ ጣቢያው በ300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመሆን የሚሰጠውን ግዳጅ መፈጸም ይችላል።

ባይራክትር ቲቢ 2ን እንደሚያመርተው ኩባንያ መረጃ ከሆነ የሰው አልባው አውሮፕላን የኋላ አካል (ጭራ) ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ 12 ሜትር ይረዝማል።

ይህ ሰው አልባ አውሮፕላን ያለምንም የሰው እርዳታ መነሳት እና ማረፍ የሚችል ሲሆን፣ ከ18 ሺህ እስከ 27 ሺህ ጫማ ከፍታ ድረስ መብረር ይችላል።

ይህ ሰው አልባ አውሮፕላን አራት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ወይንም ሮኬቶችን የመታጠቅ አቅምም አለው።

ድሮኑ በሰዓት 220 ኪሎ ሜትር እየበረረ ለ27 ሰዓታት ያህል አየር ላይ ሊቆይ ይችላል።

አንድ ባይራክተር ምን ያህል ያወጣል?

አንድ ባይራክተር ቲቢ2 ቱርክ ሠራሽ ሰው አልባ አውሮፕላን ከ5 እስከ 6 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ የተተመነለት ሲሆን፣ አብሮት ከሚሸጡት የተለያዩ መሳሪያዎች እና አገልግሎቶች ጋር ከሆነ ከዚያ በላይ እንደሚሆን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል።

እንደ ቤኔዲክት ከሆነ የሰው አልባ አውሮፕላኑ ዋጋ፤ ጥገና እና ሌሎች አገልግሎቶችን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሻጩ ኩባንያ በግዢ ወቅት እንደተስማሙበት የዋስትና ሁኔታ ይወሰናል።

የሰው አልባ አውሮፕላኑ አምራችም ሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ስለዚህ ድሮን ዋጋ እስካሁን ድረስ በይፋ ያሉት ነገር የለም።

ባይራክተር ዩክሬንን አንድ ባይራክተር ቲቢ2 ለማስታጠቅ ከ5 እስከ 5.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተከፈተውን የገቢ ማሰባሰብያ ዘመቻ በድረገፁ ላይ አጋርቷል።

የሲባይላየን ባለሙያው ቤኔዲክት፣ ሰው አልባ አውሮፕላኑ የሚያስወነጭፋቸው ሮኬቶች የእያንዳንዳቸው ዋጋ ከ 60,000 እስከ 100,000 ዶላር አንደሚገመት ተናግሯል።

ይህም ማለት እያንዳንዱ ድሮን ታጥቆ የሚሰማራው ሚሳኤሎች ዋጋ 3.5 ሚሊዮን ብር ይገመታል ማለት ነው።

ቢቢሲ በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችን ተከስክሷል ስለተባለው ሰው አልባ አውሮፕላን ጉዳይ ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ የሚባሉት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላትም ሆኑ የሰው አልባው አውሮፕላኑ ባለቤት ነው የተባለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም እስካሁን ያሉት ነገር የለም።       ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *