የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከአዋሳኝ የአፋር ክልል የመጡ ናቸው ያላቸው ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰባት የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን ገለጸ።

ግድያው የተፈጸመው በክልሉ ሃወልቲ ግራ ዋስተ አቅራቢያ ዒላ ቡብ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በነበሩ ሰባት እረኞች ላይ መሆኑን የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ስለጥቃት ፈጻሚዎቹ እና ስለተገደሉት ሰዎች ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም፣ የገዳዮቹን ማንነት ለማጣራት ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

የክልሉ መንግሥት በጥቃቱ ስለተገደሉ ሰዎች ቢገልጽም ከክስተቱ ጋር ተያይዞ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ያለው ነገር የለም።

የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እረኞቹ እድሜያቸው ከ11 እስከ 18 ዓመት ሲሆን፣ በአካባቢው ከብት ጥበቃ ላይ ተሰማርተው ነበር።

በአፋር እና በትግራይ ክልሎች መካከል በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች ሲያጋጥሙ የቆዩ ቢሆንም በሰላማዊ ሰዎች ላይ እንዲህ ዓይነት ጥቃት መፈጸሙ ግን “በጣም አሳዛኝ ነው” ብለዋል አስተዳዳሪው።

ጥቃቱ ግንቦት 12/2016 ዓ.ም. ሌሊት በመፈጸሙን የገለጹት አቶ ሃፍቱ፣ እረኞቹ በጥቃት ፈጻሚዎቹ በጥይት መገደላቸውን ገልጸዋል።

“ይህ አሳዛኝ ነው፤ የሁለቱንም ሕዝቦች ማኅበራዊ ሕይወት የሚጎዳ ነገር ነው። ከዚህ በፊት በመካከላችን ልጆችን የመግደል ድርጊት አልነበረም። ግጭት ቢፈጠር እንኳን በዚህ መልኩ ብቀላ አይፈጸመም፤ ይህ አደገኛ ነው” በማለት በክስተቱ ማዘናቸው ገልጸዋል።

ጥቃቱ ከአፋር ክልል በመጡ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈፀመ ነው የተባለ ሲሆን፣ ቢቢሲ ከአፋር ክልል መንግሥት በኩል በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማድረግ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የደቡብ ትግራይ ዞን አስተዳደር ከሚመለከታቸው የአፋር ክልል አካላት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሃፍቱ፣ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ሊኮነን እንደሚገባ ተናግረዋል።

“እንደ መንግሥት ዝም ብለን ልናየው አይገባም፤ በሕግ እንዲያዙ እናደርጋለን። የአፋር እና የፌደራል መንግሥትም ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ሊሰሩ ይገባል።”

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለአፋር ክልል እና ለፌደራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።

በትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ ካለው የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ባለፈ በተለያዩ አካባቢዎች ዘረፋ እና እገታ እንዲሁም ከፍተኛ የፀጥታ እንዲሁም የደኅንነት ስጋት ሰፍኖ እንዳለ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በተደራጀ መልኩ በታጠቁ ግለሰቦች የሚፈጸም ዘረፋ እና ግድያ እየተለመደ የመጣ ሲሆን፣ የግለሰቦች ደኅንነት በየቀኑ አደጋ ላይ እየወደቀ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸው ነበር።

የራያ-አዘቦ አካባቢ በትግራይ ደቡባዊ ክፍል የሚገኝ ሲሆን፣ ከአጎራባቾቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ጋር ይዋሰናል።     ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *