በሰሜን ጎንደር ዞን አለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች አንድ ኤርትራዊ ስደተኛን አግተው ከወሰዱ በኋላ እንደገደሏቸው ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ።

ተገድለው የተገኙት ስደተኛ ለምለም በርሔ የተባሉ የ50 ዓመት ግለሰብ ባለትዳር እና የሰባት ልጆች አባት እንደነበሩ ባለቤታቸው አብርኸት ምላሽ ለቢቢሲ ትግርኛ ገልጸዋል።

ግለሰቡ ተገድለው የተገኙት ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 10/2016 ዓ.ም. መሆኑንም ባለቤታቸው ተናግረዋል።

ባለቤታቸው በታጣቂዎች በተወሰዱበት ዕለት ሴት ልጃቸውን ለማሳከም አዲስ አበባ ሄደው እንደነበር የገለጹት አብርኸት፣ ሁኔታውን ከልጆቻቸው እና ከጎረቤቶቻቸው መስማታቸውን አስረድተዋል።

“አራት የሚሆኑ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት አርብ አመሻሽ ወደ መጠለያ ጣቢያው ገቡ። ከዚያ ከመጠለያ ጣቢያው አስወጥተው ነው የወሰዱት። አስከሬኑም ቅዳሜ [በማግስቱ] በረሃ ነው ተገኘ” ሲሉ ገልጸዋል።

ልጃቸው የነገራቸውን መረጃ በማጣቀስም ታጣቂዎቹ መጀመሪያ ወደ ጣቢያው ሲገቡ “ምን አላችሁ? ሞባይል የት አለ?” ብለው ከጠየቁዋቸው በኋላ፤ አቶ ለምለምን “እንፈልግሃለን” ብለው ይዘውት ሄደዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

አክለውም “ልጄ ሁለቱ ታጣቂዎች ቀድመው እኔን ያዙኝ፣ ሌሎች ሁለቱ ደሞ አባቴን ይዘውት ወጡ፣ ከዛ እኔን ይዘውኝ የነበሩ ታጣቂዎች እኔን ትተው እነሱን ተከትለዋቸው ሄዱ ብሎ ነግሮኛል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጎረቤቶታቸው ለፖሊስ ወዲያውኑ ሪፖርት አድርገው ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በተመባበር ፍለጋ ቢደረግም ምንም ውጤት አላመጣም ብለዋል።

ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በጣቢያው የሚኖሩ ቤተሰብ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት አርብ ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ መጥተው አቶ ለምለምን እንደወሰዷቸው አረጋግጠዋል።

በማግስቱ ከጣቢያው የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ ርቀት ባለው ጭላ በተባለ በረሃማ አካባቢ የግለሰቡ አስከሬን ተጥሎ እንደተገኘም አክለው አስረድተዋል።

“አስከሬኑ ወደ ህክምና ተቋም ከተወሰደ በኋላ እንድናረጋግጥ ተጠርተን ነበር። እሱ መሆኑንም አረጋግጠናል” በማለት ግለሰቡ ተናግረዋል።

አቶ ለምለም ከኤርትራ ከተሰደዱ 15 ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል በሚገኘው ማይአይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ኖረዋል።

ትግራይ ላይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በአካባቢው የነበሩ ስደተኞች ያለውን መከራ እና እንግልት ፈርተው ሲሸሹ አቶ ለምለም አማራ ክልል ወደሚገኘው መጠለያ ጣቢያ እንደመጡ ባለቤታቸው ተናግረዋል።

በትግራይ ጦርነት ምክንያት በርካታ ስደተኞች ግድያ፣ ዝርፊያ እና ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የተለያዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

ባለፈው ወር እንዲሁ በዳባት ወረዳ አንድ የ12 ዓመት ኤርትራዊ ስደተኛ ህጻን ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች መታገቱን ቤተሰቦቹ መናገራቸው ይታወሳል። ታዳጊው ከትምህርት ቤት ሲመለስ በታጣቂዎች ከታገተ በኋላ 200 ሺህ ብር ቤተሰቦቹ ከፍለው መለቀቁ ተነግሯል።

አለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ከትግራይ ክልል ለተፈናቀሉ የኤርትራ ስደተኞች ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመ ማዕከል ነው።

ማዕከሉ ከአቅም በላይ በመጨናነቁ በርካታ ቤተሰቦች ከማዕከሉ ወጣ ብሎ በዳባት ከተማ እንዲሰፍሩ መገደዳቸውን የአለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ማዕከል ፀሐፊ አቶ ዮሴፍ ገብረንጉሥ ለቢቢሲ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።

የታዳጊውን መታገት አስመልክቶ ቢቢሲ አቶ ዮሴፍን ባናገራቸው ወቅት እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች አዲስ እንዳልሆኑ እና ከዚህ ቀደም ወደ አምስት የሚጠጉ ህጻናት ታግተው መወሰዳቸውን እና ገንዘብ ተከፍሎ እንዲለቀቁ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የፀጥታው አሳሳቢነት በመጠለያ ጣቢያው ብቻ እንዳልሆነ እና በአካባቢው የሚገኙ ከተሞችም ዋስትና እንደሌላቸው ወ/ሮ አብረኸት ገልጸዋል።

“ፀጥታ የሚባል ነገር የለም፣ ጥበቃ የለም። ኡኡታ አሰምተንም የሚረዳ ሰው አይታሰብም፤ ወታደሮችም አይረዱም” ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የአካባቢውን ባለሥልጣናት ቢቢሲ ለማናገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ካለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ ባለፉት ስድስት ወራት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች የሚካሄደው ግጭት የቀጠለ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

በሁለቱ ኃይሎች መካከል በሚካሄደው ግጭት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሚደርሰው ጉዳት ባሻገር በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች አሳሳቢነት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድርጅቶች እየተገለጸ ይገኛል።

ስደተኞቹ ግጭቱ ለደኅንነታቸው አስጊ እንደሆነና በአካባቢው እየደረሰ ያለው አፈና እና የፀጥታ ችግር ለተለያዩ ችግሮች እያጋለጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *