የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ፤ ወረዳዎች በከተማዋ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የነበራቸው ሥልጣን ላይ ገደብ አስቀመጠ።

በአዲሱ አሠራር መሠረት ወረዳዎች በራሳቸው ውሳኔ የንግድ ቦታዎችን ማሸግ የሚችሉት ከንግድ ፈቃድ ጋር በተያያዙ ሁለት ጥሰቶች ተፈፅመው ሲያገኙ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ይህን አሠራር ያስተዋወቀው አዲስ ባወጣው “በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሠራር ሥርዓት መመሪያ” ላይ ነው።

መመሪያው፤ የከተማዋ ንግድ ቢሮ፣ ክፍለ ከተሞች ወይም የወረዳ ጽህፈት ቤቶች በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች አሠራር ላይ የሚያደርጉትን የቁጥጥር ሥራ ተፈጻሚነት ያለው እንደሆነ አስፍሯል።

ባለፈው ሳምንት በፍትህ ሚኒስቴር የምዝገባ ሂደቱን ያጠናቀቀው ይህ መመሪያ የወጣው፤ በከተማዋ በነጋዴዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን “ፍትሐዊነትን” በተመለከተ “አልፎ አልፎ የሚነሱ ችግሮች” በመኖራቸው እንደሆነ የንግድ ቢሮ የንግድ ክትትል እና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ስጦታው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በተለይ ከእርምጃ አወሳሰድ ፍትሐዊነት ጋር ተያይዞ እና ጤናማ ሂደቱን ከመጠበቅ ጋር ተያይዞ እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮች አሉ። ‘አላግባብ ታሸገብን፣ አላግባብ ተከፈተ’ የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ” ሲሉ ቢሮው ከእርምጃ አወሳሰድ ጋር በተያያዘ ቢሮው የተመለከታቸውን ችግሮች አብራርተዋል።

የንግድ ቦታዎችን ካሸጉ በኋላ ለማስከፈት የገንዘብ ድርድር ማድረግም ቢሮው “የሥነ ምግባር ብልሽት” ባለባቸው “ውስን ሠራተኞች” ላይ የተመለከተው እና መመሪያው ለመውጣቱ አንዱ መነሻ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ አክለዋል።

ምክትል የቢሮ ኃላፊዋ እንደሚያስረዱት ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ወረዳዎች ጥሰት ተብለው በሕግ የተቀመጡ ድርጊቶች ላይ እርምጃ ሲወስዱ ነበር።

ወረዳዎች፤ በነጋዴዎች ላይ እስከ ማሸግ የሚደርስ እርምጃ ሲወስዱ ከነበሩባቸው ጥሰቶች ውስጥ “የእቃዎች ዋጋ ዝርዝር አለመለጠፍ፣ ደረሰኝ አለመቁረጥ፣ ጤናማ ያልሆኑ ምርቶችን ማቅረብ፣ አድራሻ ለውጥ አለማሳወቅ እና ትክክለኛ የመለኪያ መስፈሪያ አለመጠቀም” እንደሚገኙበት ቅድስት ዘርዝረዋል።

ይህንን አሠራር የሚቀይረው አዲሱ መመሪያ እርምጃ መውሰድን በተመለከተ “የኃላፊነት ክፍፍል” ያስቀመጠ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

መመሪያው፤ የክትትል እና ቁጥጥር ባለሙያዎች በነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር የሚያደርጉባቸውን 25 ጉዳዮችን የዘረዘረ ነው። ከእነዚህም ውስጥ ከንግድ ፈቃድ፣ ከደረሰኝ፣ ከጤና፣ ከመለኪያዎች እንዲሁም ከንግድ ቦታ አድራሻ ጋር የተያያዙ ጥሰቶች ይገኙበታል።

ይህንን ክትትል እና ቁጥጥር የሚያደርጉት በወረዳዎች የሚመደቡ ባለሙያዎች “የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የመስጠት እና የማሸግ” እርምጃ የሚወስዱት ከንግድ ፈቃድ ጋር በተያያዙ ሁለት ጥሰቶች ላይ እንደሆነ መመሪያው ደንግጓል።

በመመሪያው ላይ የወረዳ ባለሙያዎች እርምጃ እንደሚወስዱባቸው የተጠቀሱ ጥሰቶች፤ “የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳይኖር በንግድ ሥራ ላይ መሰማራት” እንዲሁም “የንግድ ሥራ ፈቃድ ሳያሳድሱ ወይም በታገደ ወይም በተሰረዘ የንግድ ሥራ ፈቃድ መነገድ” ናቸው።

ባለሙያዎች በእነዚህ ጥፋቶች ላይ እርምጃ ከመውሰዳቸው አስቀድሞ ለቅርብ ኃላፊ በፅሁፍ ማሳወቅ እንዳለባቸው መመሪያ ይደነግጋል። ከእነዚህ ውጪ ያሉ ጥፋቶች ተፈጽመው ሲገኙ ባለሙያው፤ “አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ሳይኖርበት በዚህ መመሪያ መሠረት ለቅርብ ኃላፊው በፅሑፍ ማሳወቅ” እንዳለበት የቢሮው አዲስ መመሪያ አስፍሯል።

በመመሪያው መሠረት በሌሎች የሕግ ጥሰቶች ላይ እርምጃ የሚወሰደው ወረዳዎች እና ክፍለ ከተሞች ለከተማዋ የንግድ ቢሮ የውሳኔ ሃሳብ አቅርበው ቢሮው “አስተዳደራዊ ውሳኔ” ሲሰጥ ነው።

የንግድ ፈቃድ ሳይኖር እንዲሁም ሕጋዊ ባልሆነ ንግድ ፈቃድ ከመሥራት ውጪ ያሉ ጥፋቶች ለውሳኔ ወደ ከተማዋ ንግድ ቢሮ መምጣታቸው የሚፈጥረው የሥራ ጫና ይኖር እንደሆነ ጥያቄ የቀረበላቸው ምክትል ኃላፊዋ ቅድስት፤ “ሥራውን [ወደ] የሚያፋጥንልን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምም ጭምር እየገባን ስለሆነ እንወጣዋለን ብለን እናስባለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

“ረጅም ጊዜ ሊያሠራ የሚችል ነገር በጥናት ታይቶ ነው የሚወጣው። የማያስኬዱ ነገሮች አይፈጠሩም ተብሎ አይገመትም። እንደ እርሱ ዓይነት ነገሮች በሂደት የሚያጋጥሙ ከሆነ ደግሞ [መመሪያውን] መልሰን የምናየው ይሆናል” ሲሉም አክለዋል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መመሪያውን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ፤ በሚቀጥለው ሳምንት ይህንኑ መመሪያ የተመለከተ ሥልጠና ለሚመለከታቸው አካላት እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል።

ቢቢሲ ከአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማዋ ንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ከ400 ሺህ በላይ ነጋዴዎች ይገኛሉ።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *