የትግራይ ኃይል አባላትን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለማሰናበትና ከማህበረሰቡ ጋር ዳግም እንዲቀላቀሉ የሚያስችል የቅድመ ትግበራ ውይይት በመቀለ ተካሂዷል።

በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ በተካሄደው ምክክር ላይ የፌደራል መንግሥት ተወካዮች፣ የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት አመራሮች እና የአፍሪካ ኅብረት የስምምነት ክትትል፣ አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴ አባላት መገኘታቸውን የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በኤክስ ገጻቸው አስታውቀዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዚህ ምክክር ላይ የትግራይ ተዋጊዎችን በመበተን እና ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ወደ ኅብረተሰቡ የማዋሃድ ፕሮግራም፣ ፕሮጀክቶች መንደፍ እንዲሁም የመጀመሪያው የትግበራ እቅድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተጠቅሶ ነበር።

ጦርነቱ መቋጨቱን ተከትሎ ጥያቄ እያስነሳ ያለው ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ እና የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች፣ በጀት እና ሌሎችንም ጉዳዮች አስመልክቶ ቢቢሲ ከብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተስፋዓለም ይሕደጎ ጋር ቆይታ አድርጓል።

★★★

ቢቢሲ- የትግራይ ኃይሎች እና የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አዛዦች ትጥቅ መፍታት፣ ማሰናበት እና መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ የናይሮቢ የመግባቢያ ሰነድ ከተፈራረሙ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሆኗቸዋል። እነዚህን መዘግየቶች ያስከተሉት ነገር ምንድን ናቸው?

አቶ ተስፋዓለም፡ ለዚህ መዘግየት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው ምክንያት ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ውይይት አለመካሄዱ ነው።

ሁለተኛ ወደ ማህበረሰቡ ለሚቀላቀሉ የትግራይ ሠራዊት አባላት በቀጥታ በጀት ያስፈልጋል። እና በጀቱም በጣም ትንሽ አይደለም። ብዙ በጀት ይጠይቃል። ይህ በጀት በአገር ውስጥ አቅም ብቻ ሊሸፈን የሚችል አይደለም።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ያስፈልጋል። በዚህም መሰረት ቃል ገብተው የነበሩ አገራት እና አካላት በጊዜው ገቢ ያለማድረግ ችግር አለ፤ ሀብቱን በወቅቱ ማግኘት ላይ ክፍተት አለ። ስለዚህ የግብዓት እጥረት ስለነበር እስካሁን ዘግይቷል።

አሁን የፌደራል መንግሥት ሁሉንም ባይሆንም አራት ዙር በራሱ [በጀት] ለማሰናበት ተነሳሽነት ኣሳይቷል። የትግራይ መንግሥት እና የትግራይ ሠራዊት አመራሮችም ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው። የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽኑ ቦርድም አቅጣጫ አስቀምጦ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ ግብዓት ማሰባሰብ ችሏል።

በተጨማሪም መንግሥት የገቢ ማሰባሰብ ሥራዎችን እንዲያከናውን እና ሀብትን እንዲያንቀሳቅስ ከዚያም የአገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መጠን ሠራዊቱ መቋቋሚያ ተሰጥቶት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲመለስ ለማድረግ ሀሳብ ቀርቧል።

ነገር ግን የማስፈጸም አቅም ገና አልተፈጠረም። የመንግሥት ቁርጠኝነት እና እቅድ አለ፤ እንቅስቃሴም ተጀምሯል። ለምሳሌ የካናዳ መንግሥት 14 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብቷል። ስለዚህ የመዘግየቱ ዋና ምክንያት የሀብት እጥረት ነው።

ቢቢሲ፡ ፕሮግራሙን ለመሸፈን ቃል የገቡት አገሮች እነማን ናቸው?

አቶ ተስፋዓለም፡ ቃል የገቡ በርካታ አገሮች አሉ ከነዚህም መካከል አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ጀርመን እና ሌሎችም ይገኙበታል።

ቢቢሲ፡ ይህንን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ በአጠቃላይ ምን ያህል በጀት ያስፈልጋል?

አቶ ተስፋዓለም፡ የሚፈለገው ብዙ ነው። አስፈላጊው በጀት ተዘጋጅቷል። ነገር ግን ሲፀድቅ እና ይፋ ሲሆን ሌላ ግዜ እገልጻለሁ። የካናዳው ግን ራሳቸው ይፋ አድርገውታል። ሌሎችም ይኖራሉ። የሙከራ ፕሮጀክትም እየጀመርን ስለሆነ አንድ ነገር ሲፈቀድ እና ሲወሰን እንናገረዋለን።

ቢቢሲ፡ ትጥቅ መፍታት በመዘግየቱ ምክንያት በትግራይ አመራሮች እና በፌደራል መንግሥት መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል። መተማመን እንደሌለም በትግራይ ባለስልጣናት ተገልጾ ነበር። ይህ ከበጀት ችግር በላይ የሆነ ምክንያት አይደለም?

አቶ ተስፋዓለም፡ ይህ ለበጀት መዘግየት ምክንያት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም የፌደራል መንግሥት ኤጀንሲ አቋቁሟል። ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ለአፍሪካ ሕብረትም በይፋ አሳውቋል። ቦርድና ግብዓትም አቋቁሟል።

ለምሳሌ ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ የተሃድሶ ኮሚሽኑ የቦርድ አባል ናቸው። ስለዚህ የፌደራል መንግሥት እየሰራ ያለው እመርታ ነው። በመካከላቸው ስላለው ውጥረት ግን ምንም ፍንጭ የለኝም። ግን ሙሉ በሙሉ መተማመን ያለው የፖለቲካ ውይይት እንዳልነበር አውቃለሁ።

ቢቢሲ፡ የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ መፍታት፣ ማሰናበትና መልሶ ከማህበረሰቡ ቃል ማዋሃድ ሲባል ፓኬጁ ምንን ያካትታል?

አቶ ተስፋዓለም፡ አንደኛው ትጥቅ ማስፈታት ነው። እነዚህ ቀደም ሲል ከባድ፣ መካከለኛ እና ቀላል የጦር መሳሪያዎች ተብሎ ተከፋፍሎ ያስረከቡት አለ።

በተጨማሪም የትግራይ መንግሥት 50,000 የትግራይ ኃይሎች አባላትን ‘ዲሞቢላይዝ’ [ከጦሩ አሰናብቷል] አድርጓል። ስለዚህ ሲሰናበቱ አጭር ስልጠና፣ መሸኛና መቋቋምያ ተሰጥቷቸዋል።

ከሚመለከታቸው የክልልና የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የስልጠና፣ ብድርና የስራ ቦታ የሚያገኙበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸው ሙሉ በሙሉ የሚቋቋሙበትና ወደ ኑሯቸው የሚመለሱበት መንገድ ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል።

ይህ ማለት በጣም የተትረፈረፈ ይሰጣቸዋል ማለት አይደለም። ነገር ግን አሁን ያለው የአገሪቱ አቅምን መሰረት በማድረግ ወደ ሙያቸው ተመልሰው… እንደ ትግራይን መልሶ የመገንባት አንድ አካል ተወስዶ የሚቋቋሙበት መንገድ ይፈጠራል።

ቢቢሲ፡ ሠራዊቱ በዚህ ደም አፋሳሽ ጦርነት ብዙ የአእምሮ ጉዳት (ትራውማ) ደርሶበታልና የሚሰጠው ስልጠናው በምን ላይ ያተኮረ ነው? ሠራዊቱ ወደ ፌደራል መንግሥት ካምፖችስ ይገባል?

አቶ ተስፋዓለም፡ ጦርነቱ በትግራይ ስነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ አካላዊ፣ ሕይወት መጥፋትና ጾታዊ ጉዳት አድርሷል። ይህ እንዳለ ሆኖ ሠራዊቱ ‘ሳይኮሶሻል’ [ስነልቦናዊ አዕምሯዊ] ሥልጠና ይሰጠዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መመሪያ አዘጋጅቶ ከብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ጋር ተፈራርሟል።

ከጦርነቱ በኋላም ሆነ በጦርነቱ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን የሥነ ልቦና ችግሮች እንዴት እንደሚቋቋሙ፣ ያላቸውን ሕክምና እንዴት እንደሚቀጥሉ እና የሲቪል ሕይወት እና የፍትሐ ብሔር ሕግን እንዴት አክብረው እንደሚኖሩ ‘ሳይኮሶሻል’ [ስነ ልቦናዊ እና አዕምሯዊ] ስልጠና ይሰጣቸዋል።

እነዚህን ስልጠናዎች በትግራይ ካምፕ ይወስዳሉ።

ቢቢሲ፡ ለእያንዳንዱ የሠራዊቱ አባል የሚሰጠው መቋቋሚያ ምን ያህል ነው?

አቶ ተስፋዓለም፡ እስካሁን አልተወሰነም።

ቢቢሲ፡ ለዚህ ፕሮግራም ግልጽ የሆነ የጊዜ ገደብ አለ? መቼ ነው ተግባራዊ የሚሆነው?

አቶ ተስፋዓለም፡ በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት አለ። እኛ ግን ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና ከትግራይ ሠራዊት አመራር ጋር እየተነጋገርን ነው። መልሰን ለፌደራል መንግሥት እናቀርባለን። ዕቅዱን ግልጽ ካደረግን በኋላ በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን እንፈልጋለን።

ቢቢሲ፡ በአሁኑ ሰዓት ስንት የትግራይ ኃይል አባላት ትጥቅ እንዲፈቱና እንዲቋቋሙ ነው የታሰበው?

አቶ ተስፋዓለም፡ የትግራይ ሠራዊት ከላይ ከትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ ኮማንድ ጀምሮ እስከ ታች የተደራጀ ነው። ከዚህ በመነሳት ከኬንያ ፕሮቶኮል ጀምሮ በትግራይ የጸጥታ ኃይሎች እና በመከላከያ ሠራዊት (ፌዴራል) መካከል የጠበቀ ግንኙነት አለ። 274 ሺህ 800 የትግራይ ሠራዊት አባላት ትጥቅ ይፈታሉ።

ቢቢሲ፡ ወደ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚቀላቀሉ የትግራይ ኃይል አባላት ይኖሩ ይሆን?

አቶ ተስፋዓለም፡ በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ ስለሰፈረ ይኖራሉ። ወደነበራቸው የክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥት ሥራ፣ ወደ ፌዴራል የጸጥታ ኃይል የሚመለሱና እና በትግራይ የጸጥታ ኃይል ውስጥ የሚቀሩ የትግራይ ኃይል አባላት ይኖራሉ።

ቢቢሲ፡ የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የመቋጨት ስምምነት እና የናይሮቢ የትግበራ ሰነድ የትግራይ ኃይሎች ከባድ የጦር መሳሪያ ትጥቅ የሚፈቱት የውጭ እና የፌደራል ያልሆኑ የጸጥታ ኃይሎች ከትግራይ ሲወጡ በተመሳሳይ ጊዜ እንደሆነ ይደነግጋል። አሁን የቅድመ ትግበራው ውይይት ያካሄዳችሁት እነዚህ ኃይሎች ከትግራይ ስለወጡ ነው?

አቶ ተስፋዓለም፡ ያ የሚፈጸመው በሌላ ነው። አንደኛው በፕሪቶሪያ ስምምነት ውስጥ በግልፅ ተቀምጧል። የሁለቱም ተደራዳሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገናኙ ነው። ይህ በትግራይ የሚኖረው የመላው ማኅበረሰብ ጥያቄ ነው፤ የሚሰናበተው የትግራይ ሠራዊት የሚያነሳው ጥያቄ ነው። ስለዚህ እንደ ግለሰብ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ተግባራዊ ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ። ግን የራሴ ስራ እንደሆነ አድርጌ መልስ ልሰጥበት አልችልም።

ቢቢሲ፡ በፕሪቶርያ ስምምነት ላይ የውጪ እና ከፌደራሉ ውጭ ያሉ ኃይሎች መውጣታቸውን ተከትሎ በተመሳሳይ ጊዜ ይፈጸማል የሚል አንቀጽ ስላለ ነው ይህንን ጥያቄ ያቀረብነው?

አቶ ተስፋዓለም፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ የፌዴራል መንግሥት እና የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት በሂደት ላይ እንዳሉ መረጃ አለን። በደቡብ ትግራይ የተጀመረ ነገር አለ። የትግራይ ምክትል ፕሬዝዳንትም ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተውበታል። እኔ ከጄኔራል ታደሰ የተለየ ማብራሪያ የለኝም። በቀጥታም የኔ ስራ አይደለም፤ ነገር ግን እንደ አንድ የመንግሥት አመራር አካል ለጥያቄው መልሱ ጄኔራል ታደሰ የሰጡት ነው።

ቢቢሲ፡ ጀነራል ታደሰ ወረደ በደቡብና ምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋም ስራ እስከ ሰኔ ወር ድረስ ተግባራዊ እንደሚሆን ብቻ ነው የገለፁት።

አቶ ተስፋዓለም፡ በፕሪቶሪያ ስምምነት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጪ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለ ማንኛውም የታጠቀ ኃይል መውጣት እንዳለበት ይደነግጋል። ስለዚህ ይህ መተግበር አለበት።

ይህ ተግባራዊ ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ። እና ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ መተግበር እንዳለበት ሀሳብ አቀርባለሁ።

የፌደራል መንግሥት፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የሚመለከታቸው የአፍሪካ ሕብረት እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አባላት ኤርትራን እና ሌሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን ለቅቀው እንዲወጡ ቁርጠኞች ናቸው። የትግራይ መንግሥትም ያምናል፤ በስምምነቱም ላይም ሰፍሯል።

ቢቢሲ፡ የፌደራል መንግሥት በአማራ ክልል ኃይሎች ከተያዙና አስተዳደራዊ መዋቅር ከተዘረጋባቸው የትግራይ አካባቢዎች በስተቀር እስካሁን በይፋ ሲናገርም እና አቋም ሲወስድ አልታየም። እናንተ እንደ ኮሚሽን እዚህ ላይ ምን ሰርታችኋል?

አቶ ተስፋዓለም፡ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ውጪ የታጠቁ ኃይሎችን የማስወጣት ተልዕኮ አልተሰጠንም። ወደፊትም እዚህ ላይ የምንሰራው ነገር የለንም።

ለሥራችን እንቅፋት ከሆነብን፣ ለምሳሌ ወደ ዛላምበሳ ‘ዲሞቢላይዝ’ [ከጦሩ የሚሰናበቱ] ታጋዮች አሉ። እነዚህ እንዴት ይሆናሉ? መኖርያ የላቸውም፤ የት ይቆያሉ? የሚለውን ጥያቄ እንጠይቃለን። ይህ ግን በፌዴራል መንግሥት እና በትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት የሚወሰን ነው።

አሁን ትግራይ እንደመጣን አንድ የተገነዘብነው ነገር አለ። ትናንት ‘ዲሞቢላይዝ’ [ከጦሩ የሚሰናበቱ] ከተደረጉት ውስጥ አንድ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ለማነጋገር በሄድንበት ወቅት፣ አንዲት የዛላምበሳ ሴት እና ሌላ እግሩ የተቆረጠ ደግሞ ከሁመራ ‘ወዴት ነው የምንሄደው?’ ሲሉ ጥያቄ አንስተውልን ነበር።

እነዚህ እንዴት እንደሚሆኑ ከሁሉም ጋር እንወያይበታለን። ነገር ግን ሠራዊቱን ማስወጣት ወይም አካባቢውን ማስለቀቅ ለእኛ የተሰጠ ተልዕኮ አይደለም።

ቢቢሲ፡ የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን በሰባት ክልሎች የሚገኙ 371 ሺህ 971 የቀድሞ ታጋዮችን መልሶ ለማቋቋም ከ760 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ከጥቂት ወራት በፊት ገልጾ ነበር። የትኞቹ ክልሎች ላይ ያሉ ናቸው የዚህ ትግበራ አካል የሚሆኑት? እናስ እነማን ናቸው?

አቶ ተስፋዓለም፡ በአማራና ኦሮሚያ ውስጥ ይኖራሉ። በተመሳሳይ መልኩ ጥያቄያችን በሰላማዊ መንገድ እንደሚመለስ ያመኑ፣ ወደ ሰላማዊ መንገድ የሚገቡ ትጥቃቸውን የሚፈቱ የትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ ላይ የሚገኙ ኃይሎችን ይመለከታል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *