በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው መዝገብ የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ፍርድ ቤት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ በፍርድ ቤት ታዘዘ።

ትዕዛዙን የሰጠው ዛሬ ግንቦት 5፤ 2016 ዓ.ም የዋለው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ችሎት ነው።

ችሎቱ ትዕዛዙን ያስተላለፈው ባለፈው መጋቢት ወር በዐቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው ግለሰቦች ከማረሚያ ቤቱ አያያዝ ጋር አቤቱታቸውን ካቀረቡ በኋላ መሆኑን ጠበቃቸው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሁለተኛ ተከሳሽ ሆነው በመዝገቡ የተካተቱት አቶ ክርስቲያን ታደለ “ለቀናት” ምግብ አለመመገባቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል

አቶ ክርስቲያን ምግብ ያልተመገቡት፤ በማረሚያ ቤቱ “አማራ ተከሳሾች ስለሆናችሁ እንደሌሎቹ ተከሳሾች አትስተናገዱም” በሚል የቤተሰብ ጥየቃ ሰዓት ላይ ለውጥ በመደረጉ መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል።

አቶ ክርስቲያን “ተለይተን ቤተሰብ የሚጠይቀን እና ምግብ የሚገባልን ከስድስት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት እንዲሆን ተደርገናል” በሚል አቤቱታ ማቅረባቸውን ጠበቃ ሔኖክ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው ምግብ ማግኘት አለመቻላቸውን የጠቀሱት አቶ ክርስቲያን፤ “ማረሚያ ቤቱ በፈጠረው ህጉን ባልተከተለ አሰራር ምክንያት ተቸገሬ እገኛለሁ” ማለታቸውን ጠበቃ ሔኖክ አክለዋል።

ሶስተኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት ዶ/ር ካሳ ተሻገርም በተመሳሳይ፤ “ የቀጠሮ እስረኞች ሆነን እያለ ነገር ግን ከፍርደኞች ጋር እንድንታሰር አድርጎናል” ሲሉ አቤቱታቸውን ለችሎቱ በቃል መግለጻቸውን ጠበቃቸው ገልጸዋል።

ዶ/ር ካሳ “መንግሥት አላግባብ በተለያየ ሚዲያ ከሰራው ዘገባ ጋር በተገናኘ ፍርደኞች እኛ ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት አድርሰውብናል” ማለታቸውን ሄኖክ ጠቅሰዋል።

ጠበቃ ሄኖክ አክለውም “ [ዶ/ር ካሳ] ለህይወታችን አደጋ እንዲደቀንብን ማረሚያ ቤቱ አድርጓል። ይሄ ትክክል አይደለም ብለው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ተከሳሾቹ በቃል ካቀረቡት አቤቱታ በተጨማሪ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር የተያያዘ አቤቱታቸውን በጽሁፍ ማቅረባቸውን ሄኖክ ተናግረዋል።

የተከሳሾችን አቤቱታ ያዳመጠው ፍርድ ቤት የዛሬውን የችሎት ውሎ ከማጠናቀቁ በፊት ትዕዛዞችን መስጠቱን አቶ ሄኖክ ጠቁመዋል።

የቀረቡ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መርምሮ አጣርቶ ውጤቱን ለፍርድ ቤቱ እንዲያሳውቅ ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሾች “ማረሚያ ቤቱ ከማንነታችን ጋር በተያያዘ በምሳ ሰዓት ብቻ እንድንጠየቅ ተደረግን” በሚል ላቀረቡት አቤቱታ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥ እና የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊ በአካል ቀርበው እንዲያስረዱ መታዘዙንም ጠበቃ ሄኖክ አስረድተዋል።

ማረሚያ ቤቱ ምላሽ እስከሚሰጥ ድረስ ተከሳሾች በመንግሥት የስራ ሰዓት ለሌሎች ተከሳሾች እንደሚደረገው በሰዓቱ እንዲስተናገዱም አዝዟል።

ከዚህ በተጨማሪ ዛሬ በንባብ ለተከሳሾች የቀረበው ክስ ላይ ያላቸውን የክስ መቃወሚያ እና የምስክሮች አቀራረብ እንዲሁም የዋስትና ጉዳይ እንዲያቀርቡ ለግንቦት 29፤ 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በአቶ ዮሐንስ ቧያሌው ስም በሚጠራው የክስ መዝገብ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት 52 ተከሳሾች ሲሆኑ 36ቱ ክስ የተመሰረተባቸው በሌሉበት ነበር።

ዐቃቤ ሕግ ክስ ከተመሠረተባቸው 52 ግለሰቦች መካከል፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር እንዲሁም የተቃዋሚው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ይገኙበታል።

ቢቢሲ የተመለከተው እና በ68 ገጾች የተዘጋጀው የዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ አራት ክሶች ናቸው። የዐቃቤ ህግ ክስ የወንጅል ህጉን፣ የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጣር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅን እና የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅን በመንተራስ የቀረቡ ናቸው።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *