የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአሜሪካ የሚኖሩ ‘ተፈላጊዎች’ ተላልፈው እንዲሰጡ ትብብር እንዲደረግ ለአሜሪካው አምባሳደር ጠየቀ።

የፌደራል ፖሊስ ጥያቄውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ለሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ ትናንትና ግንቦት 2/2016 ዓ.ም ማቅረቡን በዚያው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ኢትዮጵያ “የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት በማወክ እፈልጋቸዋለሁ” ያለቻቸውን ሰዎች ተላልፈው እንዲሰጧት ትብብር የተጠየቀውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል እና አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በትናንትናው እለት ባደረጉት ውይይት መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል “በአሜሪካን አገር ተቀምጠው የሃገራችንን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ተፈላጊዎችን አሳልፎ በመስጠት” ከአሜሪካ በኩል ትብብር እንዲደረግ ለአምባሳደሩ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

“የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ተፈላጊዎች” የተባሉት አካላት እነማን እንደሆኑ የፌደራል ፖሊስ መግለጫ አልጠቀሰም።

አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው አሜሪካ የምትፈልጋቸውን ወንጀለኞች የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አሳልፎ በመስጠት ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ማቅረባቸው ተጠቅሷል።

አገራቸውም ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተመሳሳይ ድጋፎችን እንድታደርግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ መናገራቸው በዚሁ መግለጫ ላይ ሰፍሯል።

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ወንጀለኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ባይኖራቸውም፤ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ትውልደ ኢትዮጵያዊውን እና በሁለት ሰዎች ግድያ አሜሪካ ስትፈልገውን የነበረውን ዮሃንስ ነሲቡ የተባለውን ግለሰብ አሳልፋ መስጠቷ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአሜሪካው የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ጋር ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር አምባሳደሩ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲ አምባሳደሩ ከኮሚሽነሩ ጋር መነጋገራቸውን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ተላልፎ በመሰጠት በኩል የጠቀሰው ነገር ባይኖርም በህዝብ እና ፍትህ አካላት ላይ ባለው የህግ አፈጻጸም ዙሪያ ተወያይተዋል ብሏል።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *