በምዕራብ ሐረርጌ ጅብ ከሰው ጋር በፍቅር መኖር ብቻ ሳይሆን ከእጁ ይበላሉ፣ ከአፉ ላይ ይጎርሳሉ።

በርግጥ በሐረር ጅቦች ከሰዎች ጋር ተላምደው፣ ስም ወጥቶላቸው የቱሪስት መስህብ ሆነዋል።

የምዕራብ ሐረጌዋ ትንሽ የገጠር ከተማ መሰላም የሆነው ይኸው ነው።

በዚህች የገጠር ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ውሻ ያሳደጉት በዋናነት የቤት እንስሶቻቸውን ከጅብ ለመጠበቅ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጅቦቹ እና ውሾቹ ተወዳጅተው አብረው መዋል ጀምረዋል።

ውሾቹ ጅቦቹን ሲያዩ አይጮሁም፤ አያባርሯቸውም። ያገኙትን ተካፍለው በልተው ሁሉም ወደ የማደርያቸው ይሄዳሉ።

መሰላ ጅብ እንዲከላከል ያሳደጋችሁት ውሻ፣ ከተማ መሀል ጅብን ወዳጅ አድርጎ ከስጋ ቤት ደጃፍ የሚጣልለትን ቅንጥብጣቢ ጥበቃ ሲንቀዋለል ልታዩት ትችላላችሁ።

በመሰላ ከተማ ጅብ እና ውሻ ከስጋ ቤቶች የሚጣልላቸውን አብረው ተሻምተው ሲበሉ ይታያሉ።

አቶ ቶፊቅ ኢብራሂም፣ በመሰላ ከተማ ስጋ ቤት አላቸው።

ጠዋት ከቄራ ስጋ ይዘው ሲመጡ ጅቦች እና ውሾች ልኳንዳ ቤታቸው ፊት ለፊት ተደርድረው የድርሻቸውን ለመቀበል ይጠብቋቸዋል።

“ሌሊት ሥጋ ይዘን ስንመጣ፣ ለነፍስ የሚጠብቁን ጅቦች እና ውሾች ብዙ ናቸው። በር ላይ ተኝተው ነው የሚጠብቁን። ቅንጣቢ ስንሰጣቸው ውሻውም ጅቡም በጋራ ነው የሚበላው።”

ውሾቹንም ጅቦቹንም መመገብ ከጀመሩ ሦስት ዓመት እንደሞላቸው የሚናገሩት አቶ ቶፊቅ፣ የጅቦች ቁጥር አንዳንድ ጊዜ ከውሾቹ ቁጥር በብዙ እጥፍ ይበልጣል ይላሉ።

በዚህ ከተማ ጠዋት ጠዋት ሰዉ ከጅብ አይሸሽም ጅቡም ከሰው እና ከውሻ አይርቅም።

ሁሉም “እየተገፋፉ” የመሰላን ከዶሮ ጉሮሮ የቀጠነ ጎዳና በጋራ ይጠቀማሉ።

በውሾቹ እና ጅቦቹ መካከል ግጭት እና መጯጯህ የለም ይላሉ የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቶፊቅ።

ጅቦቹ እዚያው የስጋ ቤቱ ደጃፍ አይውሉም፣ የጸሀይ መውጣትን ተከትሎ ሆዳቸው መሙላቱን ሲያረጋግጡ ቀስ ብለው በከተማዋ ዳርቻ ወደ ሚገኝ መዋያቸው፣ጫካ ለመኝታ ይሄዳሉ።

ይህ ክስተት በየቀኑ ማለዳ የሚስተዋል ስለሆነ አሁን አሁን በከተማዋ ነዋሪዎች ብርቅ እና ድንቅ ተደርጎ የሚታይ አይደለም።

የሸነን ዱጎ ወረዳ ኮሙኑኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ቡሽራ አሊ ይህንን የሰዎች፣ ጅቦች እና ውሾች ህብረት ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚናገሩት በከተማዋ ጅብ በቀን ሽር ብትን ይላል።

ጅቦቹ በከተማዋ የሚገኙ ፍየሎችን አይነኩም የሚሉት አቶ ቡሽራ “ክፍት በር ቢያገኝም አይገባም” ሲሉ ታማኝነቱን ይመሰክራሉ።

የመሰላ ጅብ ልክ እንደ ሐረር ከተማ ሁሉ ጅቦችን ስጋ ማብላት እየተለመደ ነው።

አቶ ቡሽራ እንደሚሉት ጅብ በጠራራ ጸሐይ በከተማዋ በስፋት መንቀሳቀሱ እስካሁን ነዋሪዎች ላይ ያሳደረው ችግር የለም።

ከውሾቹ ጋር ያለው ወዳጅነትም አግራሞትን የሚፈጥር ነው ይሉታል።

መሰላ ውስጥ እስካሁን በጅቦች የደረሰ ጉዳት ባይመዘገብም ከዚህ በፊት ግን በሐረርጌ የተለያዩ አካባቢዎች ጅቦች ጉዳት

ማድረሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *