በቅርቡ ትግራይ ውስጥ የቆላ ተምቤን ወረዳ አስተዳደር፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መሬት ላይ ተጥለው ወይ ተቀብረው ሳይፈነዱ የቀሩ የጦር መሳሪያዎች ባደረሱት አደጋ ከ100 በላይ ሰዎች ህይወታቸውንና አካላቸውን አጥተዋል ብሏል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ተስፋዬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ፈንጂ ያልተዘራበት አካባቢ የለም” ማለት ይቻላል።

በጦርነቱ ወቅት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመዋጋት የተሰማሩ የኢትዮጵያ መከላከያ፣ የአማራ ክልል ኃይል እና የኤርትራ ስራዊት በቆላ ተምቤን ወረዳ በሁሉም አካባቢዎች ገብተው ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ተክላይ ይህንን ተከትሎ በርካታ ቀላልና ከባድ መሳርያዎች ተጥለው መቅረታቸውን ገልጸዋል።

“ከሞላ ጎደል በሁሉም ጣቢያዎች ውስጥ የተቀበሩ እና ከመሬት በላይ ያሉ ፈንጂዎች አሉ። ጠላት [ጦሮቹ] ከአካባቢው ከወጣ በኋላ በወረዳችን 112 ንፁኃን ዜጎች ሕይወታቸውንና አካላቸውን አጥተዋል” ይላሉ።

በመኖሪያ አካባቢዎች፣ በእርሻ ቦታዎችና በሌሎች አካባቢዎች የተበተኑ ፈንጂዎች በነዋሪዎች በተለይም በህጻናትና በእንስሳት ሲነኩ እየፈነዱ አደጋ እያደረሱ እንደሆነ አስተዳዳሪው ይናገራሉ።

ልጆች ሳያውቁ እንደ መጫወቻ ሲጠቀሙባቸው፥ አዋቂዎች ደግሞ ብረታ ብረት ለይተው ለማውጣትና ለቤት ውስጥ መገልገያ የሚሆኑ እቃዎችን ለመስራት በሚሞክሩበት ወቅት እየፈነዱ ሞትና የአካል ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ።

“በቅርብ ጊዜ በበነዊ ጣብያ ሁለት ወጣቶች ቦምብ ፈንድቶ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በቤቷ ውስጥ ስትጫወት ፈንጂ በመፈንዳቱ አንድ ህፃን ቆስሎ ወደ አይደር ሆስፒታል ተመርታለች” ሲሉ የቆላ ተምቤን ወረዳ አስተዳዳሪ ተክላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

‘ትግራይ ላይ ፈንጂ ያልተቀበረበት መሬት የለም’

ተቀብረው በቀሩ እና መሬት ላይ በተጣሉ በቀላል እና ከባድ መሳርያዎች የተነሳ ለአደጋ የተጋለጡ የትግራይ አካባቢዎች በርካታ ናቸው።

ለዚህም ምክንያቱ ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት የተለያዩ ኃይሎችን ያሳተፈ እና ሰፊ አካባቢዎችን ያዳረሰ ስለነበር መሆኑን አስተዳዳሪው ይናገራሉ።

“በጦርነቱ ወቅት የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች ግዙፍ ጥምረት ፈጥረው ከፍተኛ ጦርነት ተካሄዷል። ስለዚህ በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች የፈነዱና ያልፈነዱ ከጥይት ጀምሮ እስከ ከባድ አውሮፕላኖች ቦምቦች አሉ” ይላሉ በትግራይ የሰላም እና የጸጥታ ጽ/ቤት የምህንድስና ክፍል ኃላፊ ኮሎኔል ገብረሚካኤል ሐጎስ።

በዚህም ምክንያት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚገኘው ሕዝብ አደጋ ላይ ወድቆ እንደሚገኝ ለቢቢሲ የገለፁት ኮሎኔሉ፤ ፈንጂዎቹ እና ጥይቶቹ “በትምህርት ቤቶች፣ በእርሻ መሬት፣ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች፣ መጋዘኖች እና ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ተበታትነው ይገኛሉ” ብለዋል።

አክለውም “በተለይ ከቀየው ተፈናቅሎ የሚገኘው ሕዝብ ወደ ነበረበት ሲመለስ ለአደጋ የተጋለጠ ይሆናል። ስለዚህ የተቀናጀ ሰፊ ሥራ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በመኖሪያ አካባቢዎች የተተዉት ሳይፈነዱ ወይ ሳይመክኑ የቆዩ ቀላልና ከባድ የጦር መሳሪያዎች በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ አደጋዎች ሲያደርሱ እንደቆዩ ኮ/ል ገብረሚካኤል ያስረዳሉ።

“በተለይ በምሥራቅ ዞን በሰንቃጣ፣ የጭላ- ቆላ ተምቤን፣ ማዕከላዊ እና ምዕራባዊ ዞኖች አደጋዎች እያጋጠሙ ነው። የፈንጂዎቹ ዓይነቶች የመድፍ፣ ሞርታሮች እና አውሮፕላኖች ያካተቱ ናቸው። በሰው እና በእንስሳት ላይም ጉዳት እየደረሰ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ምን እየተደረገ ነው?

በተምቤን ሸለቆ ውስጥ ከፍተኛ እና ከባድ ውጊያ መደረጉን ያስታወሱት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ “ከመጠን በላይ ተበታትነው የሚገኙትን ከቀላል እስከ ከባድ ፈንጂዎች የማስወገድ አቅም የለንም፤ ግን አሳሳቢ ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡን ራሱን እንዲከላከል ግንዛቤ እንዲይዝ ማስተማር እንደ አማራጭ እየተሰራበት መሆኑን በመግለጽ ነዋሪዎች “እዚህ አካባቢ ተተኳሽ አለ” የሚል ጥቆማ እንዲደርሳቸውና “ወደዚህ አትጠጉ፤ እስኪነሳ ድረስ ተጠንቀቁ! . . ” የሚል ምክር ከመስጠት ባለፈ ለማንሳት ወይ ለማምከን የሚሆን አቅም እንደሌላቸው አስረድተዋል።

“በተወሰነ ደረጃ ግን ቀላል ፈንጂ ከሆነ በአካባቢያችን ያሉትን የትግራይ ኃይል አባላት በማሳወቅ እንዲያነሱልን እናደርጋለን። ነገር ግን በሁሉም ጣቢያዎች ስለሚገኝ ከአቅማችን በላይ ነው፤ ይህንን ለማድረግ የሚያስፈልገው ምንም ዓይነት መሳሪያም የለም” ብለዋል።

ኮ/ል ገብረሚካኤል ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን የማጽዳት ስራ ቀዳሚነት ተሰጥቶታል።

“ጊዜያዊ የትግራይ አስተዳደር በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መጋቢት 2015 ዓ.ም ላይ ትምህርት ከመጀመሩ አስቀድሞ ከፈንጂዎች ጸድተዋል። በዚህም ወቅት በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ብዙ ፈንጂዎች ተገኝተዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።

ትምህርት ቤቶቹን የማጽዳት ስራው ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተከናወነ ሲሆን ከ1,900 በላይ ትምህርት ቤቶችን ለማጽዳት ታቅዶ ሁሉም ላይ ፍተሻ በማካሄድ ጸድተዋል።

የክልሉ አቅም

ፈንጂዎችን በማጽዳትና በማምከን ረገድ ጊዜያዊው የክልሉ መንግሥት የሚያደርጋቸው ጥረቶች ቢኖሩም ከችግሩ ስፋትና ዓይነት አንፃር ሲታይ ግን የሚገባው ያህል እየተሰራበት ነው የሚባል እንዳልሆነ ኮሎኔሉ ይገልጻል።

“በሁሉም የትግራይ አካባቢዎች ከትንሿ ጥይት እስከ የአውሮፕላን ቦንብ ድረስ አለ። በመቀለም ቢሆን አውሮፕላኖቹ ከጣሉት ተተኳሽ መካከል አንዳንዱ የፈነዳ ሲሆን፣ አንዳንዱ ግን አልፈነዳም። የተለቀመና ያልተለቀመ አለ። አሁንም እየለቀምን ነው። በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው።”

አክለውም “ሕዝባችን በየቤቱና በእርሻ ቦታው በተተኳሽ ምክንያት ምን እየደረሰበት እንዳለ እያየን ነው። ስለዚህ ሊሰራበት ይገባል። አንዳንድ በጎ አድራጊዎችም መጥተው በግላቸው ለመሥራት እየሞከሩ ነው። ይህ ግን በፌዴራል መንግሥት የተማከለና በመተባበር ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው” ሲሉ አክለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ከሆነ ክልሉ የባለሙያ እጥረት የሌለበት ሲሆን “ዋናው ችግር የፋይናንስ እና የመሳሪያ እጥረት ነው። በክልሉ መንግሥት አቅም ብቻ የሚከናወን አይደለም። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ትኩረት ቢሰጠው” በማለት ተማጽነዋል።

እነዚህ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እስከ ሞት የሚደርስ ጉዳት እያደረሱ ያሉ ተተኳሾች የማጽዳት እና የማውደም እርምጃ እስኪወሰድ ድረስ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል፣ በተለይም አርሶ አደሩ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንዲሰራም አሳስበዋል። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *