ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዛሬ ማለዳ ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም የምስራቅ ወለጋ ዞን ከተማ ወደ ሆነችው ነቀምት አምርተው ባደረጉት ንግግር “ኦሮሞ ነጻ ወጥቷል፤ ትናንትና ታግለን በደማችን አሸንፈናል” ሲሉ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ይህንን የተናገሩት ዛሬ ማለዳ “ለውጡን በመደገፍ” በወለጋ ስታዲየም ላይ በነበረ ደማቅ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ነው።

ዐቢይ “ባለድል የሆነው ሕዝብ ድሉን ይጠብቃል እንጂ እንደገና ወደ ጦርነት አይገባም” ሲሉ አክለዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አብረው ከተጓዙ መካከል ይገኙበታል።

በወለጋ ሁሉም ዞኖች መንግሥት “ሸኔ” ሲል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የሚንቀሳቀስ ሲሆን ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ውጊያ እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባለፈው ዓመት ወደ ነቀምት አምርተው ሰላም እና ልማትን በተመለከተ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በስታዲየም ለተሰበሰቡት ነዋሪዎች የወለጋ ሕዝብ በሰላም እጦት ምክንያት ከልማት ወደ ኋላ መቅረቱን ጠቅሰዋል።

“እንደ አገር በምሥራቅ አፍሪካ በልማት ምሳሌ የሚሆን ኢኮኖሚ እየገነባን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በዚህ አገር ውስጥ ሰላም የለም፣ አንድነት የለም። ነገር ግን በአፍሪካ ምሳሌ የሆነ ኢኮኖሚ እየገነባን ነው። የኢትዮጵያ ብልጽግና ይረጋገጣል። የምትፈራ ኢትዮጵያ እንገነባለን” ብለዋል።

አክለውም “በነቀምት አዋጅ ማወጅ እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መረዳት ያለበት የኦሮሞ አንድነት የማይጠበቅ ከሆነ የኢትዮጵያ አንድነት ሊጠበቅ አይችልም። ኦሮሞ ሠላም ካልሆነ ኢትዮጵያ ሠላም አይኖራትም። ኦሮሞ ታላቅ ነው። ራሱን ለውጦ አገር ይለውጣል” በማለት ተናግረዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ባለው ግጭት የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ሲሞቱ በመቶ ሺዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።

በክልሉ ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር እየተዋጋ የሚገኘው እና በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለሰላም ድርድር በታንዛንያ ሁለት ጊዜ ቢገናኝም ስምምነት ላይ መደረስ ሳይቻል ቀርቷል።

የኦሮሞ ህዝብን ጥቅም ለማስከበር እንደሚታገል የሚናገረው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በወለጋ የተለያዩ ዞኖች በዋነኝነት ይንቀሳቀሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በዛሬው ንግግራቸው “እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠውን ማብቂያ የሌለው ሰላም ለኢትዮጵያ አውጃለሁ” ብለዋል።

በስታድየሙ የተገኙ ነዋሪዎች ከያዝዋቸው መፈክሮች መካከል “ወለጋ የሰላም ምድር” የሚል ይገኝበታል።

“የወለጋ ሕዝብ በልማት በኩል ተጎድቷል። ይህም ደግሞ በሰላም እጦት ምክንያት ነው። ወለጋን መቀየር እንፈልጋለን፤ ራዕይም አለን። ይህ ሀሳባችን በመንገድ ላይ እንዳይቀር ሕዝቡ እድል ይስጠን። ሕዝባችን እኛን ይደግፈን” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉድሩን ጨምሮ ባሉ የወለጋ ዞኖች በባለፉት ዓመታት በተፈጸሙ ጥቃቶች የተነሳ በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፣ ንብረት ወድሟል እንዲሁም ተፈናቅለዋል።

እነዚህ ጥቃቶች ብብሄር ማንነት ላይ ያነጣጠሩ እንደሆነ ነዋሪዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያሳያሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በዛሬው ንግግራቸው “የወለጋን ስም ለማጥፋት የሚደረገው ሙከራ አድሰን በጥሩ ስም ለማስጠራት እንሰራለን። ልጆቻችንን እንምከር ጸጸት ውስጥ ከመግባታችን በፊት እንረዳዳ[በሀሳብ]” ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንድማማቾች መገዳደል እንደሌለባቸው፣ በራስ ቋንቋ የማስተዳደር ጥያቄዎች መልስ ማግኘታቸውን የሳቸው መንግሥት የሚመራው ትሩፋት መሆኑን ጠቅሰዋል።

“ውድ ዋጋ ከፍለንበታል። እምቢ ብሎ የራሱን አገር ባለለቤትነት አረጋግጧል” ብለዋል።

አክለውም “ዛሬ ያለው ጥያቄ ለምን አንለማም፤ ሌብነት መስፋፋት የለበትም የሚለው ነው።ለዚህ ደግሞ መሞት አያስፈልግም” ያሉት ዐብይ፣ “እኛ አብረን ቁጭ ብለን ለመነጋገር ያስቸግረናል። ነገር ግን ከኦሮሞ ጠላቶች ጋር ቁጭ ብለን ለመነጋገር እቅድ ማውጣት ግን አያስቸግረንም። እንደዚህ ዓይነት ኦሮሞነት ከየት መጣ?” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሞ ጠላቶች ብለው የጠሯቸውን አካላት አልጠቀሱም።    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *