በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን፤ ሶስት ሬክተር ስኬል ሆኖ የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦፊዚክስ፣ ህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የመሬት መንቀጥቀጡ በዞኑ በሚገኙ አስሩም ወረዳዎች እና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች እንደተከሰተ የዳውሮ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ገልጿል።

በዳውሮ ዞን የመሬት መንቀጥቀጡ የተመዘገበው ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 29፤ 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ከ24 ደቂቃ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊው እንደሚያስረዱት፤ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ባለው ልምድ የመሬት መንቀጥቀጥን የተከሰተበትን ቦታ በትክክል ለማግኘት ከሶስት በላይ ጣቢያዎች የተመዘገቡ መረጃዎችን ይጠቀማል።

በዛሬው ዕለት ግን በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት መረጃ ማግኘት የተቻለው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ከሚገኝ ጣቢያ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ፕሮፌሰር አታላይ፤ የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው “በዳውሮ አካባቢ ነው” ብሎ መውሰድ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በሚገኝ ጣቢያው የመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ “በሬክተር ስኬል ወደ ሶስት የሚገመት” መሆኑን ፕሮፌሰል አታላይ ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የዳውሮ ዞን የታርጫ ከተማ ነዋሪዎች ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ ላይ ለሰከንዶች የቆየ የመሬት መንቀጥቀጥ እንደተሰማቸው ተናግረዋል። አቤኔዘር ተስፋዬ የተባለ የታርጫ ከተማ ብርሃን መንደር ነዋሪ፤ “መሬት ላይ ተኝቼ ነበር፣ [መሬቱ] እንደተንቀሳቀሰ ተሰምቶኛል። ከዚያ ባለፈ ድምፅም ነበር” ሲል የነበረውን ሁኔታ አስረድቷል።

በመንደሩ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ከቤት ሲወጡ እና ሲደናገጡ ማስተዋሉም አክሏል። ምህረት ምትኩ የተባለች ሌላ የከተማው ነዋሪም በተመሳሳይ የተደናገጡ ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው እንደነበር ተናግራለች።

ምህረት፤ “የተኩስ ድምፅ የመሰለውም ሰው ነበር። የተወሰነ ሰው ሊረጋጋ የቻለው በማህበራዊ ሚዲያ ሲለቀቅ ነው። ሰው መጀመሪያ ላይ የየራሱን ግምት ሲወስድ ነበር። አብዛኛው ሰው ደንግጦ ከቤት፣ ከሆስፒታል፣ ከትምህርት ቤቶች ወደ ውጪ ወጥቶ ነበር” ስትል ነዋሪዎች መጀመሪያ ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ መሆኑን እንዳልተረዱ አስረድታለች።

ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ ከታርጫ ከተማ አስተዳደር በተጨማሪ በዞኑ በሚገኙት አስር ወረዳዎች እና ዲሳ የከተማ መስተዳደር መከሰቱን እንዳረጋገጡ የዳውሮ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ሲሳይ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ የቆየው “ለሽርፍራፊ ሰከንዶች” መሆኑን የሚናገሩት አቶ ከበደ፤ በሁሉም የዞኑ መዋቅሮች ውስጥ በዚሁ ምክንያት “በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን” አስረድተዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የታርጫ ከተማ ነዋሪዎችም የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል።

ነዋሪዎች ላይ የመደናገጥ እና የመረበሽ ሁኔታ መታየቱን የሚናገሩት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊው፤ የመሬት መንቀጥቀጥ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነዋሪዎች መረጋጋታቸውን አስረድተዋል።

የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተበት የዳውሮ ዞን የስምጥ ሸለቆ አካል መሆኑን የሚገልጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊው ፕሮፌሰር አታላይ፤ በዚህም ምክንያት አካባቢው ላይ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር አታላይ፤ “የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን አቋርጦ ወደ ኬንያ እና ሰሜን ዩጋንዳ የሚሄድ ነው። ስለዚህ [የመሬት መንቀጥቀጥ] የተፈጠረበት ቦታ የስምጥ ሸለቆ አካል ስለሆነ [ክስተቱ] የሚጠበቅ ነው” ብለዋል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *