የአፍሪካ ኅብረት በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንቱ ሊወጣ የነበረው ስድስት ሚሊዮን ዶላር መክሸፉን አስታወቀ።

የአፍሪካ ኅብረት ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ስድስት ሚሊዮን ዶላር በሕገ ወጥ መንገድ ለማውጣት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች እና የአፍሪካ ኅብረት ገንዘብ ክፍል ሠራተኞች “ንቁና ፈጣን እርምጃ በመውሰድ” በሕገ ወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረውን ገንዘብ ማዳን እንደቻሉ በመግለጫው አስታውቋል።

የአፍሪካ ኅብረት “ሊደርስበት ይችል የነበረውን ኪሳራ መቀልበስ እንደተቻለም” አክሏል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን ለመመሥረት በነበራቸው እንቅስቃሴ የሚታወቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፣ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማውጣት በመሞከር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ፣ ሚያዝያ 7 ቀን 2016 ዓ. ም. “የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኛ ባልሆነ አካል የክፍያ ትዕዛዞች ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ” ገብተዋል። “ከግንባታና የውሃ ቁፋሮ ሥራ” ጋር ለተያያዘ ክፍያ በሚል ገንዘቡ ሊወጣ እንደነበር የኅብረቱ መግለጫ ያስረዳል።

ሆኖም ግን በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የፋይናንስ ዳይሬክተር በተደረገ “ጥልቅ ምርመራ” ክፍያውን ለማውጣት የገባው ሰነድ ሐሰተኛ መሆኑ እንደተደረሰበትና ይህንንም ተከትሎ ለፌደራል ፖሊስ በተደረገው ጥቆማ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተገልጿል።

ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙትን ቀሲስ በላይ፣ የሹፌራቸው እና የአጃቢያቸውን ጉዳይ የያዘው መርማሪ ፖሊስ በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ውሎ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ ያከናወናቸውን ተግባራት ረቡዕ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ. ም. ለፍርድ ቤት ሲያስረዳ፣ ቀሲስ በላይ ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ የተገኙት “ሰዎች አታልለዋቸው” እንደሆነ ለፍርድ ቤት መግለጻቸውን ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

በዕለቱ በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ፣ መርማሪ ፖሊስ የቀሲስ በላይን ቤት መበርበሩን እና በብርበራውም አንድ ሽጉጥ ማግኘቱን መናገሩን ጠበቃው አንስተዋል።

ይሁንና ፖሊስ ያገኘው ሽጉጥ ፈቃድ ያለው ስለመሆኑን ለማጣራት፣ ግብረ አበር የሆኑት ሌሎች ስድስት ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እንዲሁም ለባንክ እና ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመጠበቅ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን መጠየቁን አቶ ቱሊ አስረድተዋል።

ፖሊስ “አገራዊ ጉዳይ ነው። በጣም ውስብስብ ከባድ ወንጀል ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ መናገሩንም ጠበቃው ገልጸው ነበር።

የአፍሪካ ኅብረት ባወጣው መግለጫ ጉዳዩን “ከፍተኛ ሥፍራ ሰጥቶ” እየተከታተለው እንደሆነ ገልጾ “እንዲህ ያለ ሙከራ መደረጉ አሳሳቢ ቢሆንም ክስተቱ በኅብረቱ ያለውን “የደኅንነት ጥንቃቄ መልሶ ለማጤን” ምክንያት እንደሆነ ጠቅሷል።

የአፍሪካ ኅብረትን የፋይናንስ ሥርዓት “አደጋ ውስጥ የሚከቱ ሙከራዎችን ለመግታት” ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑንም መግለጫው ያትታል። አያይዞም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰጡት “አፋጣኝ ምላሽ” ምስጋናውን አቅርቧል።

ከቀናት በፊት በዋለው ችሎት ላይ ቀሲስ በላይ ወንጀሉ ተፈጽሞበታል በተባለው የአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገኙት “ሰዎች ወስደዋቸው” እና “ተታልለው” መሆኑን እና “በዚያ ቦታ ላይ ከመገኘት ውጪ ምንም የፈጸሙት ድርጊት አለመኖሩን” ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ከስድስት ጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *