የአውሮፓ የፍትሕና ሕግ ማዕከል “ድምጽ አልባው የአማራ ሕዝብ ስቃይ በኢትዮጵያ” በሚል አርዕስት ባወጣው ሪፖርት በክልሉና ከክልሉ ውጭ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ዘርዝሯል።

በአውሮፓ እና በአለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ የሚሰራው ማዕከሉ የአገሪቱን የረጅም ዘመን ታሪክና የተወሳሰበ የፖለቲካ ስርዓት ቃኝቶ ሪፖርቱን የሚጀምር ሲሆን፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ጉልህ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጨምሯል ብሏል።

በግጭቶች የሚባባሰውና በዋናነት በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓለም አቀፍ ትኩረትን ማግኘታቸውን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፤ በተለይ ግን በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸመው በደል የጥልቀቱን ያህል በቂ ሽፋን አያገኝም ብሏል።

መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው እና ከአውሮፓውያኑ 2007 ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ልዩ የአማካሪነት ስፍራ እንደተሰጠው የጠቆመው ማዕከሉ ይህን ክፍተት ለመሙላት በአማራ ማሕበረሰብ ላይ እየደረሰ ነው ያለውን በደል በደንብ በመፈተሽ ሪፖርቱን ስለማውጣቱ ጠቅሷል።

የሪፖርቱ ግኝት በአማራ ሕዝብ ላይ አሳሳቢ፣ ሰፊና የተያያዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እተፈጸሙ እንደሆነ ጠቁሟል። ለዚህም አሁንም ድረስ እተፈጸሙ ናቸው ያላቸውን ጥሰቶች የሚያነሳ ሲሆን፤ እልቂቶች፣ ያለ ፍርድ ግድያዎች፣ የድሮን ጥቃቶች፣ በኃይል ማፈናቀል እና የጅምላ እስሮችን ዘርዝሯል።

እነዚህ እርምጃዎች በአመዛኙ የብሄር ማንነትንና የኃይማኖት አድልዎን መሰረት አድርጎ ለአያሌዎች እልቂት እና በአገሪቱ ግጭትን ለማባባስ እንደመሩ ገልጿል።

ለጥሰቶች የመንግሥትን ምላሽ አዝጋሚ ሲል የሚተቸው ሪፖርቱ፤ ሁኔታዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጥቃቶች እርምጃ ለመውሰድ ቸልተኝነት አሳይቷል አሊያም በቀጥታ ተሳትፏል ብሏል።

እ.አ.አ በ1998 በሁለት ግለሰቦች የተመሰረተው ማዕከሉ በሪፖርቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአማራ ሕዝብ ችግር ችላ ተብሏል ያለም ሲሆን፤ እየተፈጸመ ነው ያለው ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ወደ ስልታዊ የዘር ጭፍጨፋ (ጄኖሳይድ) አዝማሚያ ስለመሆኑ አትቷል።

የብሄር ግጭት እና የዘር ማጥፋት አዝማሚያ በኢትዮጵያ

መንግሥታዊ ያልሆነው የአውሮፓ የፍትሕና ሕግ ማዕከል ባለፉት አምስት ዓመታት የአማራ ሕዝብ ለተደጋጋሚ እልቂት ተዳርጓል በማለት ከቡራዩ እስከ ሻሸመኔ፤ ከመተከል እስከ ወለጋ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ይዘረዝራል።

በቡራዩ ከመስከረም 04 እስከ 06፤ 2010 ዓ.ም. “መሬታችንን ልቀቁ” የሚሉ መፈክሮችን ያሰሙ ወጣቶች በአካባቢው ህዳጣን የሆኑ በአብዛኛው በብሄር አማራ የሆኑ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። በዚህ ጥቃት ቁጥሩ ከፍ ሊል ይችላል ቢባልም 23 ሠዎች መገደላቸውን ዋቢ ጠቅሶ ሪፖርቱ አትቷል።

ከ2010 እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሁለት ዓመታት በተለይም በአገሪቱ ደቡብና ምስራቃዊ ከፍሎች 30 የሚሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋልም ብሏል።

ሪፖርቱ ጥቅምት 2012 ዓ.ም. ታዋቂው የኦሮሞ ተሟጋች (ጃዋር መሀመድ) በማሕበራዊ የትስስር ገጻቸው በጸጥታ ኃይሎች ‘ጥቃት ሊሰነዘርብኝ ነው’ ማለታቸውን ተከትሎ በደረሰ አመጽ የ67 ሠዎች ሕይወት መቀጠፉንም ጠቅሷል። በዚህ ጥቃት ከተገደሉት ሠዎች መሀል 52ቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ መሆናቸውን መገናኛ ብዙኃንን ዋቢ በማድረግ ጠቅሷል።

ከህዳር 13 እስከ 17፤ 2016 ዓ.ም. በአርሲ ዞን ሦስት አካባቢዎች 36 ሠዎች የተገደሉበትን ጥቃትም የሚዘረዝር ሲሆን፤ በአገሪቱ በአማኞች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተጠናክረዋል ብሏል።

ባለፉት ወራት የተፈጸሙትን የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል እና የዝቋላ ገዳምን ግድያ እንዲሁም በቄለም ወለጋ የተገደሉትን የመካነ እየሱስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ጉዳይም አንስቷል።

ሰኔ 22፤ 2012 ዓ.ም. የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሻሸመኔ፣ አርሲ፣ ደራና ዝዋይ ባሉ አካባቢዎች ለሳምንታት በዘለቀ ጥቃት ብሄርና ኃይማኖት ኢላማ ተደርገዋል። በዚህ ሁከት 239 ሠዎች ተገድለዋል ያለው ሪፖርቱ ጥቃቶቹ “በቂ ዝግጅት” የተደረገባቸው መሆናቸውን በአስረጂነት የመብት ተሟጋቾችን ሪፖርት ጠቅሷል።

የአውሮፓ የፍትሕና ሕግ ማዕከል ሪፖርት ባለፉት ዓመታት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች የሚፈጸሙባቸውን በወለጋና መተከል የተከሰቱ ሁነቶችንም ዘርዝሯል።

በጥቃቶቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን መገደላቸውን እና በመቶ ሺዎች ደግሞ መፈናቀላቸውንም እንዲሁ።

“ሕገ-ወጥ” በሚል መንግሥታዊ ማፈናቀል በተለይም በአማራ ሕዝቦች ላይ መፈጸሙ በሪፖርቱ የተካተተ ሲሆን፤ በሸገር ከተማ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ፈርሰዋል ብሏል።

በአማራ ክልል እየተወሰደ ያለው ወታደራዊ እርምጃ

ሐምሌ 2015 ዓ.ም. የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በአማራ ክልል አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የ23 ሠዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የፍኖተ ሰላም የድሮን ጥቃት፣ 48 ሠዎች የሞቱበት የቋሪትና የደንበጫ የድሮን ጥቃት እንዲሁም በበረኸት ወረዳ በተመሳሳይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ህጻንን ጨምሮ የ35 ሠዎች ሕይወት ማለፉን ዘርዝሯል።

በክልሉ የድሮን ጥቃቶች በዋነኛነት አሳሳቢ ቢሆኑም ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ትኩረት ይሻሉ በማለት፤ ያለ ፍርድ ግድያዎች ‘ጉልህና አስጨናቂ’ መልክ ይዘዋል ብሏል።

ቤት ለቤት በሚደረጉ አሰሳዎች በመንግሥት ኃይሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን የጠቀሰው የማዕከሉ ሪፖርት፤ በዋናነት በማጀቴ ከተማ ከ70 ሠዎች በላይ ተገድለውበታል የተባለውን ግድያ አንስቷል።

የጅምላና የዘፈቀደ እስር በአማራ ማሕበረሰብ ላይ እንደ ማዕበል ተካሂዷል በማለትም መንግሥት ያመናቸውን ቁጥሮች አስቀድሞ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀመሮ 14 ሺህ የሚሆኑ ሠዎች ሳይታሰሩ እንዳልቀሩ ጥርጣሬውን አስቀምጧል።

አብዛኞቹ ታሳሪዎችም እንደ ትምህርት ቤት ባሉ ጊዜያዊ ማቆያዎች እንደሚገኙ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የደጃዝማች ወንድይራድን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአብነት አንስቷል።

ምክረ-ሃሳቦች

19 ገጾች ያሉት የአውሮፓ የፍትሕና ሕግ ማዕከል “ድምጽ አልባው የአማራ ሕዝብ ስቃይ በኢትዮጵያ” የተሰኘው ሪፖርት በመጨረሻ ምዕራፉ ምክረ-ሃሳቦቸን አስቀምጧል።

ሪፖርቱ የዘረዘራቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች “ከባድ” ከመሆናቸው አንጻር ሁለት አበይት ምክረ-ሃሳቦችን ጠቁሟል።

‘ገለልተኛ የመንግሥታቱ ድርጅት መርማሪ’ ማቋቋም “አስፈላጊ” ነው ሲል በቅድሚያ አስቀምጧል።

ለዚህም የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኝነትና በአግባቡ እንዲመረመሩ በተመድ የሚቋቋመው መርማሪ ማስረጃ እንዲሰበስብ፣ የክስተቶችን ሰነድ እንዲያደራጅ እና ለተፈጸሙ ግፎች ዝርዝር ግምገማ በማቅረብ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ስለ ቀውሱ ግንዛቤ እንዲኖረውና ምላሽ ሰጪ እንዲሆን ኃላፊነት ሊሰጠው ይገባል ብሏል።

ሁለተኛው የማዕከሉ ምክረ-ሃሳብ ደግሞ ተጠያቂነትንና ፍትሕን ማስፈን ነው። የመንግሥታቱ ድርጅትን ምርመራ ተከትሎ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት ሊኖር ይገባል ብሏል።

ለተጎጂዎችና ለቤተሰቦቻቸው ፍትሕን የሚሰጥ የሕግ ስርዓትና የፍርድ ሂደት ማስጀመር እንዲሁም የአጥፊዎች ስልጣን ወይም ማንነት ምንም ይሁን ምን በድርጊታቸው ለፍትሕ እንዲቀርቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሏል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *