የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ” ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች መልሰው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ የሚያስችላቸውን ድንጋጌ የያዘ የአዋጅ ማሻሻያን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መራ።

በሥራ ላይ ባለው “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ” ላይ የተደረገው ይህ ማሻሻያ፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተሰረዘበትን የፓርቲነት ሕጋዊ እውቅና መልሶ እንዳያገኝ ያደረገውን የሕግ ጥያቄ የሚመልስ ነው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአዋጅ ማሻሻያውን ተቀብሎ ወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመራው ዛሬ አርብ ግንቦት 23/2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ጽህፈት ቤቱ ያወጣው መረጃ እንደሚያስረዳው ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት በአራት ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

ከእነዚህ ረቂቆች መካከል በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አድርጎ ስለማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበው አዋጅ ይገኝበታል።

በተጨማሪም የንብረት ማስመለስ አዋጅ እና የነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሥርዓትን ለመደንገግ የቀረበው አዋጅም ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ውሳኔ የተሰጠባቸው ሕጎች ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፤ በዛሬው ስብሰባ ውሳኔ እንደተላለፈበት በቀዳሚነት የጠቀሰው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ አዋጅ ነው። ማሻሻያ የቀረበበት በ2012 ዓ.ም. የወጣው የምርጫ ሕግ፤ እውቅና የተነፈጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መልሶ ከመመዝገብ ጋር በተያያዘ ክፍተት ያለበት እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ጠቅሷል።

“ከሕጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ እነዚህን አካላት ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ሥርዓት በነባሩ አዋጅ ላይ አልተካተተም” ሲል በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ላይ የታየውን ክፍተት ይገልጻል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ የመራው ማሻሻያ ላይ የፖለቲካ ቡድኖች “በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ” መልሰው ለመመዝገብ የሚችሉበትን ሥርዓት የሚዘረጋ እንደሆነም ተጠቅሷል።

ዛሬው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔ ላይ የተጠቀሰው የፖለቲካ ቡድኖች መልሶ የመመዝገብ ጉዳይ ከህወሓት ዳግም ሕጋዊ እውቅና የማግኘት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ውዝግብ ፈጥሮ ነበረ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ “የአመጻ ተግባር ላይ ተሰማርቷል” በሚል የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት የሰረዘው ጥር 2013 ዓ.ም. ነበር። ምርጫ ቦርድ በወቅቱ “የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉም” ውሳኔ አስተላልፎ ነበር።

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ እና ህወሓት የተጣለበት የሽብርተኝነት ስያሜ ከተነሳ በኋላም፤ ምርጫ ቦርድ የፓርቲው ሕጋዊ እውቅና እንዲመለስ የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጎታል።

ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ ይህንኑ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ለህወሓት መሰረዝ ምክንያት የሆነው “ኃይልን መሠረት ያደረገው የአመጻ ተግባር” እንደሌለ ጠቅሷል። ይሁንና በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ላይ የፓርቲውን ሕጋዊ እውቅና ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች ባለመኖራቸው ጥያቄው “በሕግ የተደገፈ ሆኖ እንዳላገኘው” ቦርዱ አስታውቆ ነበር።

ህወሓት በድጋሚ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ በፖለቲካ ፓርቲነት መንቀሳቀስ የሚችለው “በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሕጉን መሠረት አድርጎ ሲፈቅድ” እንደሆነም በቦርዱ ውሳኔ ላይ ተጠቅሷል።

ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ግን በህወሓት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ህወሓት ከዚህ ውሳኔ መገለጽ ከቀናት በኋላ ባወጣው መግለጫ ውሳኔው “በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰላም ተስፋ ከመደገፍ ይልቅ የሰላም ስምምነቱ ዋናው ባለቤት የሆነውን የህወሓት ህልውና እንዳይኖረው ለማድረግ” ያለመ ነው በሚል ምርጫ ቦርድን ከስሶ ነበር።

ውሳኔውን “በሕግም በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም” ሲል ያጣጠለው ህወሓት፤ የቦርዱ ውሳኔ “የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የሰላም መንገድ ለመደገፍ ሕግን በአወንታዊ የትርጉም ሥርዓት ከመረዳት ይልቅ፤ ቴክኒካዊ በሆነ አረዳድ” ላይ ያተኮረ እንደሆነ ጠቅሶ ነበር።

ህወሓት፤ “የትግራይ አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል እና አጠቃላይ የሰላም ሂደቱን የሚያደናቅፍ ተግባር” ሲል የጠራውን ይህንን ውሳኔ ቦርዱ “መርምሮ እንዲያስተካክል” ጠይቋል።

ይህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ይፋ የሆነው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ እና ህወሓት ተከታታይ ፖለቲካዊ ንግግሮችን በአዲስ አበባ እና መቀሌ ካደረጉ በኋላ ነው።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *