ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማውጣት በመሞከር የተጠረጠሩት ቀሲስ በላይ መኮንን፤ ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ የተገኙት “ሰዎች አታልለዋቸው” እንደሆነ ለፍርድ ቤት መግለጻቸውን ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን ለመመሥረት በነበራቸው እንቅስቃሴ የሚታወቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፤ ይህንን የተናገሩት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም. በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ ነው።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ረፋድ አራት ሰዓት የተሰየመው፤ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት በነበረው ችሎት ሰባት ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቅዶባቸው የነበረውን ቀሲስ በላይ ጉዳይ ለሁለተኛ ጊዜ ለመመልከት ነበር።

ቀሲስ በላይ የተጠረጠሩት፤ በአዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ “በሐሰተኛ ሰነድ ተገልግለው ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት ሙከራ አድርገዋል” በሚል እንደሆነ ጠበቃው አቶ ቱሊ ገልጸዋል።

በዚህ ዓይነት መንገድ ስድስት ሚሊዮን 50 ሺህ ዶላር ለማውጣት በመሞከር የተጠረጠሩት ቀሲስ በላይ፤ በአፍሪካ ኅብረት የጥበቃ ሠራተኞች ተይዘው ለፌደራል ፖሊስ ምርመራ ቢሮ ተላልፈው መሰጠታቸውን ጠበቃው አስታውሰዋል።

ባለፈው ሳምንት ሰኞ ዕለት በሐሰተኛ ሰነድ ገንዘቡ ሊወጣ የነበረው ከአፍሪካ ኅብረት የባንክ አካውንት ውስጥ እንደሆነ የአፍሪካ ኅብረት ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ክፍል ከጻፈው ደብዳቤ ላይ መመልከቱት “ዘ ሪፖርተር” ጋዜጣ ዘግቦ ነበር። ዘገባው እንደሚያመለክተው ገንዘቡ ሊወጣ የነበረው አራት የግንባታ ክፍያ ምክንያቶች ተጠቅሰው ነው።

ከዚህ ድርጊት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙት ቀሲስ በላይ እንዲሁም ሹፌራቸው እና አጃቢያቸውን ጉዳይ የያዘው መርማሪ ፖሊስ በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ውሎ በተፈቀደለት የምርመራ ጊዜ ያከናወናቸውን ተግባራት ዛሬ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን አቶ ቱሊ ጠቅሰዋል። መርማሪ ፖሊስ፤ የቀሲስ በላይን ቤት መበርበሩን እና በብርበራውም አንድ ሽጉጥ ማግኘቱን መናገሩን ጠበቃው አንስተዋል።

ይሁንና ፖሊስ ያገኘው ሽጉጥ ፈቃድ ያለው ስለመሆኑን ለማጣራት፣ ግብረ አበር የሆኑት ሌሎች ስድስት ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እንዲሁም ለባንክ እና “ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች” ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመጠበቅ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን መጠየቁን አቶ ቱሊ አስረድተዋል። ፖሊስ “አገራዊ ጉዳይ ነው፣ በጣም ውስብስብ ከባድ ወንጀል ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ መናገሩንም አክለዋል።

ቀሲስ በላይን ወክለው የቀረቡት ስድስት ጠበቆች በበኩላቸው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፈቀድ እንደሌለበት “አጥብቀው” መከራከራቸውን ገልጸዋል።

አቶ ቱሊ፤ “አንደኛ እሳቸው በቦታው ከመገኘት ውጪ ደብዳቤውን በማዘጋጀት፣ በመቀበል በዚህ ወንጀል ውስጥ ተሳትፎ የላቸውም። ደብዳቤው ላይ የእሳቸው ስም፣ የባንክ ቁጥር የለም። የቤተ ክርስቲያን የሂሳብ ቁጥር የለም። ስለዚህ ከመጀመሪያውም ወንጀሉ በሌሎች ሰዎች የተሞከረ ቢሆንም እሳቸውን አይመለከትም። ቢመለከት እንኳ የዋስትና መብት የሚያስከለክል አይደለም” ሲሉ በጠበቆች በኩል የቀረበውን መከራከሪያ አብራርተዋል።

በችሎቱ ላይ ለመናገር ዕድል ያገኙት ቀሲስ በላይ በበኩላቸው “ለፖሊስ ታዛዥ እና ለሕግ ተገዢ” መሆናቸውን እንዲሁም “በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ በተፈለጉ ጊዜ መቅረብ እንደሚችሉ” በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ በዋስትና እንዲለቃቸው መጠየቃቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል።

ቀሲስ በላይ አክለውም፤ ወንጀሉ ተፈጽሞበታል በተባለው የአፍሪካ ኅብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገኙት “ሰዎች ወስደዋቸው” እና “ተታልለው” መሆኑን መናገራቸውን የጠቀሱት አቶ ቱሊ፤ “በዚያ ቦታ ላይ ከመገኘት ውጪ ምንም የፈጸሙት ድርጊት አለመኖሩን” ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ገልፀዋል።

ቀሲስ በላይ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ፤ “ሰዎቹ ናቸው አታልለውኝ እዚያ ድረስ የወሰዱኝ። እኔ ወደዚያ የሄድኩት ለመተባበር፣ ይህ ሰነድ ‘ትክክለኛ ሰነድ ነው አይደለም’ የሚለውን የባንክ ማናጀሮችን ለመጠየቅ ነው። እንጂ በምንም ሁኔታ በሰነዱ ለመገልገል አስቤ አይደለም። ጉዳዩ ዞሮ እኔ ታሳሪ ሆንኩኝ እንጂ፤ ሰነዱ ‘ትክክል አይደለም’ የሚል የባንክ ማናጀሩ ሲገልጹልኝ ወዲያው ፖሊስ ያስጠራሁት እኔ ነኝ” ማለታቸውን አቶ ቱሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው፤ ሰነዱን አዘጋጅተዋል የተባሉት ሰዎች “ማምለጣቸውን” እንዲሁም ስለ ሰነዶቹ “የሚያውቁት እና መመርመር ያላባቸው” እነሱ እንደሆኑም ለፍርድ ቤቱ አንስተዋል ተብሏል።

ቀሲስ በላይ፤ የእሳቸው ትብብር ያስፈለገበትን ምክንያት አለመጠቅሳቸውን የተናገሩት ጠበቃው፤ የዛሬው ችሎት የጊዜ ቀጠሮ ለማየት የተሰየመ በመሆኑ ይህ ዓይነቱ ዝርዝር የሚገለጸው ወደፊት በሚኖሩ ሂደቶች መሆኑን አስረድተዋል።

ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ፖሊስ ከጠየው 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውስጥ ስምንት ቀን መፍቀዱን ጠበቃው አቶ ቱሊ ገልጸዋል።      ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *