የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ፓርቲያቸው ህወሓት ከገዢው ብልፅግና ጋር በሚያደርገው ንግግር ወቅት የውህደት ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ እንደማያውቅ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ህወሓት ዋነኛው መሥራች እና አስኳል የነበረበት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኢሕአዴግ) በመተካት የገዢነት መንበሩን ከተረከበው ብልፅግና ጋር ከተለያየ በኋላ ነበር በሁለቱ ወገኖች መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት የተከሰተው።

በዚህም ሳቢያ ሁለቱ ፓርቲዎች ሊዋሃዱ ንግግር እያካሄዱ የመሆናቸው ጉዳይ በስፋት መነጋገሪያ ቢሆንም ፓርቲውም ሆነ አቶ ጌታቸው ዜናውን አስተባብለዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ማክሰኞ ምሽት ከ’ቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ’ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለውህደቱ፣ ስለሰሞኑ ግጭት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ስላለቸው ግንኙነት እና የይገባኛል ጥያቄ ስለሚነሱባቸው አካባቢዎች ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ባለፉት ሳምንታት በአማራ እና ትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ያጋጠመው በሁለቱ ክልሎች ባሉ “የሚሊሻ አባላት” የነበረ እንጂ መደበኛ ኃይሎች የተሳተፉበት ግጭት አልተካሄደም ብለዋል።

ጌታቸው ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ እንዳሆን የሚፈልጉ ያሏቸው እና በስም ሊጠቅሷቸው ያልፈቀዱ አካላት ግጭት ለመፍጠር እየጣሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።

ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን ሁኔታ ሲያስረዱም፤ “በአማራ ክልል የነበሩ ሚሊሻዎች የተለያዩ አስጊ እንቅስቃሴያዎችን ሲያደርጉ ነበር። በእኛ በኩል ያሉ የሚሊሻ አባላት ምላሽ ሰጥተዋል” ብለዋል።

ይህን ተከትሎ የአማራ ክልል ያወጣው መግለጫ “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ” ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የደረሱት የሰላም ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆን እያደረገ ያለው ሕጋዊ የልሆነ የአማራ አስተዳደር ነው ብለዋል።

“አለመታደል ሆኖ ከአማራ ክልል መግለጫ ተሰጥቷል። በባሕር ዳር ያለ ሕዝብ ግን ልዩነትን በመነጋገር ብቻ መፍታት ብቸኛው አማራጭ መሆኑን መረዳት አለበት” ብለዋል።

ስለአወዛጋቢ አካባቢዎች

የአማራ ክልል ሚያዝያ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫው ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ አራተኛ ዙር ወረራ ፈጽሟል በማለቱ መክሰሱ ይታወሳል።

ክልሉ ይህንን ያለው አወዛጋቢ በሆኑት የራያ አካባቢዎች ለቀናት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ በከተሞች አካባቢ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ በዙሪያቸው ደግሞ የህወሓት ታጣቂዎች መግባታቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በይገባኛል ከሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች መካከል የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ የተባሉትን የህወሓት ኃይሎች በወረራ መቆጣጠራቸውን በመጥቀስ የፌደራል መንግሥቱ እና ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ድርጊቱን እንዲያስቆሙ የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቅርቦ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ከ50 ሺህ የማያንሱ የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ሲናገሩ “ሕጋዊ ያልሆኑ” የአማራ አስተዳደሮችን ለማፍረስ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ሚያዚያ 8/2016 ዓ.ም. የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጄኔራል ታደሠ ወረደ በሰጡት መግለጫ “በደቡባዊ ትግራይ እና ጸለምት ወረዳዎች” በአማራ ክልል የተቋቋሙ አስተዳደሮችን ለማፍረስ በፌዴራል መንግሥቱ እና በትግራይ መካከል ስምምነት መደረሱን ተናግረው ነበር።

አቶ ጌታቸው ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 15/2016 ዓ.ም. ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከስምምነት መደረሱን አስታውሰው፤ “ሕጋዊ ያልሆኑ አስተዳደሮችን ለማፍረስ ከፌደራል መንግሥቱ እና ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር ጭምር እየሠራን ነው” ብለዋል።

“የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነት አስቁሟል። ነገር ግን ስምምነቱ የተኩስ ድምጽ ማስቆም ብቻ አይደለም” ያሉት አቶ ጌታቸው “ምዕራብ ትግራይ፣ ሰሜን ምዕራብ ትግራይ እና ደቡብ ትግራይ ያሉ ሕገ-ወጥ አስተዳደሮች ፈርስው” ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የደኅንነት ማረጋገጫ መስጠን ይጨምራል ብለዋል።

ይህን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ረዥም ጊዜ ወስዷል የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ረዥም ጊዜ መውሰድ ባይኖርበትም “ከፌደራል መንግሥቱ ጋር አብረን እየሠራን ነው። ከአማራ ክልል ጋርም ቢሆን በተወሰነ ደረጃ አብረን እየሠራን ነው” ብለዋል።

“የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚሹ አካላት እንዳሉ ግን በጣም እርግጠኞች ነን” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው አሁን እየተደረገ እንዳለው ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት የሚቀጥል ከሆነ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች እና ውጥረቶች ተባብሰው ይቀጥላሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ከብልፅግና እና ከጠ/ሚ ዐቢይ ጋር ያለ ግንኙነት

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ከገዢው ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕምድ ጋር አዎንታዊ የሥራ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ነገር ግን ባለፉት ቀናት ትግራይን እያስተዳደረ ያለው ህወሓት ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ሊዋሃድ ስለመሆኑ የወጡ ሪፖርቶች “ፍጹም ሐሰት ናቸው” ሲሉ አስተባብለዋል።

“በቅርቡ የተደረገው ንግግር ከውህደት ጋር የተያያዘ አይደለም። የቅርብ ጊዜ ንግግራችን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ስለማድረግ ነው። ውህደት አጀንዳ ሆኖ አያውቅም” ሲሉ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

በጦርነቱ ወቅት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተፈረጀው እና ዓላማውን በትጥቅ ለማሳካት ተንቀሳቅሷል የተባለው ህወሓት ምንም እንኳን የሽብርተኛ ቡድንነት ፍረጃው ቢነሳለትም አስካሁን ከምርጫ ቦርድ የሕጋዊ ፓርቲነት እውቅናውን አላገኘም።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ስላላቸው ግንኙነት በቢቢሲ የተጠየቁት አቶ ጌታቸው “ጥሩ የሥራ ግንኙነት ነው ያለን። የራሳችን የሆነ ልዩነት አለን። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አመለካከቶች አሉን።”

አክለውም “የፕሪቶሪያው ስምምነት አብረን እንድንሠራ ዕድል ስለሰጠን፤ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችን ምንም ይሁኑ ምን አብረን እንድንሠራ አስችሎናል። ይህም ወደፊት ይቀጥላል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ በሙሉ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ሲሉም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

“ማንም ሰው ቢሆን፤ እኔን ጨምሮ መጠየቅ አለብን። ማንም ነጻ እንዲሆን መፈቀድ የለበትም። ሰላም እና ፍትህ ለማስፈን ያጠፋ መጠየቅ አለበት” ብለዋል።

በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ “አስከፊ” የሚባል መሆኑን የገለጹት ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች እርዳታ ለማድረስ ከፌደራል መንግሥቱ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በተመተባበር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል። በሁሉም ወገኖች በኩል በስምምነቱ መሠረት ተግባራዊ ያልሆኑ ነገሮች አሉ የሚል ቅሬታዎች ሲሰሙ ቆይተዋል።

ከእነዚህም መካከል በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል ያሉትን አወዛጋቢ ጉዳዮችን በተመለከተ ምላሽ የመስጠቱ ሂደት መዘግየቱ ተጨማሪ ግጭት እና መፈናቀል እንሳየስከትል ተሰግቷል።

በገዢው ብልፅግና ፓርቲ እና በህወሓት መካከል ተከታታይ ውይይቶች በአዲስ አበባ እና በመቀሌ ባለፉት ሳምንታት ሲካሄዱ ቆይተዋል። ይህንንመ ተከትሎ በሁለቱ ወገኖች መካከል የውህደት ንግግር እየተደረገ መሆኑ መዘገቡ አነጋጋሪ ሆኗል።

ነገር ግን ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ዜናው ትክክል አይደለም በማለት የስተባበለ ሲሆን፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸውም የውህደቱ ጉዳይ በፓርቲዎቹ ንግግር ላይ አጀንዳ እንዳልነበረ ገልጸዋል።  ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *