የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ አራተኛ ዙር ወረራ በሕዝብ በላይ ፈጽሟል ሲል ከሰሰ።

የክልሉ መንግሥት ዛሬ የሚያዝያ 9/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫው “ከትናንት ታሪካዊ ስህተቱ መማር የተሳነው ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ ለአራተኛ ዙር ሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” ብሏል።

ክልሉ ይህንን ያለው ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ አወዛጋቢ በሆኑት የራያ አካባቢዎች ለቀናት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደ በኋላ በከተሞች አካባቢ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ በዙሪያቸው ደግሞ የህወሓት ታጣቂዎች መግባታቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።

የክልሉ መንግሥት ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ወረራ የፈፀመባቸው የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ መሆናቸውን በመግለጽ የክልሉ ሕዝብ፣ የፌደራል መንግሥቱ እና ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ድርጊቱን እንዲያስቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

ትናንት መግለጫ የሰጡት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጄኔራል ታደሠ ወረደ፣ “በደቡባዊ ትግራይ እና ጸለምት ወረዳዎች”በአማራ ክልል የተቋቋሙ አስተዳደሮችን ለማፍረስ በፌዴራል መንግሥቱ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ስምምነት መደረሱን ተናግረው ነበር።

የማንነት ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩ እና በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበሩ አካባቢዎች ከጦርነቱ በኋላ በአማራ ክልል ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ይታወቃል።

ቀደም ሲል የፌደራል መንግሥቱ ከአወዛጋቢዎቹ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች እንዲመለሱ እና የእራሳቸውን አስተዳደር እንዲያቋቁሙ እንዲሁም በቀጣይነትም ሕዝበ ውሳኔ በማድረግ የይገባኛል ጥያቄዎቹ ምላሽ እንደሚያገኙ ገልጾ ነበር።

የፕሪቶሪያን ስምምነት ተከትሎ ተግባራዊ ካልሆኑ ጉዳዮች አንዱ ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው የመመለስ ጉዳይ ነው ያሉት ጄነራል ታደሰ በቅርቡ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በተደረገው ውይይትም መግባባት ላይ እንደተደረሰም ገልጸዋል።

መግባባት ላይ ተደርሶባቸዋል ካሏቸው ጉዳዮችም መካከል “ተፈናቃዮችን ለመመለስ በዋነኝነት በደቡብ እና ምዕራብ ትግራይ የተቋቋሙ ህገወጥ አስተዳደሮችን ማፍረስ፤ የተደራጁ ታጣቂዎችን ቡድኖችን መበተን” ሌሎች ጉዳዮች ተፈጻሚ እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የፍትህ ስርዓቱ ተጠሪነት ወደ አማራ ክልል የሆነውም ጉዳይ እንደሚመለስ እና ከፌደራሉ ክልል ውጭ ያሉ ኬላዎችም እንደሚፈርሱ ገልጸዋል።

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮችም ክትትል እና ቁጥጥር እና ማረጋገጫ እንዲደረግባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

በዋነኝነት ይህንን የሚተገብረው የመከላከያ ሰራዊት እንደሆነ ገልጸው ክትትል፣ ቁጥጥር እና ማረጋገጫውን ደግሞ በአሁኑ ወቅት በመቀለ ያለው የአፍሪካ ኅብረት የስምምነት ክትትል አረጋጋጭ እና አስከባሪ ኮሚቴም የሚከታተል ይሆናል።

የኮሚቴው አባላት ቁጥር አናሳ ሊሆን ስለሚችል የትግራይ አስተዳደርን ያካተተ ቡድንም ለመመስረትም መግባባት ላይ መደረሱንም ነው የጠቀሱት።

ወረራ ተፈጽሞብኛል ያለው የአማራ ክልል መንግሥት በመግለጫው አወዛጋቢ ቦታዎቹን በተመለከተ በፌደራል መንግሥቱ አማካይነት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት ለማድረግ በርካታ ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም “ህወሓት ይህን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ አካባቢዎች” መውረሩን ገልጿል።

ስለዚህም ህወሓት ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማድረግ ከመሞከር እንዲታቀብ እና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በማክበር በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ጠይቋል።

“ይህ የማይሆን ከሆነ የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድም እና እህት ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሆን አገርን ከማፍረስ መታደግና ሕዝባችንንም ከጥቃት ለመከላከል የምንገደድ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲል አስጠንቅቋል።

ክልሉ በመግለጫው የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሲያፈርስ ቆይቷል ያለው ህወሓት “በሙሉ አቅሙ ወደ ጦርነት ገብቷል” በማለት የፌደራል መንግሥቱ ቡድኑ “በአጭር ጊዜ ከወረራቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ በማድረግ ሕዝባችንን ከጥፋት መታደግ እና የአገራችንን ሉዓላዊነት ማስከበር ይገባል” ሲል ጥሪ አቅርቧል።

አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በተመሳሳይ ትናንት ባወጣው መግለጫ ህወሓት በራያ በኩል “ቀጥተኛ የሆነ ጥቃት” በመክፈት “አራተኛ ዙር ወረራ ፈጽሟል” ሲል ከስሷል።

አብን በመግለጫው፤ “ፌዴራሉ መንግሥት እና የአማራ ክልል መንግሥት በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘውን ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ አበክረን እንጠይቃለን” ብሏል። “በሁሉም አካባቢዎች” የሚገኘው የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ጥቃቱን እንዲመክት ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል መግለጫ ከማውጣቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የትግራይ ክልላዊ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በትግራይ እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚሰተዋለው ግጭት በትግራይ እና በአማራ ወይም በትግራይ እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተፈጠረ አይደለም ብለው ነበር።

ጌታቸው ረዳ በሁለቱ ክልሎች መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎችን የተመለከተ ንግግር በአዲስ አበባ እየተካሄደ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በአካባቢዎቹ የሚታየው ሁኔታ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲተገበር የማይፈልጉ “የስምምነቱ ጠላቶች ሥራ” መሆኑን በመልዕክታቸው አስፍረዋል። “ፀረ ፕሪቶሪያ” ስምምነት የሆኑ “ቅርብ እና ሩቅ የሚገኙ” አካላት “የጦርነት ቅስቀሳ” ቢኖርም ብቸኛው መንገድ “ሰላም” እና “ንግግር” መሆኑን አቶ ጌታቸው ጠቅሰዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በአማራ ክልል ስር የገቡት አወዛጋቢ አካባቢዎች ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኘው በሕዝበ ውሳኔ እንደሆነ የፌደራል መንግሥት መግለፁ ይታወሳል። ጉዳዩን ለመፍታትም ከፌደራል መንግሥት እንዲሁም ሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ ሥራ ላይ መሆኑን የፌደራል መንግሥት አስታውቆ ነበር።

ከሁለት ሳምንት በፊት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ “በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች” ላይ “በትግራይ በኩል” የሚታየው “አዝማሚያ”፤ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ” እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ዶ/ር ለገሰ፤ “ወሰንን በኃይል እናስከብራለን” የሚል አካሄድ “የትግራይ ሕዝብን ለሌላኛው ዙር ስቃይ እና እንግልት የሚዳርግ ነው” ሲሉም በዚህ መግለጫቸው አሳስበው ነበር።   ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *