ካለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጀምሮ የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድባቸው በነበሩ የራያ አላማጣ አካባቢዎች አቅራቢያ የምትገኘው አላማጣ ከተማ በመከላከያ ሠራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር መሆኗን የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የራያ አላማጣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ደርበው መገደላቸውን እና ሌሎች የወረዳው እና የከተማዋ ኃላፊዎች አካባቢውን ለቅቀው ወደ ሌሎች የራያ ወረዳዎች መሄዳቸውንም ገልፀዋል።

ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ በራያ አላማጣ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች ለተከታታይ ቀናት በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ስጋት ውስጥ ገብታ የነበረችው አላማጣ ከተማ በመከላከያ ሠራዊት እና በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የሆነችው ከትላንት ሰኞ ሚያዝያ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ ተናግረዋል።

የራያ አላማጣ ባለሥልጣናት ለተኩስ ልውውጡ ምክንያት የሚያደርጉት በትግራይ ኃይሎች “ተከፍቷል” ያሉትን ጥቃት ሲሆን፣ የትግራይ ክልል ደቡብ ትግራይ ዞን ደግሞ የወረዳ አስተዳደሩ ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸውን በመጥቀስ ሌላውን አካል ተጠያቂ ያደርጋል።

ለቀናት በቀጠለው ግጭት ውስጥ የትግራይ ኃይሎች “ክፍለ ጦሮችን ማሰለፋቸውን” የሚናገሩት የራያ አላማጣ ወረዳ ባለሥልጣናት፤ ታጣቂዎቹ ሌሎች የወረዳውን አካባቢዎች መቆጣጠራቸውን እና ወደ አላማጣ ከተማ እየተጠጉ መሆኑን ሰኞ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ቢቢሲ በዛሬው ዕለት ያነጋገራቸው ሁለት የአላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ከሰኞ ከሰዓት ጀምሮ በርካታ ነዋሪዎች ወረዳውን እና ከተማውን ለቀው በመውጣት ወደ አጎራባች አካባቢዎች መሸሻቸውን ተናግረዋል። ነዋሪዎች “ሸሽተውባቸዋል” ከተባሉ አጎራባች አካባቢዎች አንዱ ቆቦ ከተማ ሲሆን፣ አንድ የቆቦ ከተማ ኃላፊ ከትናትን ጀምሮ በርካታ ወደ ከተማዋ እየገቡ መሆኑን ገልፀዋል።

የራያ አላማጣ ወረዳ እና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎችም ከሰኞ ጀምሮ አካባቢውን ለቅቀው መውጣታቸውን በአሁኑ ሰዓት ቆቦ እንደሚገኙ የገለፁት የአላማጣ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ተናግረዋል። ከትናንት ጀምሮ አላማጣ ከተማን እየተቆጣጠሩ ያሉት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት መሆናቸውን ከንቲባው አስታውቀዋል።

“[አላማጣ] ከተማው መከላከያ እና ፌደራል ፖሊስ ነው ያለው። ዙሪያው የተያዘው ግን በትግራይ ታጣቂዎች ነው” ያሉት አቶ ኃይሉ፤ በከተማዋ “ውስጥ ለውስጥ የትግራይ ታጣቂዎች” አሉ ሲሉ ከስሰዋል።

“ቦታውን ከተቆጣጠሩት እዚያ እየሠራን ነው ማለት አይደለም” ያሉት አቶ ኃይሉ፤ የራያ አላማጣ አካባቢዎች በአማራ ክልል ስር ከሆነ በኋላ በተመሠረው የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የነበሩት ኃላፊዎች በአሁኑ ሰዓት ከተማውን እያስተዳደሩ አለመሆኑን ገልፀዋል።

የራያ አላማጣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ሞላ ደርበው እና ለሌች ቁጥራቸውን ያልገለጿቸው ሰዎች በትናንትናው ዕለት መገደላቸውን ከንቲባው ተናግረዋል። የአቶ ሞላ ህልፈት ምክንያት ከትግራይ ኃይሎች ጋር በተደረገ “ውጊያ” አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

“[አቶ ሞላ ሕይወታቸው ያለፈው] ከህወሓት ጋር በተያያዘ አይደለም። ሕግ የያዘው ነገር ስለሆነ ተጣርቶ የሆነ ነገር እስከሚባል ድረስ ዝርዝሩን [አልገልፅም]” ሲሉ ምክንያቱን ከመናገር ተቆጥበዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት ምሽት በማኅበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ “በደቡባዊ ትግራይ እና ሌሎች የተያዙ የትግራይ ግዛቶች” ያለው ሁኔታ በፌደራል መንግሥት እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲሁም የትግራይ እና የአማራ ክልል የተፈጠረ ግጭት እንዳልሆነ ገልፀዋል።

በአካባቢዎቹ የሚታየው ሁኔታ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲተገበር የማይፈልጉ “የስምምነቱ ጠላቶች ሥራ” መሆኑን በመልዕክታቸው አስፍረዋል። “ፀረ ፕሪቶሪያ” ስምምነት የሆኑ “ቅርብ እና ሩቅ የሚገኙ” አካላት “የጦርነት ቅስቀሳ” ቢኖርም ብቸኛው መንገድ “ሰላም” እና “ንግግር” መሆኑን አቶ ጌታቸው ጠቅሰዋል።

አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ ህወሓት በራያ በኩል “ቀጥተኛ የሆነ ጥቃት” በመክፈት “አራተኛ ዙር ወረራ ፈጽሟል” ሲል ከስሷል። አብን በመግለጫው፤ “ፌዴራሉ መንግሥት እና የአማራ ክልል መንግሥት በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ የሚገኘውን ወረራ በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ አበክረን እንጠይቃለን” ብሏል። “በሁሉም አካባቢዎች” የሚገኘው የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ጥቃቱን እንዲመክት ጥሪ አቅርቧል። ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *