በመሐል አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ ፖሊስ የፋኖ አባላት ናቸው ካላቸው ግለሰቦች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርጎ ሁለቱን መግደሉን ለቢቢሲ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለቢቢሲ እንደገለጹት ዛሬ አርብ ሚያዝያ 4/2016 ዓ.ም. ፖሊስ ክትትል ሲያደርግባቸው በነበሩ የቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ ወስዶ አመራር ነው የተባለ ግለሰብ ተገድሏል።

የቡድኑ አባላት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ “የሽብር ተግባር ለመፈጸም” በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ በፀጥታ ኃይሉ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፍቃደኛ ከመሆን ይልቅ በፀጥታ አካላት ላይ ተኩስ በመክፈት በሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንዳደረሱ የጸጥታና ደኅንነት ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ አትቷል።

የከተማዋ ፖሊስ ግለሰቦቹን በሽብር ተግባር ጠርጥሯቸው ሲከታተላቸው እንደነበረ የጠቀሱት የፖሊስ ኃላፊው፣ “የፋኖ አመራሮች” ናቸው ካላቸው ጋር በተፈጠረ የተኩስ ልውውጥ ሁለቱ ሲገደሉ አንዱ ጉዳት ሳይደርስበት መያዙን ገልጸዋል።

በተኩስ ልውውጡ ወቅት ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን ጨምሮ አራት ሰዎች መቁሰላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ባወጣው መግለጫም አስታውቋል።

ምክትል ኮማንደር ማርቆስ የፋኖ አባላት ናቸው ባሏቸው ናሁሰናይ አንድአርጌ ታረቀኝ፣ አቤኔዜር ጋሻው አባተ እና ሀብታሙ አንድአርጌ ተሰማ ላይ ፖሊስ ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ ሚያዚያ 4/2016 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር ለማዋል ሲሞክር በተሸከርካሪ ለማምለጥ መሞከራቸውን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ዲዛዬር መኪና በመጠቀም በፖሊስ አባላት ላይ ተኩስ መክፈታቸው ተገልጿል። በዚህም ፖሊስ የፋኖ መሪ ነው ያለው ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ በተኩስ ልውውጡ ከቆሰለ በኋላ ወደ ህክምና ተወስዶ ሕይወቱ አልፏል ብሏል።

ናሁሰናይ አንዳርጌ “የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ የመለመላቸው ወጣቶች ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የፋይናንስና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ከሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸው በማሰባሰብ ሁኔታዎችንም ሲያመቻች እንደነበር የግብረ ኃይሉ መግለጫ ጠቅሷል።

ግብረ ኃይሉ ጽንፈኛ ሲል የጠራው ቡድን አባላት “የሽብር ጥቃት ለማድረስ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ህቡዕ እንቅስቃሴ ሲያደርጉም” እንደነበር እና ክትትል እየተደረገባቸው ነበር ብሏል።

ምክትል ኮማንደር ማርቆስ “ናሁሰናይ አንዳርጌ የሚባለው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረገው እንቅስቃሴ እጅ ላለመስጠት ከፍተኛ የሆነ ትግል ነው ያደረገው። ከዚያም አልፎ በዚያ አካባቢ የሚሄድ አንድ ግለሰብ ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል። ሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ተኩስ ከፍቶ ከባድ ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።

ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ በተኩስ ለውውጡ መሃል መገደሉ ተገልጿል።

አቤኔዘር ጋሻው አባት የተባለው ሦስተኛው ተጠርጣሪ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

እንደ አዲስ አበባ መግለጫ ከሦስቱ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ አንድ ሰላማዊ ሰው መገደሉን እና ሁለት የፖሊስ አባላት መቁሰላቸው አመልክቷል።

ሳጅን አራርሳ ተሾመ እና ኮንስታብል ማቲያስ ጴጥሮስ የተባሉ የፖሊስ አባላት በተኩስ ልውውጥ መቁሰላቸውን ፖሊስ የገለጸ ሲሆን፤ እንዳሻው ጌትነት የተባሉ ግለሰብ ተፈላጊዎቹን አልተባበርም በማለታቸው “በፅንፈኛው አባላት ተገድለዋል” ብሏል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የተኩስ ልውውጥ በተፈጸመበት አካባቢ ነዋሪ ከሆኑ አንድ ግለሰብ ሁለት መንገደኞች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የተኩስ ልውውጡ የተፈጸመው ከሚሊኒየም አዳራሽ ጎን በሰንሸይን ቪላ ቤቶች ወደ ቦሌ መድኃኒያለም ወደሚያስወጣ መንገድ ላይ መሆኑን በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ለወራት ከዘለቀው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ስሙ የሚነሳው የፋኖ ቡድን አባላት እና አመራር ናቸው የተባሉት ግለሰቦችን ለመያዝ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ፖሊስ ገልጿል።    ዘገባው የቢቢሲ ነው፡፡

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *